Exif_JPEG_420

ከአምስት ሺህ አራት መቶ በላይ ካሬ መሬት ላይ የተጀመረው ማስፋፊያ ግንባታ ለአከባቢው ማህበረሰብ የሚሰጠውን ህክምና አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተሻለ ጥራት ለመስጠት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የተጀመረው ተጨማሪ የሆስፒታሉ ግንባታ ማስፋፊያ በሁለት አመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን ግንባታውም በርካታ ገንዘብ ተመድቦ በዘመናዊ አሰራር የሚሰራ በመሆኑ በታቀደው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቅ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግበት ስርዓት ጭምር ተዘርግቶ መጀመሩን የሆስፒታሉ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኃላፊ እንጂነር በፀጋው አክሊሉ ተናግረዋል።

የማስፋፊያ ግንባታ ለመጀመር የታቀደው ቀደም ተብሎ ቢሆንም ከባለ ይዞታዎች ጋር በተያያዘ በተባለው ጊዜ መጀመር አለመቻሉን ገልፀው አሁን ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩ ተፈቶ ወደ ስራ መገባቱን እንጂነር በፀጋው ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ በከተማዋ ደረጃውን የተጠበቀ ዘመናዊ ባለ 9 ወለል ህንፃ ላይ የራዲዮቴራፒ፣ የኬሞቴራፒ፣ አለም የደረሰበት ዘመናዊ ከፍተኛ የቀዶ ህክምና አገልግሎት እንዲሁም ለሴቶችና ለህፃናት የሚሰጠውን ህክምና ወደተሻለ ደረጃ በማሸጋገር ከሀገራችንም አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ ያደርገዋል እንደሚያደርገውም እንጂነር በፀጋው በተለይም ከ”ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ” ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ከ5400 በላይ ካሬ መሬት ይዞታ ላይ የተጀመረው ማስፋፊያ ፕሮጀከት ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የተሻለ ህክምና ከመስጠት ባሻገር ለበርካታ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች የስራ ዕድል የሚፈጥር ለከተማው ፈጣን እድገት የራሱን አስተዋጾ እንደሚያበረክትና በግንባታ ሂደትም ከሶስት መቶ በላይ ሰዎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ኃላፊው አክለው ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት የተገልጋዮችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን በዘመናዊ መንገድ በጥራት እና በስፋት ለመስጠት በማለም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በይፋ መጀመሩን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ገብረስላሴ ለ”ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ” ተናግረዋል።

ተጨማሪ ግንባታው ከዚህ በፊት በሆስፒታሉ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን በጥራትና በስፋት ከመስጠት በተጨማሪ በምስራቅ አፍርካ የራዲዮቴራፒ፣ የኬሞቴራፒ፣ ከፍተኛ የአጥንት ስፔሻሊስቶች ትምህርት የሚማሩበት ማዕከል እንደሚያካትትና አገልግሎት ለማግኘት ከሩቅ ቦታ መጥተው ተራ በመጠበቅ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ለሚያባክኑ ወገኖች እፎይታ የሚፈጥርና በአከባቢው የህክምና ቱሪዚም ፈሰት የሚጨምር መሆኑንም አቶ ኤፍሬም አብራርተዋል።

የማስፋፊያ ስራው መጀመሩ ዘመናዊ ህክምና ዘርፍ በጥራት ለመስጠት የሚያስችል በተላይም ለሴቶችና ህፃናት የሚሰጠውን ህክምና ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ለዎላይታና ለአከባቢው እንዲሁም ለአጎራባች ህዝቦች ብሎም ለመላው ኢትዮጵያዊያን መልካም ዜና እንደሆነም አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሆስፒታሉ ተጨማሪ ግንባታ ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ ደረጃ ከዚህ በፊት ያልተጀመረ የህክምና አገልግሎት በዘመናዊ መሳሪያዎች እንዲጀመር የሚያስችልና በተላይም የእናቶችና የህፃናት ህክምናን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝም ስራ አስኪያጁ አክለዋል።

የዎላይታ ሶዶ ክርስቲያን አጠቃላይ ሆስፒታል ከተለያዩ ሀገራትና ሀገር ውስጥ የተሰበሰቡ እውቅ የጤና ባለሙያዎች በሚሰጠው ህክምና አገልግሎቶች ከአፍሪካ ከሚገኙ አስር ሆስፒታሎች መካከል አንዱ ሲሆን በዛሬው ዕለት የተጀመረው ተጨማሪ ግንባታ ሲያልቅ እንዲሁም ዘመናዊ የህክምና መሣሪያዎች አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ በሀገሪቱ ጤና አገልግሎት ዘርፍ የራሱን ሚና ለመጫወት መታቀዱንም የ“ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ” ከሆስፒታሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በዎላይታ ታይምስ ሚዲያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: