የሀገር ህልውና ለማረጋገጥ በጁንታው ህወሃት ቡድን ላይ መንግስት እየወሰደ ለሚገኘው እርምጃ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ በዎላይታ ዞን የሚገኙ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
በዛሬው ዕለት በሀገራዊና በአከባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ምክክር መድረክ ከዞኑ የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች በተገኙበት በዎላይታ ጉተራ አዳራሽ ተካሂዷል።
ውይይቱ በዋናነት በወቅታዊ አገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር የተደረገ ሲሆን በመድረኩም የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የዞኑ ከፍተኛ የመንግስትና የድርጅት አመራሮች፣ ከወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣የሀይማኖት አባቶች፣የወጣት አደረጃጀቶች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
አቶ ጌታቸው መና በመድረኩ ተገኝቶ አስተያየት ከሰጡ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት መንግስት የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በጁንታው የህወሃት ቡድን ላይ እየወሰደ የሚገኘው እርምጃ መንግስት በሆደ ሰፊነት በማየቱ የዘገየ ቢሆን እንጂ ተገቢ ነው በማለት መንግስት ይሄንን ዓላማ ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት በማንኛውም መንገድ ከጎኑ በመቆም ድጋፋቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በተላይም በአሁኑ ወቅት ለሀገር ክብር ዘብ በቆመው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጁንታው የህወሓት ቡድን የወሰደው አሳፋሪ ተግባር ለሀገር ያለውን ንቀት በግልጽ ያሳየ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በመከላከያ ሰራዊት ጎን መቆም እንዳለበት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ኢያሱ ጋጃባ ተናግረዋል።
ጁንታው የህወሓት ቡድን ለእኩይ አላማ ማስፈፀሚያ በተለያዩ አከባቢዎች ያልተገባ ጥቅም በመስጠት ያሰማራቸው ሴራኞች በአካባቢያችን ሰላምና መረጋጋት ላይ ጥላሸት ቀብቶ እንዳይሄዱ ህብረተሰቡ ከወትሮው በተለየ መንገድ ከመንግሥት ጎን በመቆም መጠበቅ እንዳለበትም አስተያየት ሰጪዎቹ አክለው ተናግረዋል።
በተጨማሪም በዞኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ የፖለቲካ ልዩነቶችን በመፍታት ሁሉም ህብረተሰብ ክፍሎች ለአከባቢው ዕድገት የበኩላቸውን እንዲጫወቱ የውይይት መድረኮች ሊፈጠሩ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ብሎም በዞኑ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ሁኔታዎች ያሉበትን እና በተለይም የዎላይታ ህዝብ በህጋዊ መንገድ የጠየቀው በክልል የመደራጀት ጥያቄ ያለበትን ደረጃ ለታዳሚዎቹ በስፋት አብራርተዋል።
በጁንታው ህወሓት ቡድን የተቀናበረ ድራማ ህዝቡ ሳይታለል ለመከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ያለውን ወገንተኝነት እና ድጋፍ በማድነቅ ይሄንንም አጠናክሮ እንዲጥልም ዶክተር እንድሪያስ ጠይቀዋል።
በዞኑ ውስጥ በተከሰተው የፓለትካ ብልሽት ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስታዊ መዋቅሮችን መልሶ የማደራጀት ስራ እየተሰራ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በአከባቢው የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መስተጓጐል መኖሩን ገልጸው ቀጣይ ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱም አብራርተዋል።
አሁን በዞኑ እየተያ የሚገኘውን አንፃራዊ ሰላም ወደ ተሻለ አስተማማኝ ሁኔታ በመቀየር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ እያስተዋለ የሚገኝውን መስተጓጎል ለመቅረፍ የተለያዩ አስቻይ ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ እንደሚገኝ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ በመድረኩ ተናግረዋል።
በዞኑ ከዚህ በፊት የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር እንዲሁም ተጨማሪ የመልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ አድማሱ አክሎ ተናግረዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን መመሪያ ዘግቧል።
