በጦርነቱ ጊዜ የዜና ሽያጭ በትግራይ ክልል
በትግራይ ክልል ማንኛውም ዓይነት የመገናኛ ዘዴዎች ተቋርጠው በነበሩበት ጊዜያት ዜጎች የዶቼቬለን ጨምሮ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ዜና እና ሌሎች ወቅታዊ መረጃዎችን እንዴት ያገኙ ነበር? አንዳንዶች ኤሌክትሪክ ኃይል ባልነበረበትና የመገናኛ ዘዴዎች በተዘጉበት ወቅት በውድ ዋጋ ባትሪ ድንጋይ በመግዛት ጭምር የዶቼቬለ ስርጭትን ለመከታተል ይጥሩ ነበር።

በትግራይ ክልል ማንኛውም ዓይነት የመገናኛ ዘዴዎች ተቋርጠው በነበሩበት ጊዜያት ዜጎች የዶቼቬለን ጨምሮ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ዜና እና ሌሎች ወቅታዊ መረጃዎችን እንዴት ያገኙ ነበር? አንዳንድ አድማጮች እንደገለጹት የኤሌክትሪክ ኃይል ባልነበረበት እና የመገናኛ ዘዴዎች በተዘጉበት ወቅት በውድ ዋጋ ባትሪ ድንጋይ በመግዛት ጭምር የዶቼቬለ ስርጭትን ለመከታተል ይጥሩ ነበር። በተለይም በመቐለ ኗሪ የሆኑት ደግሞ መረጃዎችን ኢንተርኔት በሚያገኙ ሰዎች በኩል በስልክ ወይንም በኮምፒተር ምስል አንስቶ በማተም ቅጂዎችን (ስክሪሾት) በመግዛት የመረጃ ጥማቸውን ያሟሉ እንደነበር ተናግረዋል።   

ስልክ እና ኢንተርኔት ጨምሮ ሁሉም የመገናኛ አማራጮች ጠፍተው በነበሩበት ግዜ በመቐለ የሚገኙ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች የነበረውን መዘጋጋትና የመረጃ እጦት ለመሙላት የጀመሩት ስራ ነው፦ ከዶቼቨለ ጨምሮ ከተለያዩ ሚድያዎች፣ ማሕበራዊ መገናኛዎች የተወሰዱ ዜናዎች ስክሪን ቅጂ ለፈላጊዎች መሸጥ። በመቐለ በተለይም በከተማዋ እምብርት ሮማናት አደባባይ በስፋት የሚካሄደው የስክሪን ቅጂ፣ የድምፅ ምስል ዜናዎች ሽያጭ የሕብረተሰቡ የመረጃ ፍላጎት በመጠኑም ቢሆን የሚሞላ፣ የመረጃ እጦት በነገሰበት ወቅት አማራጭ መረጃ ማግኛ ዘዴ ሆኖ ረጅም ግዜ ቆይቷል።

በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዕለታዊ ዜናዎች ከዶቼቨለ የማሕበራዊ መገናኛ ገፅ እንዲሁም ከተለያዩ የዜና አውታሮች፣ የፌስቡክ ልጠፎች ተቀናጅተው የመረጃ ጥም ሊቆርጡ በአስር ብር ይሸጣሉ። ተጠቃሚዎችም የስክሪን ቅጂዎቹ እና ሌሎች የድምፅና ምስል ፋይሎች ኔትዎርክ አልባ በነበሩ ስልኮቻቸው ላይ አልያም ፍላሽ ላይ ጭነው ይወስዳሉ። 

የመረጃ ጦት በነበረበት ጊዜ ትግራይ ክልል መረጃዎችን ማሰራጪያ ዘዴዎች፤ ወጣት ልጅ መንገድ ዳር ኮምፒተር ፊት ይታያል
የኢንተርኔት አገልግሎት ባልነበረበት ወቅት እነዚህ የስክሪክ ቅጂዎች፣ በምስል እና ድምፅ የሚቀርቡ መረጃዎች ከየት ይገኙ ነበር ለሚል ጥያቄ ፣ አገልግሎቱ የሚያቀርቡ ወጣቶች ሲመልሱ፥ ዋነኛ ምንጫቸው በአንዳንድ የውጭ መስርያቤቶች ያሉ የተለየና የማይቋረጥ የኢንተርኔት አገልግሎት ከነበራቸው ግለሰቦች መሆኑ ያስረዳሉ።  

ወጣቱ ዳኒኤል አምሃ ከጦርነቱ ጅማሮ በፊት ሶስተኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ እንደነበረ ገልፆልናል። በጦርነቱ ምክንያት ከትምህርት ገበታው ሲለይ፣ የራሱን መረጃ የማግኘት ፍላጎት ለመሙላት፦ ከሚያውቃቸው የዩኤን ሰራተኞች የየዕለቱ የፌስቡክ ስክሪን ቅጂ በመቀበል የጀመረው ልምድ በሂደት ተፈላጊነቱ በማየቱ ወደ ስራ በመቀየር ከተመረጡ ሚድያዎች፣ ታዋቂ ጦማርያን ገፃችን እንዲሁም ሌሎች ያካተተ በየቀኑ ከ70 እስከ 100 የስክሪን ቅጂዎች ለፈላጊዎች ማቅረብ መጀመሩ አጫውቶናል።

ከአንድ ዓመት በላይ በስራው መቆየቱ የገለፀልን ዳኒኤል በሂደት ከስክሪን ቅጂ በተጨማሪ ከየዩትዮብ ገፁ የሚገኙ ዜናዎች፣ የቴሌቪዥን ውይይቶች፣ የዓለምአቀፍ ሚድያዎች ዘገባዎች ያካተተ የዜናና መዝናኛ ፓኬጅ አልያም (ማእቀፍ) ለተጠቃሚዎች መሸጥ፣ መግዛት ለማይችሉት ደግሞ ከግል ላፕቶፑ በማጉልያ በመክፈት ያሰማል። 

አብዛኞቹ በየጎዳናው የስክሪን ቅጂ እና የድምፅና ምስል መረጃዎች የማቅረብ ስራ የሚከውኑ ወጣቶች የዪኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩ፣ የኢንተርቴመን ድርጅቶች እና የኢንተርኔት ካፌ የነበራቸው በጦርነቱ ምክንያት ግን ከስራ ውጭ የሆኑ ናቸው። እንደ ዳኒኤል ተመሳሳይ ስራ የሚሰራው በመቐለ ሮማናት አደባባይ የሚሰራው ዮናስ አረጋዊ በበኩሉ  ታማኝ የተባሉ የዜና ምንጮች በመምረጥ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ያላቸው ሰዎች እንዲያወርዱላቸው በማድረግ ለደንበኞቹ መረጃ እንደሚሸጥ ገልጿልናል። “እንደነ ቢቢሲ፣ ዶቼቬሌ ፣ ቪኦኤ የመሳሰሉ ዓለምአቀፍ ሚድያዎች የሚያቀርቡት ዘገባ ጨምሮ፣ ከሀገር ውስጥ ደግሞ ታማኝ የተባሉት በመምረጥ፣ ለአድማጭ እናቀርባለን” ይላል ዮናስ።

በዚህ መረጃ የመሸጥ ስራ የተሰማሩ ወጣቶች እንደሚሉት በቅርቡ የስልክ፣ ኢንተርኔት፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መመለሱ ተከትሎ የስክሪን ቅጂ ሽያጭ ስራው ተቀዛቅዟል።
የኤሌክትሪክ፣ ኢንተርኔት ይሁን ስልክ አገልግሎት ባልነበረባቸው ረዥም ወራት በትግራይ የሚገኙ የሚድያ ተከታታዮች በአብዛኛው መረጃዎች ያገኙ የነበሩት በባትሪ ከሚሰሩ ሬድዮዎች በሚሰራጩ ዶቼቬሌ የመሰሉ ጣብያ እንደነበር ገልፀዋል።

ላለፊት ከ30 በላይ ዓመታ የዶቼቬሌ የራድዮ ስርጭት ይከታተላሉ እንደነበር የገለፁልን የሽረ ከተማ ነዋሪው እና አሁን ተፈናቅለው ዓብይዓዲ ከተማ እንዳሉ የገለፁልን አቶ ብርሃነ ታፈረ  ኤሌክትሪክ ባልነበረበት፣ ለሬድዮአቸው የሚሆን ባትሪ ለማግኘት እንኳን አስቸጋሪ በሆነበት ያለፉት ጨለማ ግዜያት የዶቼቬሌ የየዕለቱ ስርጭት ለመከታተል ለአንድ ባትሪ 150 ብር እየገዙ የጣብያው ዜናዎች ይከታተላሉ እንደነበር አጫውተውናል። አቶ ብርሃነ እንደሚሉት “ሽረ እያለን 150 ብር ለአንድ ባትሪ እየገዛሁ ነበር ዶቼቬሌን እሰማ የነበረው። ሁሉ ነገር የተዘጋ በመሆኑ 150 ብር አውጥቶ እንኳን ባትሪ ለማግኘት አስቸጋሪ ነበር። መረጃ ማግኘት ትልቅ ነገር ነው። ብዙ ሰው ምን አዲስ ነገር አለ የሚል ለመጠየቅ እኔ ጋር ነው የሚመጣው። በተለይም ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ዜና ሲያቀርብ ደስ ይለኛል። ከነበርኩበት የአንድ ሰዓት የዶቼቬሌ ዜና እንዳያመልጠኝ ቶሎ ነው ቤት የምደርሰው” በማለት የቅርቡ ትዝታቸው አውግተውናል።

ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ባለው ግዜ በየአቅጣጫው ምን እየሆነ እንዳለ ለማወቅ፣ ዜናና የተለያየ መረጃ ለማግኘት ይደረግ የነበረ አስቸጋሪ ጥረት ቀንሷል። በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰሩ ራድዮና ቴሌቭዥኖች፣ በኔትዎርክ የሚሰሩ ስልኮች ወደ ተለመደ አገልግሎታቸው በከፊል ተመልሰዋል። ያለፈው ጨለማ ግዜ ግን የቅርብ ትዝታ ሆኖ ይታወሳል ስል ዶቼቬሌ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *