ከሳምንት በፊት ጀምሮ በማህበራዊ ሚዲያ በስማቸውና በብዕር ስማቸው በአከባቢው የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራር በተለይም ከህዝብ ፍላጎት ውጪ ተካሂዶ ከተሰረዘ በኃላ ዳግም ለማካሄድ በሚል ዝግጅት እየተደረገ ባለው ህዝበ ውሳኔ ምርጫ ዙሪያ ሀሳባቸውን የሚያጋሩ ወጣቶች ያለምንም ህገዊ መጥሪያ እስርቤት እየገቡ ስለመሆኑ ከስፍራው ለWT ሚዲያ የሚደርሱ መረጃዎች ያመለክታል።

ወጣቶቹና የመብት ተሟጋቾች የጅምላ እስራትና አፈሳ በአረካ፣ ሶዶ፣ ቦዲቲ ከተማ እንዲሁም ሌሎች መዋቅሮች ላይ የተጀመረ ሲሆን አንዳንድ የታሰሩ ግለሰቦች የሚያርፉበት እስርቤት ከመደበኛ ፓሊስ ጣቢያ ውጪ ስለመሆኑም ከአይን እማኞችና በአከባቢው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል ምንጭ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያስረዳው።

በዎላይታ ዞን የተካሄደውን የህዝበ ውሳኔ ምርጫ ውጤት “በተፈጠረው መጠነ ሰፊ” ጥሰቶች ምክንያት ውድቅ አድርጎ በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑን በርካቶች ቢያደንቁም በህዝቡ ዘንድ ያለውን እውነታ ሳይረዳ አሁንም በድጋሚ በተመሳሳይ ሰኔ 12/2015 ዓ.ም የሚደረግ ምርጫ አላስፈላጊ ጊዜና ገንዘብ የሚባክን በመሆኑ እውነተኛ የህዝብ ፍላጎት በምርጫ አማራጭ ላይ እንዲካተት ካልተደረገ መንግስትንም ህዝብንም ትልቅ መስዋዕትነት የሚያስከፍል አካሄድ ይሆናል ስሉም ሀሳባቸውን ያጋራሉ።

ከሶስት ቀናት በፊት በጉዳዩ ዙሪያ የዎላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ባወጣው መግለጫ ” በድጋሚ ቀጣይ የሚካሄድ ህዝበ ውሳኔ የዎላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሚል አማራጭ ያልተካተተ ከሆነ ፓርቲያችን ለኢህገመንግስታዊ ሪፈረንደም እውቅና የማይሰጥ መሆኑን ከወድሁ እናሳውቃለን ” ስል መግለፁ ይታወሳል።

በተመሳሳይ መንገድ የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ “የዎላይታ ዳግም ህዝበ ውሳኔ አጀንዳ ላይ በግልፅ “የዎላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት” የሚል አማራጭ እስካልቀረበ ድረስ ለህዝበ ውሳኔ ህጋዊ እውቅና እንደማንሰጥ እና ሂደቱንም ውጤቱንም እንደማንቀበል በአፅኦት አሳውቀን ወጥተናል” በሚል ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ላይ ግልጽ አቋም መግለፁን መዘገባችን ይታወቃል።

በዞኑ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በአከባቢው ሀሳቦችን በነፃነት ለመግለጽ በሚሞክሩ ግለሰቦች ላይ የሚደርሰውን ጫና እንዲሁም አጠቃላይ ሂደት በተመለከተ በየቀኑ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን የሚሰጥ ሲሆን የትኛውንም ጠቃሚ ጥቆማዎች ካሉ ማድረስ እንደሚቻል እየገለፅን ከታች ሰሞኑ ከታሰሩ ወጣቶች የተወሰኑት ፎቶ አያይዘናል። Wolaita Times

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *