
ከህዝበ ውሳኔ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በዎላይታ ዞን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና ተሳታፊ አካላት በህግ ቁጥጥር ስር የማዋል ዘመቻ ተጀመረ።
ከምርጫ ማጭበርበር ጋርና በሌሎች ጉዳዮች ተጠርጥረው የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ የህግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የመንግስት ጥበቃ መነሳቱንም የመረጃ ምንጮች ማምሻውን ለWT አረጋግጧል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለመመሰረት በቅርቡ በተካሄደው “ህዝበ ውሳኔ” በዎላይታ ዞን ህብረተሰቡ የእኛ ፍላጎት በምርጫው አልተካተተም በሚል ህዝባዊ እምቢተኝነት በማሳየቱ የአከባቢው አመራሮች በህገወጥ መንገድ የምርጫ ሂደቱን ማጭበርበራቸው በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተረጋግጦ ውጤቱ መሰረዙ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ “ጥሰቶቹን ያስፈጸሙ፣ የፈጸሙ እና የተባበሩ” ያላቸውን አካላት በመለየት ምርመራ እንዲያከናውን እና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት እንዲያደርግ ለፌደራል ፖሊስ ደብዳቤ እንዲጻፍ ውሳኔ ማሳለፉም ይታወቃል።
ወሳኔውን ተከትሎ በዛሬው ዕለት ከፌደራል የተወጣጡ የአቃቤ ህግ፣ ፓሊስ እንዲሁም የደህንነት አካላት ከህዝበ ውሳኔ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በዎላይታ ዞን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና ተሳታፊ አካላትን የህግ ተጠያቂነት ለማስፈን የማሳር ዘመቻ መጀመራቸውን ከስፍራው ማምሻውን ለWT ሚዲያ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
በዛሬው ዕለት በቦዲቲ ከተማ አስተዳደር የጀመረው እርምጃው እስከ ሁሉም ወረዳ ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን እንዲሁም በሂደቱ የተሳተፉ ከፍተኛ የዞን፣ የክልል እና የፈደራል ባለስልጣናት ድረስ እንደሚሆን ተገልጿል።