የአለምአቀፍ የዎላይታ ተወላጆችና አጋሮቹ ጥምረት የዎላይታ ህዝብ ህገመንግስታዊ በክልል የመደራጀት መብት እንዲከበርና ምርጫውን ያጭበረበሩ አካላት በህግ እንዲጠየቁ አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በዎላይታ ዞን የተካሄደውን የህዝበ ውሳኔ ምርጫ ውጤት በተፈጠረው “መጠነ ሰፊ” ጥሰቶች ምክንያት ውድቅ አድርጎ በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል።

ቦርዱ “ጥሰቶቹን ያስፈጸሙ፣ የፈጸሙ እና የተባበሩ” ያላቸውን አካላት በመለየት ምርመራ እንዲያከናውን እና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት እንዲያደርግ ለፌደራል ፖሊስ ደብዳቤ እንዲጻፍ ያሳለፈው ውሳኔ በአስቸኳይ በተገቢው ተፈፃሚ እንዲሆንና የህግ የበላይነት እንዲከበር የአለምአቀፍ የዎላይታ ተወላጆችና አጋሮቹ ጥምረት ጠይቋል።

“እኛ በመላው ዓለም የምንገኝ የዎላይታ ማህበረሰብ አባላት በወቅታዊና አሳሳቢው የማህበረሰባችን ጉዳይ ላይ ባደረግነው ጥልቅ ግምገማ የዎላይታ ህዝብ አሁን የሚገኝበት ዝርዝር ሁኔታ እጅግ አደገኛና ከመቸውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ ደረጃ በመሆኑ በሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ የመፍትሔ እርምጃዎች ተወስዶ የህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ” ስሉ ጠይቋል።

“የዎላይታ ህዝብ በህገ መንግስቱ መሰረት በራሱ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ተከትሎ በተደረገው ህዝበውሳኔም ቢሆን ካርድ ባለመውሰድና ባለመሳተፍ ባሳየው ህዝባዊ እምቢተኝነት ራሱን በራሱ በክልል የማስተዳደር ውሳኔ በመታፈኑና ባለመጠናቀቁ ህዝቡ የመልማት ጊዜውን በመዋቅር ጥያቄ ብቻ እያደረገ በመሆኑ መንግስት ገንዘብ ሳያባክን በፖለቲካ አቅጣጫ በአስቸኳይ የህዝቡን ውሳኔ እንዲያከብርና እንዲያስከብር እናሳስባለን” ስሉ ጥሪ አቅርቧል።

“መንግስት ህዝቡ በፍጹም ሰላማዊ መንገድ የሚያካሂደውን ትግል ማበርታታት ሲገባው በተለያዩ መንገዶች ለማፈን የሚያደርገውን ማንኛውንም አካሄድ እያወገዝን፥ የዎላይታ ህዝብ ወደ ቀድሞ ክብሩ እንዲመለስና የህዝብ እኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መዋቅር እውን እንዲሆን የሚያደርጉትን ወሳኝ ትግል እንድታግዙ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ስሉ ጥሪ አቅርቧል።

ከዚህ በፊት የዎላይታን ህዝብ የሚወክል ህጋዊ የዎላይታ ዞን ምክር ቤት የወሰናቸው ውሳኔዎች በሙሉ ሳይሸራረፉ ተግባራዊ እንዲሆንና ለህዝብ የሚወግኑ የመብት ተሟጓቾችን፣ አመራሮችን ከየመዋቅሩ የማሳደድና ህዝብ ባላመነበት ለመተካት የሚደረገው ሩጫ ቆሞ የዎላይታ ህዝብ ህገመንግስታዊ መብት ጥያቄ የሆነው “የዎላይታ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት” በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥበት አጥብቆ ጠይቋል።

በተቃራኒው መንግስት ለህዝቡ በክልል የመደራጅት መብት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት ሲገባው የህዝቡን ራሱን በራሱ የማስተዳደር የማይገረሰስ መብት ለመቀልበስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የማያቆም ከሆነ መላውን ህዝብ ያሳተፈ ተከታታይ ጠንካራ የትግል ጥሪዎች የሚደረጉ መሆናቸው ታውቆ ህዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ በተጠንቀቅ እንዲሆን በአባላቱ በአጽንኦት ተነስቶ ከመግባባት ተደርሷል።

የዎላይታ ህዝብ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ የራሱን ጉዳይ በራሱ ለመወሰን የሚያደርገው ትግል ከኢትዮጵያ አንድነት ጋር የማይጣረስ በመሆኑ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ከዎላይታ ህዝብ ጎን እንዲትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ስሉም በአፅንኦት ጠይቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: