የዎላይታ ሶዶ ክርስቲያን አጠቃላይ ሆስፒታል ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ግንባታና የህክምና ቁሳቁስ አገልግሎት በቅርቡ እንደሚጀመር ተገልጿል።

የማስፋፊያ ክፍሎቹ ስምንት የተለያዩ ከፍተኛ የቀዶ ህክምና ክፍሎችን ያካተተና አስራ ሶስት አጋዥ የተለያዩ ክፍሎች የያዘ ዘመን የደረሰበት የህክምና ቁሳቁስ የተገጠመለት መሆኑም ተነግሯል።

የተሰራው የማስፋፊያ ግንባታ ለማጠናቀቅ አንድ አመት የታቀደ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች አራት ወራት መዘግየቱን የገለፁት የሆስፒታሉ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኃላፊ እንጂነር በፀጋው አክሊሉ ጥራት ያለው ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ጥራት ያለው ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ያንን በሚመጥን ደረጃ መገንባቱን አስረድተዋል።

በሆስፒታሉ ግቢ ወስጥ የተሰራው ይህ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ከግንባታ ሂደት ጀምሮ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ከፍተኛ የቀዶ ህክምና ማሽኖችንና ዘመናዊ የአጥንት ቀዶ ህክምና ቁሳቁሶችን በእያንዳንዱ ክፍሎች ለመትከልና ለመገጣጠም በሚያመች አኳኋን ለማደራጀት መቻሉንም እንጂነር በፀጋው ገልጸዋል።

ማስፋፊያው ዘመናዊ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ የግንባታ ጥራት ተጠብቆ እንዲሰራ ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር አሰራር ተዘርግቶ የተሰራ ሲሆን በተጨማሪም የህክምና ስፔሻሊስት ተማሪዎች የሚኖሩበት ህንፃም በተጓዳኝ መገንባቱን ኃላፊው አስረድተዋል።

ሆስፒታሉ ወቅቱ የደረሰበት ጥራት ያለው ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ጥራት ያለው የግንባታ ስራ እንዲሁም ለህክምና አገልግሎት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከቀናት በፊት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ደረጃውን የተጠበቀ ዘመናዊ ባለ 9 ወለል ህንፃ ለመገንባት መጀመሩም የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ወደተሻለ ደረጃ በማሸጋገር ከሀገራችንም አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ይበልጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም እንጂነር በፀጋው በተለይም ከ”ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ” ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ እየጨመረ የመጣውን የተገልጋዮችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን በዘመናዊ መንገድ በጥራት እና በስፋት ለመስጠት በማለም የማስፋፊያ ስራ መከናወኑን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ገብረስላሴ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተናግረዋል።

ተጨማሪ ግንባታው ከዚህ በፊት በሆስፒታሉ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን በጥራትና በስፋት ከመስጠት በተጨማሪ ከፍተኛ የአጥንት ቀዶ ህክምና ክፍሎች እጥረትን በመቅረፍ እንዲሁም እጂግ ዘመናዊ የህክምና ቁሳቁስ የተገጠመላቸው ክፍሎቹን ያካተተ በመሆኑ ለተገልጋዮች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑንም አቶ ኤፍሬም አብራርተዋል።

ለማስፋፊያ ግንባታው በአጠቃላይ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግንባታውና በየክፍሎቹ ከፍተኛ የቀዶ ህክምና ቁሳቁስ ገጠማ እየተከናወነና ቀሪዎቹ ቁሳቁስ ከውጪ ሀገር እየገቡ ሲሆን በጥቂት ወራት ውስጥ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመርም አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ በሚሰጠው ህክምና አገልግሎቶች ከአፍሪካ ከሚገኙ አስር ሆስፒታሎች መካከል አንዱ ሲሆን በአሁኑ የተጠናቀቀውና በቅርቡ በግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የተጀመረው ተጨማሪ ማስፋፊያ ግንባታ ሲያልቅ እንዲሁም ዘመናዊ የህክምና መሣሪያዎች አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ በሀገሪቱ ጤና አገልግሎት ዘርፍ የራሱን ሚና ለመጫወት መታቀዱንም ከሆስፒታሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: