በዛሬው ዕለት ከፌደራል የመጡ አመራሮች ከዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ጋር ምክክር እያደረጉ መሆኑ ተነግሯል።

አጠቃላይ የዎላይታ ዞን አመራሮች ከትላንትናው ዕለት ጀምሮ ከፌደራል በምስጢር መጥተው ከዞን አስተባባሪዎች ጋር ምክክር እያደረጉ ከዋሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በዞኑ ብልፅግና ፅ/ቤት ስብሰባ አዳራሽ ላይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እያወያዩ መሆኑን ከስፍራው ለ#WT ሚዲያ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

እንደምንጮቹ ገለፃ ከፌደራል ከመጡ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በሶዶ ከተማ እየተደረገ የሚገኘው ይህ ምክክር በዋናነት “በዞኑ የተፈጠረው ፓለቲካ ቀውስ ምክንያት የሆኑ ምክንያቶችና አመራሮች ላይ ያተኮረ እንዲሁም ቀጣይ በዞኑ ከሚሾሙ አዲስ አመራሮች ምን ይጠበቃል” በሚለው አቅጣጫ ላይ ትኩረት አድርጓል።

የዎላይታ ዞን አስቸኳይ ምክርቤት በነገው ዕለት በሚያካሂደው ስብሰባ በህዝበ ውሳኔ ምርጫ ማጭበርበር የተሳተፉ ሁሉም የዞኑ አስተባባሪ አመራሮች ከስልጣን በማስነሳት በአዲስ አመራሮች መተካት እንደሚጠበቅ ለWT ሚዲያ አፈትልኮ በደረሰው መረጃ ከሰዓታት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።

የWT ሚዲያ ምንጮች እንደገለፁት በነገው ዕለት በሚካሄደው የዎላይታ ዞን አስቸኳይ ምክርቤት ስብሰባ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ጨምሮ አምስት የፊት አስተባባሪዎች ከኃላፊነታቸው የሚነሱ ስሆኑ እርምጃው እስከ ወረዳ ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆንም መረጃውን አጋርተን ነበር።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለመመሰረት በቅርቡ በተካሄደው “ህዝበ ውሳኔ” በዎላይታ ዞን ህብረተሰቡ “የእኛ ፍላጎት በምርጫው አልተካተተም” በሚል ህዝባዊ እምቢተኝነት በማሳየቱ የአከባቢው አመራሮች በህገወጥ መንገድ የምርጫ ሂደቱን ማጭበርበራቸው በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተረጋግጦ ውጤቱ መሰረዙ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ “ጥሰቶቹን ያስፈጸሙ፣ የፈጸሙ እና የተባበሩ” ያላቸውን አካላት በመለየት ምርመራ እንዲያከናውን እና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት እንዲያደርግ ለፌደራል ፖሊስ ደብዳቤ እንዲጻፍ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል። በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *