ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ለኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር/ማኔጅመንት በዛሬው እለት በነበረው አስቸኳይ ስብሰባ ጁንታው የሕወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት እጅግ የሚወገዝ ተግባር መሆኑን አሳውቋል።
የማኔጅመንቱ አባላት በዛሬው የውይይት መድረክ ለቁርጠኛውና የሀገር መከታ ለሆነው ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አገልግሎት እንዲውል በዩኒቨርሲው ለድጋፍ ከተያዘ በጀት የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ መወሰናቸውንም ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት ለማሳየትና አጥፊው የሕዋሃት ጁንታ ቡድን ሀገርንና ወገንን በመካድ እያደረሰ ያለውን እኩይ ተግባሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥርዓት ለማስያዝ ብሎም የሀገሪቱን የመከላከያ ሠራዊት የትግል ስልት ለመደገፍ ታሳቢ በማድረግ ድጋፍ መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ በውይይቱ ተናግረዋል።
ሕወሓት ባለፉት 27 አመታት ሀገሪቱን የመራበት መንገድ ሀገሪቱ ዛሬ ላለችበት ችግር ዋነኛ መንስኤ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ የሕዋሃት ጁንታ ቡድን የፈጸመው የሀገር ክህደት ይቅር የማይባል ተግባር መሆኑና መንግስት እየወሰደ ያለው ሀገርን የመታደግ እርምጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የፈፀመውን ጸያፍ ተግባር ማስቆም የሚቻለው የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ብቻ እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህም ግቡን እስኪመታ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከሠራዊቱ ጎን እንዲቆም ፕ/ር ታከለ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የዩንቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዬች ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሙላቱ ዴአ በበኩላቸው መንግስት ሀገርንና ትውልድን ለመታደግ ተገዶ የገባበት ጦርነት በመሆኑ እንደ ተቋም የጀመርነውን አስፈላጊውን ድጋፍ የማሰባሰብ ለሰራዊቱ የማድረስ ተግባራችን ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከህዝብ በወጡ እንቁ ልጆች የተገነባ የሀገር መከታ የሆነ ባለ ሙሉ ክብር ተቋም በመሆኑ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግን የማስከበር ስራ አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል ሲሉም የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መስፍን ቢቢሶ ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገር ጠባቂ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት አለብን ሲሉም በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብርሃም ቦሻ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለውን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እና መንግስት የጁንታው ቡድን አባላትን ለሕግ ለማቅረብ እየሰራ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ለቀጥል ይገባል ሲሉም በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ተክሌ ሌዛ ተናግረዋል።
በቀጣይም የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት በዓይነት ለመደገፍ፣ በደም ልገሳ መርሃ ግብር ደም ለማሰባሰብ ብሎም የተቋሙን አጠቃላይ ሰራተኞች በማስተባበር ከሚያገኙት ወርሃዊ ደመወዝ መዋጮ ለማሰባሰብ እቅድ መያዙን በውይይቱ ተገልጿል።
የመከላከያ ሠራዊቱ እየተዋጋ የሚገኘው ከጨካኙ ጥቂት የሕወሓት ቡድን ጋር በመሆኑ፤ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግን የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ ሊያስቀጥል እንደሚገባ የማኔጅመንቱ አባላት ጠቁመዋል ሲል የዩኒቨርስቲ ኮሙኒኬሽን ዳይረክቶሬት ዘግቧል።
