ያም ሆኖ በክልሉ ያለው ሁኔታ በሚገባው ደረጃ እየተገለፀ አለመሆኑን እና ሌላ አደጋ ማጋረጡን ምሁራን ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን የአምቦና የአርሲ ዩኒቨርስቲ መምህራን በኦሮሚያ ያለው ሁኔታ በተገቢው አሃዝ እና አውድ እየተገለፀ አይደለም ባይ ናቸው።

በክልሉ እየተደረገ ያለው ጦርነት ባህሪ እና ስፋት፣ ያስከተለው ጉዳት፣ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች እንዲሁም የጦርነቱን ጉዳት ያወሳሰበውና ድርቅ ያስከተለው ረሀብ፣ የተፈናቃዮች ሰቆቃ እና ተላላፊ በሽታ የደቀነው አደጋ በአግባቡ እየተገለጹ አይደሉም ይላሉ።

እየተንጠባጠቡም ቢሆን የሚወጡ መረጃዎችም በክልሉ ያለው ሁኔታ አስደንጋጭ መሆኑን ያመለክታሉም በይ ናቸው አስተያየት ሰጪዎቹ።

በክልሉ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ከ20ሺ በላይ ሴቶች ለፆታዊ ጥቃት መጋለጣቸው፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት በምግብ እጥረት ውስጥ መሆናቸው፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ የመጠለያ ቦታዎች ውስጥ ሚሊየኖች በጦርነት እና በድርቅ ተፈናቅለው ሰቆቃ ውስጥ መኖራቸው፣ በክልሉ በረሃብ ሰዎች እየሞቱ እና መቶ ሺዎች በተላለፊ በሽታ አደገ ውስጥ መሆናቸውን በማሳያነት ያነሳሉ።

በሌላ በኩል በክልሉ መንግስት በኦሮሚያ ጦርነቱን በህዝብ ውስጥ ያለውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ኔትወርክ በመበጣጠስ አሸንፋለሁ በሚል ንጹሃንን በስፋት ኢላማ ያደረገበት ጦርነት መሆኑንም ምሁራኑ ይገልፃሉ።

በክልሉ መንግስት የጸረ ሽምቅ ዘመቻ በሚል በተለያዩ ጊዜያት እያደረጃ የላካቸው የስርአቱ ዘቦች፣ የሚሊሺያ አደረጃጀት፣ የአማራ ክልል ታጣቂዎች፣ የኤርትራ ወታደሮች፣ የኦሮሚያ ልዩ ሀይል እና መከላከያ ሰራዊት በጦርነቱ በተለያዩ ደረጃዎች ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።

በተለያዩ የእዝ ማእዘን የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ሀይሎች በክልሉ ላለፉት አራት አመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ንጹሃንን የገደሉ ሲሆን በምእራብ ኦሮሚያ ብቻ ቢያንስ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አፈናቅለዋል ይላሉ ምሁራኑ።

በክልሉ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በአደባባይ ሰዎች በእሳት ጭምር ተቃጥለዋል ቀሪዎቹም ተገድለዋል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በረሀብ ጭምር ሰዎች የሞቱበት ክልል መሆኑንም ይገልፃሉ።

በክልሉ የደረሰው ጉዳት በአግባቡ መዝግቦ ይፋ ያደረገ አንድም መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አለመኖሩ በክልሉ ያለው ችግር መጠኑ እንዳይታወቅ እንዳደረገው ምሁራኑ ይናገራሉ።

ጦርነቱ ቢቆም እንኳ የተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስ ለአመታት የህዝቡን ህልውና የሚፈታተን ይሆናል ባይ ናቸው ምሁራኑ።

በክልሉ የችግሩ መጠን በሚገባ አለመታወቁ ደግሞ በቀጣይ ችግሩ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቆጣጠር ተገቢ አቅም እና እቅድ ለመፍጠር በቂ መነሻ እንዳይኖር ያደርጋል ይላሉ።

አለማቀፉ ማሕበረሰብም በኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በአግባቡ አለመረዳቱ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዳይመጣ ምክንያት ይሆናልም ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች።

በክልሉ የተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስ እንደጦር መሳሪያ የመጠቀም አዝማሚያ በመኖሩም ይህንንም መመርመር እንደሚገባ ገልጸዋል።

አሁን ላይ በክልሉ ተፈናቅለው የሚገኙ ነዋሪዎች ሰላም ሳይሰፍን ወደ ግጭት ቀጠናዎች ለመመለስ እየተሞከረ መሆኑን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎች ይህም ለዜጎች ህይወት መንግስት ግድ እንደማይሰጠው ያመለክታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን ቀውስ በሙሉ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ማያያዙ ብቻ ተገቢ አለመሆኑን በአጽንኦት ገልፀዋል።

የአገሪቱን ውስብስብ ችግር ሁሉን አካታች በመሆነ መልኩ በማየት የመፍትሄው አካል መሆን እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል ስል OMN ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *