በዎላይታ ዞን ብልፅግና ፓርቲ አስተባባሪነት የድጋሚ የህዝበ ወሳኔ ለማጭበርበር የተዘጋጀ አጭር ምስጥራዊ ሰነድ ይፋ ሆነ።

ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው በዚሁ ይፋ በሆነው ምስጢራዊ ሰነድ ባለፈው ጥር 29/2015 ዓ.ም ከ500 ሚሊዮን ገንዝብ በላይ ወጪ ተደርጎበት የተካሄደው ምርጫ አመራሮች ባደረጉት ማጭበርበር ምክንያት ውድቅ መሆኑን ተከትሎ በድጋሚ ለማሳካት እስከ ቀበሌ ድረስ የዘረጉትን አሰራር ይተነትናል።

ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ቀጣይ በምርጫው ዕለት እንዴት ማጭበርበር እንደሚቻልም የተዘጋጀ ምስጢራዊ ሰነድ የደረሰውን በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ እያሳወቅን ክፍል አንድ እንደሚከተለው ቀርቧል👇

“ለድጋሚ የህዘበ ውሳኔ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት ሥራ ውስጥ በሚንገባበት ወቅት በተግባባነው ቁርጠኝነት ልክ የመራጭ ቁጥር ከፍ አድርገን ማቀዳችን የሚታወስ  ስሆን ለዚህ ደግሞ እንደ መልካም  አጋጣሚ ሊወሰድ የሚገባው ጉዳይ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያ ቁጥር በፊት ከነበረዉ ላይ 692 ጣቢያ ጨምሮ መላኩ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የጠቅላላ ምርጫ ጣቢያዎቻችን ቁጥር ወደ 1804 ከፍ ብሏል፡፡

ይህንን እንደ ዞን እናሳካለን ተብሎ የታቀደውን 2011170 መራጭ ለ1804 ጣቢያ ስናካፍል በአማካይ በአንድ ጣቢያ 1115 ሰዉ ይመዘገባል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዚህ መነሻ ለሁሉም መዋቅሮች ተጨማሪ ሆኖ የወረደውን ምርጫ ጣቢያ በማካለል (ማፕንግ በመስራት) ጣቢያዎችን በማደራጀትና መለያ ስያሜ በመስጠት እስከ ሚያዝያ 18 ድረስ መረጃው በአስቸኳይ እንዲደርስ ተጠይቆ ነበር፡፡

በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት ተግባራዊ  በማድረግ መረጃዉን የላኩ መዋቅሮች – ሁምቦ፤ ዳሞት ጋሌ፤ ኦፋ፤ ዳሞት ሶሬ፤ ዳሞት ወይዴ፤ አባላ አባያ፤ ኪንዶ ኮይሻ፤ ጠበላ ከተማ፤ ቦዲቲ ከተማ፤ ቤለ አዋሳ ከተማ ስሆኑ ቦሎሶ ሶሬና ፤ዳ/ፑላሳ በሐርድ ኮፒ ብቻ የላኩ ናቸዉ፡፡ ከቀሪ  አስራ አንድ መዋቅሮች ዛሬ እስከ 6፡30 ድረስ በሐርድና በሶፍት ኮፒ ካልደረሰ መረጃዉን በጊዜ ባለማድረስ በምርጫ ቦርድ በኩል የምንወቀስ መሆናችን ልታወቅ ይገባል፡፡ 

በዚህ ሂደት የጣቢያ ቁጥር በመጨመሩ ይህንን ያህል ጣቢያ የትና እንደት እናደራጅ በሚል ስጋትና ጥያቄ ስያነሱ የነበሩ መዋቅሮች ቢኖሩም የጣቢያው ቁጥር ተጨማሪ የላከው ምርጫ ቦርድ እንደሆነና ይህንን አደራጅቶ ወደ ተግባር ማስገባት ያለዉን ጠቀሜታ ስናስረዳ ተቀብሎ ሁሉም ወደ ሥራ መግባቱ በበጎ የሚወሰድ ይሆናል፡፡

ሌላው ግብአቶችን በቅርበት ለማድረስ ተጨማሪ ሦስት ማዕከል እንድናደራጅ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል፡፡ ለዚህም ዳ/ፑላሳ፤ቦሎሶ ቦምቤና ሶዶ ዙሪያ ወረዳዎች ማዕከል እንድደራጅ የተባለው በቀጣይ ሁለትና ሶስት ቀናት ዉስጥ አዘጋጅተዉ ሪፖርት እንድያደርጉ የሚፈለግ አድስ ተግባር ነው፡፡

ይህ ድጋሚ የሚካሄደዉ የህዝበ ዉሳኔ ቅድመ ዝግጅት ተግባር ገና ጅምር ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን አሁን ላይ በዝርዝር የሚቀርብ ሪፖርትም ይሁን በጥንካሬና በጉድለት የሚቀርብ ዝርዝር ግብረ መልስ ብዙ ባይኖርም በመጀመሪያ ዙር ከታዩ ጉድለቶች ብዙ በመማር የቀደመዉ ስህተት እንዳይደገም የምርጫ ቦርዱን ደንብና አሰራር ብቻ ተከትለን ለመስራትና የተሻለ ዉጤት ለማስመዝገብ ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በአጭሩ እንደሚከተለዉ ቀርበዋል፡፡

በዋናነት ለቀጣይ በከፍተኛ ትኩረት መሰራት ያለባቸው ተግባራት ተብሎ በምስጢራዊ ሰነድ የተዘረዘሩ ነጥቦች 👇

👉 አድስም ሆነ ነባር የተደራጁ ምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ ማካሄድና ቁሳቁስ ማስቀመጥ የሚያስችል ደህንነቱ የተጠበቀ ጽ/ቤት ወይም ቢሮ መኖሩ በአስቸኳይ ማረጋገጥ፤

👉ጣቢያዎች በቀበሌ ጽ/ቤት እና በፖሊስ ማዕከላት እንደማይደራጁ አዉቆ ከውድሁ አስፈላጊ ጥንቃቄ መወሰድ፤

👉 አድስ የሚከፈቱ ማዕከላት ለዕቃ ማስቀመጫ የሚሆን ሰፊ ክፍል ቤት (ለመጋዘንና ለቢሮ) የሚያገለግል ቤት ማመቻቸት፤

👉ነባር ማዕከላት ከዚህ በፊት ከተለያየ ቦታ የተሰበሰቡ ለሥራ የሚያስፈልጉ ግዝአቶች ማለትም ጠረጴዛ፤ ወንበር፤ ሸልፍ፤ መብራት፤ የፋይል አቃፍ እና ሌሎችም ከማዕከል ወጥተው ከሆነ ወደ ቦታው በመመለስና በማደራጀት ለሥራው ሚቹ ሁኔታ መፍጠር፤

👉 አድስ የሚከፈቱ ማዕከላትንም በዚህ ልክ ዝግጁ እንድሆኑ ማድረግ፤

👉ከዚህ ቀደም ብዙ ጥያቄ ያስነሳና ተጠያቂ ያደረገዉ ጥሰት እንዳይደገም የቀበሌ ነዋሪነት መታወቂያ ካርድ ዕድሜዉ ለደረሳቸዉ ለሁሉም ዜጎች ከወዲሁ እንድያገኙ ማድረግ፤

👉ከምርጫ ቦርድ የሚወርደዉ የጊዜ ሰሌዳ የተጣበበ ልሆን ስለምችል እንደ ከዚህ ቀደሙ መዘናጋት እንዳይኖር ለምዝገባም ይሁን ለድምፅ መስጫ ጊዜዉን በአግባቡ እንዲጠቀምና በነቂስ እንድወጣ በህዝቡ ዘንድ ቁጭት የመፍጠርና የማነሳሳት ሥራዎችን ከወድሁ መስራት፤

👉ከቅድመ ዝግጅት ሥራ ጀምሮ በምርጫዉ ሂደት አስተዳደራዊ የሆኑ ጉዳዮችን በቅርበት  የሚከታተል የሚደግፍ የሚያመቻች የመረጃና የሪፖርት ልዉዉጥ ሂደቱን የሚያሳልጥ ጠንካራ ሰዉ መወከሉን ማረጋገጥና ለተወከለዉ ሰዉ ግልፅ ኦሬንተሸን መስጠት፤

👉የምርጫን ቁሳቁስ ከማዕከል ወደ ጣቢያ የማጓጓዝ ሥራ አሁንም በመዋቅሮች ላይ ልወድቅ የሚችል ተግባሪ እንደሆነ ታሳቢ በማድረግ አስፈላጊ ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ፤

👉በአንድ ማዕከል ሥር የተካተቱ መዋቅሮች ማዕከሉን እንዲጠረንፍ ከተወከለ አመራር ጋር ጤናማና ጠንካራ ግንኙነት በማድረግ በማዕከል አስተባባሪዎች ላይ የተለየ ጫና እንዳይፈጠር መቀናጀት፤

👉አሁን የአስተዳደር ክልል አካል ሆነዉ እያሉ በምርጫ ክልል በሌላ መዋቅር የተካተቱ ምርጫ ጣቢያዎች መረጃ እንዳይዘለልም እንዳይደገምም ጥንቃቄ የታከለበት የመረጃ ልዉዉጥ ሥርዓት መከተል፤

👉በአጠቃላይ በቅድመ ምርጫ በምርጫና በድህረ ምርጫ ወቅት የሚከሰቱ አዳድስ አጋጣሚዎችና የሚወርዱ ተልዕኮዎችን ተግባሩ በሚጠይቀዉ ጥራትና ፍጥነት ምላሽ እየሰጡ መሄድ የሚያስችል ትኩረትና የዉስጥ አንድነት የሚፈልግ ተግባር ከፊት ለፊታችን ስለሚገኝ ተልዕኮን የሚመጥን ዝግጁነት ከሁላችን ይጠበቃል ስል በድጋሚ የሚካሄደውን ምርጫ በተቀናጀና በረቀቀ ሁኔታ ለማጭበርበር የሚያስረዳ ሲሆን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ቀጣይ በምርጫው ዕለት እንዴት ማጭበርበር እንደሚቻል የተዘጋጀ ምስጢራዊ ሰነድ የደረሰውን በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *