
“የዎላይታ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ ህግ የተጣሰው የዜጎች መብት ብቻ ሳይሆን በፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በራሱ በምርጫ ቦርድ ጭምር ነው” ሲሉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ገለፀ።
በሌላ በኩል የዎላይት ዞን የክልልነት ጥያቄ ሕገመንግስቱን ተከትሎ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘም ያለው የዎላይታ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሊወስደው መሆኑ ተገልጿል።
ሕገመንግስቱን የጣሰ ውሳኔ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በመወሰኑ የተነሳ በዞኑ ሕዝቡ ያላመነበት ሕዝበ ውሳኔ ተደርጓል ያለው ፓርቲው በዚህም የተነሳ የአገሪቱ ገንዘብ እና ጉልበት እንዲባክን ሆናል ሲሉ የግንባሩ ሊቀመንበር ጎበዜ ጉአ ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡
የዎላይታ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ፓርቲዎች ጋር በመሆን ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ የተወሰነበትን አግባብ ወደ ፍርድ ቤት ብቻ ሳይሆን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕግ ጉዳዮች እና የሕገ መንግስት ጉዳይ አጣሪ ፍርድ ቤት ድረስ እንዲወሰድ በፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ተወስኗል፡፡
ጉዳዩን በቅርቡ ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድም ከሕግ ባለሙያዎች ጋር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፓርቲው በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወሰነውን ውሳኔ ላይ ያለውን ቅሬታ እና የይግባኝ አቤቱታ ሦስት ጊዜ በደብዳቤ ጠይቆ ምላሽ እንዳላገኘም አስታውቋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ከደቡብ ክልል የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ በድጋሚ እንዲካሄድ የወሰነውን የዎላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔን ሰኔ 12 እንደሚያካሂድ ሐሙስ ሚያዚያ 26 2015 ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ምክክር ላይ ተናግሯል።
በድጋሜ እንዲካሄድ የተወሰነውን የዎላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔን በተመለከተ በትናንትናው ዕለት በተደረገው የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ የተገኙት የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አማኑኤል ሞጊሳ ከሕግ ጥሰቱ ጋር በተያያዘ ሲናገሩ
‘’የሕግ ጥሰቱ የተጀመረው የምርጫው ምዝገባ ላይ ሳይሆን የሪፈረንደም ውሳኔው ተሸሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብን ፍላጎት ያላካተተ አማራጭ ካመጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው ብሎ ቢወስደው የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግስት አመራሮችም ለዚህ መጠየቅ አለባቸው ፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ….. የዜጎችን መብት ሊያስከበር የተቋቋመ ተቋም ይህንን በመጣሱ መጠየቅ አለበት፡፡ …… ስለዚህ ይህ ሕዝበ ውሳኔ በሕግ ሊታገድ ይገባል የሚል ሀሳብ አለኝ ‘’ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ተወካይ የሕዝበ ውሳኔው ሕግ የተጣሰው በፌዴሪሽን ምክር ቤት ነው፡፡ የዎላይታ ሕዝቦች የክልልነት ጥያቄን ሕገመንግስታዊ ነው፡፡ ስለዚህ ሕጉ የተጣሰው በዜጎች ብቻ ሳይሆን በፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በራሱ በምርጫ ቦርድ ጭምር ነው ሲሉ ተናግረዋል ስል ዋዜማ ዘግቧል፡፡