

በህዝብ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች “የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጡትን መግለጫ ብቻ” ከመዘገብ እንድትቆጠቡ በጥብቅ ስለማሳሰብ ይሆናል።
የዎላይታ ህዝብ ለዘመናት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለትካዊ ነፃነትና ተጠቃሚነት ለማግኘት ሌሎች ህዝቦችን ሳይገፋ በአንድነት፣ በአብሮነት እና ከሁሉም ህዝቦች ጋር በጋራ የመኖር እሴት የገነባ ህዝብ መሆኑን ከታሪክ ብቻ ሳይሆን አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ በደምብ መገንዘብ ይቻላል።
የዎላይታ ህዝብ በተላያዩ ጊዜያት በአደረጃጀት ምክንያት ያጣቸውን ህገመንግስታዊ መብት ለማገኘት ሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ተከትሎ በግልጽ በተለያዩ መንገዶች ብርቱ ትግል ሲያደርግ ቆይተዋል።
በተለይም የዎላይታ ህዝብ የራሱን ሉአላዊ ሀገር ካጣ በኃላ በተደራጀ ሁኔታ በተለይም በደቡብ ክልል አደረጃጀት ውስጥ ከገባ ወዲህ ያጣቸውን የፓለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችንና ነፃነቱን ለማግኘት በህገመንግስቱ መሠረት “በክልል መደራጀት አለብን” የሚለውን ህጉንና ሥራዓቱን ተከትሎ በየደረጃው ለሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ህዝቡ በወከሏቸው ተወካዮች በኩል ግልፅ ህገመንግስታዊ መብት ጥያቄ ተጠይቆ በክልሉ መፍትሔ የሚሰጥ አካል በማጣት የህዝብ ድምፅ እንዲከበር ጥያቄው ወደ ፌደሬሽን ምክርቤት በቅሬታ መልክ መቅረቡ ይታወሳል።
የሕዝበ ውሳነው ሂደቱ ሆነ የሕዝበ ውሳኔ ተግባር በርካቶች በአጽንኦት የሚቃወምና ዕውቅና የማይሰጥ፣ የህዝቡን የመልማትና ፍትሐዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ያላረጋገጠ በአንድ ፓርቲ ጠቅላይ ገዥነት አካሄድና ፍላጎት በመሆኑ በዞኑ የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የመብት ተሟጋቾች እንዲሁም ህብረተሰቡ የእኛ ፍላጎት ያልተካሄደበት ምርጫ ብለው በግልጽ እየተቃወሙ እየተደረገ በመሆኑ ተፈፃሚ ለማድረግ በሚሞከርበት ጊዜ አከባቢውን ያልተፈለገ መስዋዕትነት እንዳያስከፍል በህዝብ ግብር የሚተዳደሩ ሚዲያዎች በገለልተኝነት ሙያዊ ግዴታ እንድትወጡ የዎላይታ ታይምስ እንደ አንድ የህዝቡን ፍላጎት በቅርበት እንደሚከታተል፣ የሚያውቅና ያለውን ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ እንደሚረዳ ሚዲያ አጥብቀን እንጠይቃለን።
ነገር ግን ከዚህ ውጪ የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግስት ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አጥንቶ ያቀረበው 55/1 አደረጃጀት ጥናት ውጤት የህዝብ ህገመንግስታዊ መብት ጥያቄ የሚጋፋ በመሆኑ በወቅቱ የዎላይታ ተወካዮቹ አንቀበልም በማለታቸው የጥናቱ ውጤት ተፈፃሚነት ውድቅ መደረጉም ይታወሳል።
ያንን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ጉዳዩ በሌላ አቅጣጫ መፈትሔ ማግኘት አለበት በሚል የሰላም አምባሳደር ኮሚቴ ተዋቅሮ የህዝቡ ትክክለኛ ፍላጎት ጥናት ተደርጎ ምክረ ሀሳብ እንዲቀርብ በተደረገው መሠረት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ምክረ ሀሳብ መቅረቡም እንዲሁ ይታወሳል።
በወቅቱ ምክረ ሀሳቡ በሚቀርብበት መድረክ ላይ የተገኙ የዎላይታ ህዝብ ተወካዮች በኮሚቴው የቀረበው ምክረ ሃሳብ በመነሻ የተቀመጡ መርሆችን ያልጠበቀ፣ ወጥነት የጎደለውና የሕዝቦችን አብሮነት ያላገናዘበ በመሆኑ መቃወማቸውም ይታወሳል።
በቀን 02/10/2012 ዓ ም በጠ/ሚ/ጽ/ቤት በደቡብ ክልል አዲስ አደረጃጀት ዙሪያ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተዋቀረው ኮሚቴ የመጨረሻ ምክረ ሀሳብ የክልል ርዕሰ መስተዳድር፣ የዞን እና የልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የድርጅት ሀላፊዎች እና የፌዴረሽን ም/ቤት አባላት በተገኙበት ለውይይት አቅርበው ነበር።
የቀረበዉ ምክረ ሀሳብ ከዝህ ቀደም ከቀረበው ጋር ተመሳሳይ የሆነ በመሆኑ መርህን ያልጠበቀ፣ ወጥነት የጎደለውና የሕዝቡን ነፃነትም ሆነ የሕዝቡን አንድነት በሙላት ያልመለሰ እና ከዝህ ቀደም ከሕዝቡ ጋር ከተማከርነውና ከህዝብ ፍላጎት የተለየ በመሆኑ ውጤቱን በወቅቱ የነበሩ የህዝብ ተወካዮች አለመቀበሉ ይታወሳል።
በወቅቱ የዎላይታ ተወካዮች በመድረኩ ሰፊ ዕድል በማግኘት በአስተያየታቸውም የህዝባቸውን ውክልና በሚገባ በማስረዳት የዎላይታ ህዝብ ጥያቄ ህገመንግስታዊ መብት ጥያቄ በመሆኑ በተገቢው የህዝብን ፍላጎት በጠበቀ መልክ እንዲመለስ በግልጽ በማሳወቅ የዎላይታ ተወካዮች የዎላይታ ህዝብ ጥያቄ “በልዩነት ይታይ” የሚል ሀሳብ በግልጽ በማንሳታቸው ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሀሳቡን በመቀበል የወይይት መድረክ በቅርብ ቀናት ውስጥ ለማዘጋጀትና ለማወያየት ቃል ገብተው የነበሩ ቢሆንም ያንን ስጠይቁ የነበሩ የህዝብ ተወካዮችንና አመራሮችን ከስልጣን በማንሳትና በማሰር የክልልነት ጥያቄ የሚቃወሙ በሌላ ባለስልጣናት እንዲተካ መደረጉም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ቀጥሎም በአከባቢው የአመራሮቹ ከስልጣን መነሳትና መታሰር ተገቢ አይደለም በሚል በባዶ እጅ አደባባይ የወጡ መላው የዎላይታ ህዝብ ላይ የፈደራል ፓሊስ፣ መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የክልሉ ልዩ ኃይል በማሰማራትና ህዝቡ ዝም እንዲል ከ38 ንፁሃን ዜጎች በላይ እንዲሞቱ፣ መቶች አካላዊ ጥቃት እንዲደርሳቸው፣ ለመብት የሚታገሉ የአከባቢው ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችን፣ ነጋዴዎችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችንም ጭምር በማሰርና የተለያዩ ጫናዎች እንዲደርስ በሚደረግበት ወቅትም ሚዲያዎች ከህዝብ ይልቅ የመንግስት አመራሮች ድምፅ ብቻ ስያሰሙ ነበር።
በዚያ ልክ ሕዝቡ ያነሳውን የመብት ጥያቄ ኢ-ሕገመንግሥታዊ በሆነ አካሄድ የራሱን መብት እንዳይጎናጸፍ ተከልክሎ ሕዝቡ በብሔሩ ምክር ቤት ከቀበሌ ጀምሮ ራሴን በራሴ አስተዳድራለሁ ብለው ወስኖ ለክልል ም/ቤትም፣ ለፌድረሽን አቤቱታ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ በነበረበት ወቅት የዞን ም/ቤት የምርጫ ዘመኑን ባጠናቀቁትና ጊዜ ባለፈቸባቸው አባላት የሕዝቡን ሕገመንግሥታዊ ውሳኔ በኃይል ሽሮ በክላስተር እናደራጃለን በማለት ሕገወጥ ህዝበ ውሳኔ ለማከናወን እንቅስቃሴ በጀመሩበት በአሁኑ ወቅትም በአከባቢው ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ዝምታን በመምረጥ የመንግስት መግለጫ ብቻ በማቅረብ የህዝብ ድምፅ ታፍኖ ቀጥሏል።
በመሆኑም የዎላይታ ህዝብ በኢትዮጵያ አንድነት ጉልህ ሚና የተጫወተ እና አሁንም በኢትዮጵያ አንድነት የማይደራደር በህብረብሄራዊ ፈደራልዝም ፅኑ እምነት ያለው ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለትካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው ተወያይቶበት የጠየቀው ህገመንግስታዊ መብት ጥያቄ “የዎላይታ ክልላዊ መንግስት” እንዲሁም ተመሳሳይ ጥያቄ ያላቸውን ወደ ታች ህዝቡ ጋር ወርዳችሁ እውነትም አሁን መንግስት “ክላስተር ብሎ ያመጣው ህዝበውሳኔ ትክክል ነው ወይ” ? የሚለውን በዜና፣ በፕሮግራም እንዲሁም በምርመራ ዘገባ በገለልተኝነት በመስራት አጋርነታችሁንና ኢትዮጵያዊነትን እንድታረጋግጡ አጥብቀን እንጠይቃለን።
ከዚህ ባለፈ በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት ፍላጎት ባሻገር የህዝብ ፍላጎት ምንድነው በሚለው ዙሪያ OMN ሚዲያ፣ አዲስ ስታንዳርድ፣ ዶቼቬሌ፣ ኢትዮጵያ እንሳይደር የመሳሰሉ የግል ሚዲያዎች በተለያዩ ጊዜ ሽፋን እየሰጡ ስለመሆናቸው እናረጋግጣለን።
በቅርቡ በዞኑ የሚገኙ የህዝብ ቴለቪዥን ጣቢያ፣ ሬዲዮ ጣቢያና ፋና ዎላይታ ሶዶ ኤፍ ኤም በአመራር ጫና ውስጥ በመግባት የህዝብ ድምፅ እንዲሰማ ባለመቻሉ “የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ” ይሄን ክፍተት ለማሟላት በሚያደርገው ጥረት የተለያዩ ጫናዎች በመንግሥት አመራሮች በመድረሱ ዋና መቀመጫ የነበረውን ዎላይታ ሶዶ ያለውን ቢሮ በመዝጋት ከኢትዮጵያ ውጪ ከስደት ሀገር ለመስራት መገደዱ ይታወቃል።
የዩቱብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
https://youtube.com/@wolaitatimes