ህዝበ ውሳኔውን በመቃወም የምርጫ ካርድ የሚወስድ ሰው በመጥፋቱ በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መታወቂያ ስም ጭምር ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑም ተጠቁሟል።

የምርጫ አስተባባሪዎች ከአመራሮቹ ጋር በመመሳጠር ከዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ ሬጂስተራል የተማሪዎች ስም ዝርዝርና መታወቂያ በማስመጣት ለህዝበ ውሳኔ ምርጫ ካርድ እንደወሰዱ በማድረግና በማስመሰል ከህግ አግባብ ውጪ እየመዘገቡ እንደሆነ ከስፍራው ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል በአከባቢው ህዝበውሳኔው ህዝቡ የሚፈልገው አማራጭ ያልተካተተበት በመሆኑ ህብረተሰቡ ካርድ ላለመውሰድ ህዝባዊ እምቢተኝነት በመግጠሙ የአከባቢው አመራሮች ከፖሊስ ጋር ቤት ለቤት እየሄዱ ህብረተሰቡ በግድ እንዲወስዱ ለማድረግ እያስገደዱ መሆኑም ተገልጿል።

የህዝበውሳኔ ምርጫ ካርድ የሚወስድ ሰው በመጥፋቱ አመራሮቹ ከሌላ አከባቢ በትልቅ መኪና ጭኖ ሰው በማምጣት መታወቂያ መስጠትና ማስመዝገብ፣ የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ስምና መታወቂያ ከአመራሮቹ በመናበብ በማስመጣት ሰው እንደተመዘገበ ተደርጎ መፃፍ፣ በዞኑ የተለያዩ ኮሌጆች የሚማሩ ተማሪዎች ዝርዝር ማስመዝገብ፣ ከወሳኝ ኩነት መዝገብ የሞቱ ሰዎች ስም ዝርዝር አምጥቶ ማስመዝገብ፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ዝርዝር፣ ስምና መታወቂያ ተዘጋጅተው እንደተመዘገበ ተደርጎ በምርጫ መዝገብ ላይ እየሰፈረ መሆኑንም ታማኝ ምንጮች ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የእውነት የህዝበ ውሳኔ ካርድ የወሰደ በአከባቢው ከአመራሮቹና በግል ጥቅም ከተደለሉ ግለሰቦች ውጪ አንድም ሰው በፍቃደኝነት ካርድ አለመውሰዱን በመግለፅ ይሄንን ከህዝብ ፍላጎት ውጪ ለማስፈጸም እየተሞከረ የሚገኘውን ህገወጥ አካሄድ የሚመለከተው አካል ውሸት ከሆነ አስቸኳይ ማጣሪያ አድርጎ እውነተኛ የህዝብ ፍላጎት እንዲያዳምጥ ስል “#በእግዚአብሔር” ስም ተማፅነዋል።

ከዲላ ጌዲኦ፣ ጎፋ ዞኖችና እንዲሁም ከሌሎች አከባቢዎችም ተመሳሳይ ጫና እየተደረገ ስለመሆኑ ከየስፍራው በተጨባጭ በWT ታማኝ መረጃ ምንጮች አማካይነት የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ይካሄዳል ለተባለው “ህዝበ ውሳኔ” ምርጫ በዎላይታ ዞን ከየትምህርት ቤታቸው ለመመዝገብ የሚያስችል መታወቂያ ሆነ ለመራጭነት ዕድሜያቸው ያልደረሰ በግዳጅ በፓሊስ ታጅበው ተማሪዎች ካርድ እንዲወስዱ እየተገደዱና ይካሄዳል በተባለው ሕዝበ ውሳኔ ላይ ላለመሳተፍ በርካቶች “የምርጫ ካርድ ባለመውሰድ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ከመግለፁ” የተነሳ የሕዝበ ውሳኔው ምዝገባ ከሚደረግበት የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች በመውጣት ወደየቤተ እምነቶች በማቅናት ወደየ ቤተክርስቲያን ማለዳ ለሚገቡ ምዕመናን በር ላይ ለማደል ቢሞክሩም ሕዝባዊ ተቋውሞ መግጠሙን መግለፃችን የሚታወስ ሲሆን ምርጫ ቦርድም በጉዳዩ ዙሪያ ትክክል በመሆኑ ማስጠንቀቂያ በመስጠት እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል።

በተያያዘም በአከባቢው የሚንቀሳቁሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ይደረጋል የተባለው ምርጫ “የህዝብ ፍላጎት ያልተካተተበትና የሀገሪቱን ህገመንግስት በግልጽ የጣሳ አካሄድ ብሎ በህጋዊ መንገድ ለሚመለከታቸው አካላት አቤቱታ ቢቀርብም እስካሁን በእምቢተኝነት እየሄደ መሆኑን በመግለፅ ያለህዝብ ፍላጎት በግድ የሚጫን ነገር አላስፈላጊ ዋጋ እንደሚያስፈልግም መጠቆሙን” ዘግበን ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: