የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር “ወደ ክልል የማካተት” ህዝበ ውሳኔ ዘገባን ውድቅ አደረገ

የድሬዳዋ አስተዳደር በኢፌዲሪ 6ኛ ህዝብ ተወካዮች እና የፌዲሬሽን ምክር ቤቶች 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር “ህዝበ ውሳኔ ተደርጎ ወደ አንዱ ክልል እንዲጠቃለል ማድረግ ነው” በሚል በአንድ የምክር ቤት አባል የተነሳውን ሃሳብ እና የሚዲያ ዘገባ አስተባብሏል፡፡

የድሬዳዋ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በማህበራዊ ሚዲያ ገፁ እንዳስተላለፈው “ሃሳቡን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም የሚናፈሰውን ጉዳይ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር ትኩረት ሰጥቶ ተመልክቶታል” ብሏል።

“ህዝበ ውሳኔ ተደርጎ ወደ አንዱ ክልል እንዲጠቃለል ማድረግ ነው” የሚለው ሃሳብ ውይይት ያልተደረገበትና የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር አቋም አለመሆኑን ነዋሪው እና የአስተዳደሩ የልማት አጋሮቻችን እንድያውቁልን እንሻለንም ብሏል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በአዋጅ ቁጥር 416/1996 ዓ.ም በወጣው ቻርተር እየተዳደረ እንደሚገኝ የጠቆመው መግለጫው ቻርተሩ ለአስተዳደሩ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ የነበረው ቢሆንም በተጓዳኝ በአዋጅ የተደገፈው ቻርተር ችግሮች ስለነበሩበት አስተዳደራችን እንደተፈለገው ማደግና መበልጸግ ተስኖት ቆይቷል ብሏል፡፡

ቻርተሩ የፈጠረውን ተግዳሮት ለማስተካከል አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑንም መግለጫው ጠቁሞ የድሬዳዋን መፃዒ ብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና አለዉ ያለውን የቻርተር ማሻሻያ ረቂቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኣቅርቦ እንዲፀድቅ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *