የአዲሱ ክልል ምሥረታ እና የነባሩ ክልል ዕጣ ፈንታ ምንድነው ?

በስድስት ዞኖች እና በአምስት ልዩ ወረዳዎች የሚያቋቁመው ክልል “ደቡብ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ ይሰጠዋል።

ነባሩ ክልል የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚለው መጠሪያ ወደ “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ ለመቀየር መታቀዱ ተሰምቷል።

ሁለቱን ሥራዎች ለማከናወንም፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምሥረታ እና ነባሩን ክልል በአዲስ የማደራጀት ተግባር ማስፈጸሚያ የሚል ስያሜ ያለው ጽህፈት ቤት ተከፍቷል።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው፣ በደቡብ ክልል ለረጅም ጊዜ በኮሚዩኒኬሽን ባለሙያነት የሰሩት እና አሁን መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጀት ውስጥ የሚሰሩት አቶ ዳያሞ ዳሌ፣ የሚደራጁት ክልሎች እንደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አንድ ዋና ከተማ ላይኖራቸው ይችላል ይላሉ።

ለዚህም መነሻ ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ በሚደራጀው እና ከኬንያ ድንበር እስከ ዎላይታ የሚያካልለው አዲሱ ክልል እንደ ርዕሰ መስተዳደር ጽ/ቤት ያሉ “ወሳኝ” ተቋማት በአርባ ምንጭ ከተማ ላይ ሊመሰረት እንደሚችል “አዝማሚያው ያሳያል” ብለዋል።

ዎላይታ ሶዶ፣ ሳውላ እና ጂንካም ቁልፍ መንግሥታዊ ተቋማትን በስራቸው ሊይዙ እንደሚችል ያነሱ ሲሆን፣ ልዩ ወረዳዎችም “አንዳንድ መሥሪያ ቤት ይድረስን” የሚል ጥያቄ እንዳላቸው “ጉምጉምታ አለ” ብለዋል።

ከውስጡ ሦስተኛ ክልልን ሊመሰረት የተቃረበው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም ሕዝበ ውሳኔው ሳይካሄደበት እንደ አዲስ ይደራጃል።

በስሩም ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሀላባ፣ ሃዲያ፣ ከንባታ ጠምባሮ ዞኖች እና የየም ልዩ ወረዳን የሚያጠቃልል ይሆናል።

ይህንንም ለማድረግ፣ ክልሉ ሕገ መንግሥቱ ላይ ለውጥ ለማድረግ ተዘጋጅቷል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በክላስተር የመደራጀት ሃሳብን ውድቅ በማድረጉ እዚህ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።

ክልሉም ለአስርት ዓመታት ከነበረበት ሐዋሳ ከተማ በ“ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” ስር ወደሚካተቱ ከተሞች የሚሸጋገር ይሆናል።

ክልሉ ከአንድ በላይ ዋና ከተማ ሊኖረው እና የርዕሰ መስተዳድሩ መቀመጫም ሆሳዕና ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

የክልል ምሥረታ ምን ለውጥ ያመጣል?
አቶ ዳያሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደተወለዱበት አካባቢ እየሄዱ “ነጯን እርግብ ምረጡ” የሚል ቅስቀሳ እያካሄዱ ስለመሆናቸው ይናገራሉ።

ይህም ሕዝበ ውሳኔው በሕዝብ ተቀባይት እንዲኖረው ለማድረግ እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን፣ የአዲስ ክልል መደራጀት ከነዋሪዎች ሕይወት አኳያ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የላቸውም።

“ምክንያቱም ክልሉን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ተመሳሳይ ፓርቲ እና ባለሥልጣናት ናቸው። ስለዚህ ከተማ ወደ እኛ ቀረበ ከሚል በስተቀር ብዙም ለውጥ ያመጣል የሚል ግምት የለኝም። መሠረታዊ ለውጥ የሚጠበቀው ወይ ፖሊሲ ወይ ፓርቲ ሲቀየር ነው” የሚሉት አቶ ዳያሞ ለውጥ ለማምጣት ክልል መመስረት የግድ አይደለም ይላሉ።

“ከታች ላለው ሕዝብ መሠረታዊ አገልግሎት ያለው ወረዳ እና ቀበሌ ላይ ነው። እዚያ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ እና ሙስናን መከላከል ነው እንጂ ክልል ስለተፈጠረ ለውጥ አይኖርም” ሲሉ ይከራከራሉ።

የክልል መመሥረት እና የዋና ከተሞች ለዜጎች ቅርብ መሆንን ብዙም ለውጥ አያመጣም የሚሉት አቶ ዳያሞ፣ በዋናነት ለወረዳ አስተዳዳሪዎችና ካድሬዎች አመቺ ሁኔታን ከመፍጠር በስተቀር ለተራው ሕዝብ ጥቅሙ እምብዛም ነው ይላሉ።

“አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ወደ ክልል ከተማ የሚያመላልሳቸው ጉዳይ የለም። ክልል ከሕዝብ አገልግሎት አንጻር ሩቅ እርከን ነው። ትክክለኛው አገልግሎት ለሕዝቡ የሚቀርበው በወረዳ እና በቀበሌ ነው።”

በሌላ በኩል አንድ ክልል ለመመሥረት ከተዘጋጁት 6 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች መካከል ጌዲዮ ዞን ከተቀሩት አካባቢዎች ጋር ምንም የየብስ ግንኙነት የለውም።

ዞኑ በደቡብ እና በምሥራቅ ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ጋር የሚዋሰን ሲሆን፣ በሰሜን በኩል ደግሞ ከሲዳማ ክልል ጋር ይወሰናል። ይህ ማለት በጌዲዮ ዞን እና በአማሮ ልዩ ወረዳ መካከል ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን እና በኦሮሚያ ክልል ስር ያለ አካባቢ አለ።

አካባቢው በፀጥታ ችግርም የሚፈተን ነው።

ይህንን ውሳኔ በጌዲዮ ዞን ካሉ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች ቢቃወሙትም የዞኑ ምክር ቤት ይሁንታን ሰጥቶታል።

ሲዳማ ክልል እስኪ መሰረት ድረስ የየም ልዩ ወረዳ ከቀሪው የደቡብ ክልል ጋር በየብስ የማይተሳሰር ብቸኛው አካባቢ የነበረ ሲሆን በሲዳማ ክልል መመስረት ምክንያት ጌዲዮ ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሞታል።

እነዚህን ሁኔታዎች በቀጣይ የሚመሰረቱት ክልሎች መፍትሄ ይፈልጉለታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *