በክርስትና እምነት ተከታዮች ከትንሳኤ ዕለት የምትቀድመዋን ዕለተ አርብ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት ቀን በማለት በየዓመቱ ያስቧታል።

ይህች ዕለትም ከብዙ እንግልት እና ስቃይ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ ከተዘፈቀበት ሃጥያት ለማንጻት ሲል በመስቀል ላይ የከፈለው የመስዋዕትነት የሚዘከርባት ናት።

የእምነቱ ተከታዮችም ዕለቱን ኢየሱስ ለሰው ልጆች ፍቅር ሲል ራሱን አሳልፎ የሰጠበት ነው ብለው ያምናሉ።

ኢየሱስ በወቅቱ የተቀበለው ስቃይ እና ሞት እጅግ አሰቃቂ ቢሆንም፣ በዕለተ እሁድ ሞትን ድል አድርጎ በመነሳት ትንሳኤው ተበስሯል።


በመስቀል ተቸንክሮ የሞተው ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ ድርሳናት ዘንድ ከፍ ያለ ስፍራ ቢሰጠውም፣ ይህ አሰቃቂ ሞት ግን ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ተፈጻሚ ሲሆን ቆይቷል።

ኢየሱስ ከመወለዱ ከምዕተ ዓመታት በፊት በተጀመረው የስቅላት ቅጣት በርካታ የዓለማችን ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

“በጥንት ጊዜ አንድን ሰው ለመግደል ይፈጽሟቸው ከነበሩ ሦስት አሰቃቂ መንገዶች መካከል ስቅለት እጅግ የከፋው እንደሆነ ይታሰብ ነበር” ሲሉ በደቡብ አፍሪካ የፍሪ ስቴት ዩኒቨርስቱ የጥንታዊ ባህል ደራሲ እና ተመራማሪ ሉዊዝ ሲሊየር ያስረዳሉ።

ሌሎቹ የግድያ መንገዶች ደግሞ “ሰውን በሕይወት እያለ ማቃጠል እና አንገትን መቅላት” ይገኙበታል።

በዘመኑ “በሕዝብ ውስጥ በተቻለ መጠን ከፍተኛ ሽብር ለመፍጠር ፍጹማዊ ጭካኔ በተላበሰ መልኩ ሰዎችን መግደል የተለመደ ነበር” የሚሉት ደግሞ በስፔን በሚገኘው የናቫራ ዩኒቨርስቲ የሥነ መለኮት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዲዬጎ ፔሬዝ ጎንዳር ናቸው።

በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞት ቅጣት የሚፈጸምበት ሰው ወዲያውኑ ሕይወቱ አያልፍም። ማንኛውም አላፊ አግዳሚ እንዲያየውም በአደባባዮች ላይ የሚፈጸም ሲሆን፣ ሕይወቱም የሚያልፈው ከቀናት በኋላ ነው።

በቀናት ውስጥም የተሰቀሉ ሰዎች የመታፈን፣ የደም መፍሰስ፣ የድርቀት እንዲሁም የተለያዩ የሰውነታቸው ክፍሎች ሥራቸውን ያቆማሉ።

ለመሆኑ ይህ ሰውን በመስቀል ላይ በመስቀል የሚፈጸመው የሞት ቅጣት መቼ እና የት ተጀመረ?

ክርስቶስ ከመወለዱ 500 ዓመት በፊት
በአሁኑ ወቅት መካከለኛው ምሥራቅ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይኖሩ የነበሩ እና የሁለት ታላላቅ ስልጣኔዎች ባለቤት የሆኑት አሶራውያን እንዲሁም በባቢሎናውያን ዘመን በመስቀል ላይ የሚፈጸም የሞት ቅጣት እንደተጀመረ ዶክተር ሲሊዮር ያምናሉ።

በተጨማሪም በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በፋርሶች ዘንድም ስልታዊ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ይሆን እንደነበር ይነገራል።

ዶክተር ፔሬዝ እንደሚሉት ይህንን የሞት ቅጣት መንገድ በተመለከተ እጅግ ጥንታዊ መረጃዎች የተሰበሰቡት በአሶራውያን ቤተ መንግሥት ማስጌጫዎች ላይ ነው።

“በቤተ መንግሥት ግድግዳዎች ላይ የጦርነት ድሎች እና የጦር ምርኮኞች እንዲሁም ምርኮኞቹ የተገደሉበትን መንገድ የሚያመለክቱ ሥዕሎች ነበሩ። እነዚህ የአገዳደል ዘዴዎች በመስቀል ላይ ከሚፈጸም ስቅላት ጋር ተመሳሳይም ሆነው ተገኝተዋል” ብለዋል።

ዶክር ሲሊየር ስለ ስቅለት ታሪካዊ አመጣጥ እና ምንነት የሚዘረዝር አንድ ጽሁፍ በደቡብ አፍሪካ ሜዲካል ጆርናል ላይ በአውሮፓውያኑ 2003 አሳትመዋል።

ፋርሳውያን ከመደበኛ መስቀል ይልቅ ሰዎችን በዛፎች ወይም በቆሙ ዘንጎች ላይ ይሰቅሉ እንደነበር ያስረዳሉ።

“የሞት ቅጣት የተፈረደበትን ሰው መሳቂያ፣ መዘባበቻ ማድረግ እንዲሁም ጭካኔያዊ አሟሟቶችን ማጣመር የተለመደ ነበር። ከዘዴዎቹ መካከልም አንዱ በዛፍ ላይ በመስቀል በመታፈን እና በድካም እንዲሞቱ ማድረግ ነው” ብለዋል ፕሮፌሰል ፔሬዝ።

የስቅለት መስፋፋት

በአራተኛው ክፍለ ዘመን ታላቁ እስክንድር የስቅላት ቅጣትን ወደ ምሥራቅ ሜዲትራንያን አገሮች አመጣ።

“ታላቁ እስክንድር እና ወታደሮቹ የጢሮስን (የአሁኗ ሊባኖስ) ከተማን ከበቧት። ወደ ከተማዋ ማዕከል ለመግባትም ተቸግረው ነበር” ይላሉ ዶክተሯ።

“በመጨረሻም ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ 2 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎችን ሰቀሉ።”

የታላቁ እስክንድር ተተኪዎችም የስቅላት ቅጣትን ለግብፅ፣ ለሶሪያ እንዲሁም በፊንቄያውያን ለተመሠረተችው ታላቋ የሰሜን አፍሪካ ከተማ ካርቴጅ (የአሁኗ ቱኒዝ) አስተዋወቁ።

ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ264 አስከ 146 ዓመተ ዓለም በተካሄዱ የፑኒክ ጦርነቶች ሮማውያን ዘዴውን የተማሩ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላም “ለ500 ዓመታት በማሻሻል በውጤታማ መንገድ ተጠቅመውበታል” ይላሉ ተመራማሪዋ።

“የሮማውያን ጭፍሮች በየሄዱበት አካባባቢ ሰዎችን መስቀልን ይለማመዱ ነበር” ይላሉ።

የስቅለት የሞት ቅጣት ተግባራዊ ባደረጉባቸው አንዳንድ ቦታዎች ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎችም ድርጊቱን ተቀብለው ተፈጻሚ ማድረግ ጀመሩ።

በዘጠነኛው ዓመተ ዓለም የጀርመኑ ጀኔራል አርሚየስ ቴውበርግ፣ ፎረስት በተሰኘው ጦርነት ሮማውያንን ድል ከነሳ በኋላ የሮማ ወታደሮች እንዲሰቀሉ አዘዘ። ይህም ለሮማውያን በጀርመን ጎሳዎች አሳፋሪ ሽንፈትን ያሳየ ነበር።

በ60 ዓመተ ዓለም አይሰኒ በመባል የሚታወቀው የጥንታዊ ብሪታንያ ጎሳ ንግሥት ቡዲካ በወራሪ ሮማውያን ላይ አመጽ በማስነሳት በርካታ የሮማ ጭፍሮችን ሰቀለች።

ቅድስት አገር

በጥንታዊቷ እስራኤል፣ ሮማውያን ከመምጣታቸው በፊትም ቢሆን ሰዎች በስቅላት ይቀጡ ነበር።

“ሮማውያን ቅድስት አገርን ከመውረራቸው በፊት የስቅላት ቅጣት ተፈጻሚ ስለመሆኑ የሚናገሩ ምንጮች አሉን” ይላሉ ፕሮፌሰር ፔሬዝ።

ከመካከላቸው አንዱ ሮማዊ-አይሁዳዊ የታሪክ ምሁር፣ ፖለቲከኛ እና ወታደር የነበረው ፍላቪየስ ጆሴፈስ ሲሆን፣ በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢየሩሳሌም ውስጥ ነበር የተወለደው።

ለ27 ዓመታት፣ ከ125-76 ዓመተ ዓለም አይሁዶችን ስለገዛው አሌክሳንደር ያኔየስ ዘመን ፍላቪየስ በጻፈው ዘገባ በ88 ዓመተ ዓለም አካባቢ የጅምላ ስቅለቶች ይፈጸሙ እንደነበር ጠቅሷል።

“ንጉሡ ከዕቁባቶቹ ጋር በአንድ ስፍራ እየተዝናና እያለ 800 የሚሆኑ አይሁዶች እንዲሰቀሉ፣ እንዲሁም በአደባባይ ልጆቻቸው እና ሚስቶቻቸው እንዲገደሉ አዘዘ” ሲል ፍላቪየስ ጆሴፈስ ጽፏል።

ሮማውያን

ሮማውያን በዚህ ወቅት የተለያዩ መስቀሎችን ይጠቀሙ እንደነበር የሚገልጹት ዶክተር ሲሊየር፣ የኤክስ ቅርጽ ያለው ነበር ይላሉ።

“ይሁን እንጂ በአብዛኛዎቹ አጋጣሚዎች ታዋቂውን የላቲን መስል ወይም ታው የተሰኘው እና ‘ተ’ ፊደልን የሚመስለውን ይጠቀሙ ነበር። እነዚህ መስቀሎች ከፍ ብለው የሚሰቀሉ ቢሆንም፣ መሬት ላይ የተጋደሙ መስቀሎችም የተለመዱ ነበሩ” ይላሉ።

የስቅላት ሞት የታዘዘበት ሰው ልክ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው የመስቀሉን አግዳሚ እንጨት ተሸክሞ ወደ መሰቀያው ስፍራ እንዲወስድ ይገደዳል።

“የሚሰቀሉት ግለሰቦች እርቃናቸውን ካልሆኑ ልብሳቸው ይገፈፍና በጀርባቸው ተኝተው እጃቸው እንዲቸነከር ይደረጋል።”

በደም የተጨማለቁ ሰውነቶች

እጆቻቸው በመስቀሉ አናት ላይ እንዲታሰር ይደረግና ከመዳፋቸው በታች በሚገኘው አንጓ ሚስማር እንዲቸነከር ይደረጋል።

ሚስማር በመዳፍ ላይ አይቸነከርም ምክንያቱም ሚስማሮቹ የሚሰቀለውን ሰው ሥጋ በጣጥሰው ማለፍ ስለሚችሉ እና መዳፍ የአብዛኛውን ሰውነት ክብደት መሸከም ስለማይችል ነው። ስለዚህም ሚስማሩ በእጅ አንጓ ላይ ወይም አጥንት ላይ እንዲያርፍ ይደረጋል።

ሚስማሮቹ ርዝመታቸው 18 ሴንቲ ሜትር እንዲሁም ውፍረታቸው 1 ሴንቲሜትር ሊደርስ ይችላል።

የሚሰቀለው ሰው እግሮቹም እንዲሁ ተጠፍረው ይታሰሩና በመደራረብ ከእግሮቹ ከፍ ብሎ በሚገኘው አጥንት ላይ ሚስማሩ እንዲቸነከር ይደረጋል። ጉልበትም ትንሽ አጠፍ ይላሉ።

ይህ ሁሉ ሲሆን የሚሰቀለው ሰው ላይ የሚፈጠረው ህመም በቃላት ለመግለጽ የማይቻል አሰቃቂ ነው።

“በዚህ ሂደት በርካታ ነርቮች ይጎዳሉ” ይላሉ ፕሮፌሰር ፔሬዝ።

ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ ደም ይፈሳል፣ መተንፈስም ስለሚያስቸግር በመታፈን የሚሞቱት በርካቶች ናቸው።

በርካታ የሰውነት የአካል ክፍሎችም መሥራት የሚያቆሙ ሲሆን የተሰቀለው ሰው ተሰቃቶ ይሞታል።

የመከራ ሰዓታት፣ ቀናት

የስቅላት ጭካኔ አንዱ ማሳያ ነፍስ ከሥጋ እስክትለይ ድረስ የሚፈጀው ጊዜ ረጅም መሆኑ ነው። ምንም እንኳን አንዳንዶቹ በተሰቀሉ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ቢሞቱም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለስድስት ሰዓታት ያህል እንደተሰቃየ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል።

“በአንዳንድ ሁኔታዎች ወታደሮች ሞታቸውን ለማፋጠን የሚያደርጉት የጉልበታቸውን ቋንጃ በመምታት እግራቸውን መስበር ነው። በዚህም የተሰቀሉት ሰዎች የእግራቸውን ጡንቻ ተጠቅመው መተንፈስ ስለማይችሉ ሞታቸው ይፋጠናል” ይላሉ ፕሮፌሰር ፔሬዝ።

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የሮማ ወታደሮች ከኢየሱስ ጋር አብረው የተሰቀሉት ሁለት ወንጀሎችን እግር ሰብረዋል። ኢየሱስ አስቀድሞ ስለሞተ በእሱ ላይ ይህንን አልፈጸሙም።

“ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት በጅራፍ በተደጋጋሚ ተገርፏል። ጅራፉ የብረት ቁርጥራች እና የሾሉ አጥንቶች ያሉት ሲሆን፣ በዚህም ብዙ ደም ፈሶታል። በመገረፍ ብቻ የሞቱ ሰዎችም በታሪክ ድርሳናት ውስጥ አሉ” በማለት ፕሮፌሰሩ ያክላሉ።

በክፉ ጠላቶች ላይ የሚፈጸመው ቅጣት
በመስቀል ላይ የሚፈጸመው ስቅላት የተወገዙ፣ የተጠሉ ሰዎችን “ለማጋለጥ እና ለማዋረድ” የሚደረግ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ፔሬዝ።

“ሮማውያን ሰዎችን በስቅላት ሲቀጡ ሌሎች ያንን ወንጀል እንዳይፈጸም ለማድረግ ማስተማሪያ እንዲሆን እና ለከፉ ጠላቶችም የተዘጋጀ ሞት ነው።”

በአብዛኛው በባሪያዎች እንዲሁም በውጭ አገር ሰዎች ላይ ተፈጻሚ ሲሆን፣ በሮማ ዜጎች ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው በጣም አልፎ አልፎ ነበር።

“እንዲህ አይነቱ ቅጣት አብዛኛውን ጊዜ ከአገር ክህደት፣ ከወታደራዊ አመጽ፣ ከሽብርተኝነት እና ደም መፋሰስን ካስከተለ አንዳንድ ወንጀሎች ጋር የተያያዘ ነው።”

በዚህም ምክንያት ፕሮፌሰር ፔሬዝ ኢየሱስ መሰቀሉ በጣም ምክንያታዊ እንደሆነ ይታመናል ይላሉ።

“ነገር ግን እሱን እንደ አደጋ መመልከታቸው በጣም የሚያስደንቅ ነው።”

“ዓለም እንድትለወጥ የማይፈልጉ እሱን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን እንዲገደል የወሰኑነበት መንገድም የኢየሱስ መልዕክት እንዳይቀጥል ለማድረግ ግልጽ የሞከሩበት ቅጣት ነው” ይላሉ።

የስቅላት መቅረት

የሮም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ቆስጠንጢኖስ ስቅለትን በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንዲቀር ያደረገ ሲሆን፣ እምነቱንም ወደ ክርስትና የለወጠ የመጀመሪያው የሮማ ንጉሥ ሆኗል።

በዚህም የክርስትና እምነትን ሕጋዊ በማድረግ ባህላዊ ሃይማኖቶች ሊያደርጉት ያልቻሉትን የክርስቲያን ሮማን ንጉሣዊ ግዛትን መፍጠር ቻለ።

ይሁን እንጂ የስቅላት ቅጣት ወደ ሌሎች አገራት ተስፋፋ። በአውሮፓውያኑ 1597 ጃፓን 26 ሚስዮናውያንን የሰቀለች ሲሆን የክርስትና እምነት ተከታዮችም መሳደድ ጀመሩ።

መስቀል ለዘመናት የቀጠለ ጭካኔን የሚያስታውስ ቢሆንም፣ ለክርስቲያኖች ግን ኢየሱስ ለፍቅር ሲል መስዋዕትነትን መክፈሉን የሚያመለክት ነው። ምንጭ ቢቢሲ አማርኛ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *