ዎላይታ ውስጥ የሚስተዋለውን ሙስናና ብልሹ አሰራር ያጋለጡና የተቃወሙ፣ የሕዝቡን የመልማትና የነፃነት ጥያቄ የሚደግፉና የሚመሩ ለከፍተኛ ጥቃት መጋለጣቸውን ጋዜጠኛና ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታጁራ ላምቤቦ ገልጿል።

የዎላይታ ሕዝብ መብት እንዲከበርና የሕዝቡ ፍትሃዊ ጥቅሙ እንዲጠበቅለት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ድምፅ በመሆን የሚታወቀው ጋዜጠኛ ታጁራ ላምቤቦም ሐሳቡን በነፃነት በመግለፁ ብቻ በተለያየ ጊዜ መታሰሩንና መሰቃየቱንም አስረድቷል።

ዎላይታ ውስጥ ሐሳብን በነፃነት መግለፅ፣ የመብት ጥያቄ ማንሳት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ማጋለጥና ለህሕዝቡ ሁለንተናዊ ለውጥ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መታገል በዞኑ ከወረዳ እስከ ፈደራል በተዘረገው መንግሥት አመራሮች ሰንሰለት ምክንያት የተከለከለ፣ የሚያሳስር፣ የሚያስደበድብ፣ የሚያሰቃይና የሚያስገድል መሆኑን የገለፀው ጋዜጠኛ ታጁራ፣ ለሕይወቱ በመስጋት ከሐገር መሰደዱንም ገልጿል።

በዎላይትኛ ቋንቋ የመጀመሪያ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የሆነው ታጁራ ላምቤቦ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሚዲያው በመንግሥት አፈና እስከተዘጋበትና የሥራ አጋሮቹ በሙሉ እስከታሰሩበት ጊዜ ድረስ “Daamoota Makkisuwaa” በሚል የፕሮግራም ስያሜ በOromia Media Network ሐገሪቷንና ዎላይታን ማዕከል ያደረገ ዝግጅት ስያቀርብ መቆየቱ ይታወቃል።

እንዲሁም በUbuntu Tv ላይም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዓለም አቀፍ፣ ሐገራዊ በተለይ ዎላይታን የሚመለከቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ወቅታዊ ጉዳዮችን “ጉታራ ማክሷ፣ አዲስ አጀንዳ፣ ልዩ ዝግጅትና ዕለታዊ ዜና” በሚሉ ርዕሶች አዘጋጅቶ በማቅረብ ሕዝቡን በማንቃት፣ በማስተማር፣ በማሳወቅና ለለውጥ በማዘጋጀት ሙያዊ ኃላፊነቱን ስወጣ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ የዎላይታ ዞን የቀድሞ እና የአሁኑ አመራሮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እኩልት የማይቀበሉ ኃይሎች አበርክቶውን ወደ ጎን በመተው፣ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ ጋዜጠኛው በለለበት ስም እየጠቀሱ አንዴ “አሸባሪ” ሌላም ጊዜ “ፅንፈኛ” አለፍ ስልም “ሐገር አፍራሽ” የሚል ማሰርን፣ ማሰቃየትንና መግደልን ዓላማ ያደረገ እኩይ ዘመቻ በመክፈት ለከፍተኛ ስነልቦና ቀውስ ከማጋለጣቸው አልፈው ማሰራቸውን፣ ማሰቃየታቸውን፣ ለመግደል መሞከራቸውንና ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከተደሰደደበት ዕለት ድረስ ከሁሉም ሕዝባዊና መንግሥታዊ አገልግሎቶች ማገዳቸውንም ከጋዜጠኛው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከሚወደው ሕዝብ በስደት እንደለይ ያደረገው ስቃይና መከራ በግሉ የደሰረሰ ሳይሆን ከወረዳ እስከ ፈደራል ድረስ የተዘረጋው የዎላይታ ዞን አመራሮች መላው ዎላይታ ሕዝብ ላይ የሚፈጽሙት ግፍ አካል መሆኑንም ጠቁሟል።

የፌዴራሉ ገዢው መንግሥትና መሪው ድርጅት ብልፅግናም የዎላይታን ሕዝብ ከሐገሪቷ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች በማግለል፣ ሕዝቡን ለስልታዊ ጥቃትና ለመዋቅራዊ ጭቆና በማጋለጥ፣ የሕይወት መስዋዕት ከፍሎ በደሙና በአጥንቱ ባቆመው ሐገር ባይተዋርና የበይ ተመልካች በማድረግ፣ እንደዎላይታ በህልውናው የመቀጠል ተስፋውን አደጋ ላይ መጣሉንም ጋዜጠኛው ገልጿል።

በተለይ ሕዝቡን ደፍቆ ከያዘው መዋቅራዊ ጭቆና ለመላቀቅ፣ በክልል ለመደራጀት ሕገመንግስቱ በሚፈቅደው አካሄድ በሙሉ ድምፅ የወሰነውን የዎላይታ ሕዝብ እጅግ አውዳሚና አደገና የሆነ ከባድ የጦር መሣሪያና መከላከያ ሠራዊት በማዘዝ ከ100 በላይ ንፁሃንን ያስጨ’ፈጨፈው ገዢው መንግሥት የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ፣ ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችንና አንቂዎችን ዳግም የጥቃቱ ዒላማ ለማድረግ ያቀደበት ኢህገመንግስታዊው “ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የዎላይታን ሕዝብ ከታላቅነቱና ከከፍታው የሚያወርድ በመሆኑ ሁሉም በየአቅጣጫው ሠላማዊና ጠንካራ ትግል በማድረግ እቅዱን ማክሸፍ እንደሚገባም ታጁራ ተማፅኗል።

ለዚህም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሕግ ውግናና ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ ዳግም ለማካሄድ ያቀደውን ሕዝበ ውሳኔ መላ የዎላይታ ሕዝብ ድምፅ በሚሰጥበት ዕለት ከቤት ያለመውጣት ሕጋዊ መብቱን ተጠቅሞ ውድቅ እንዲያደርግም አሳስቧል።

በበኩሉም ከሕዝቡ ጋር የሚያደርገውን ሠላማዊና ሕጋዊ ትግል ከመቸውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።

ጋዜጠኛና ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታጁራ ላምቤቦ ከሀገር ቢሰደድም ከአምስት ወራት በፊት በተመሳሳይ መንገድ በአከባቢው ሀሳብን በነፃነት መብት አደጋ ላይ በመውደቁ በዎላይታ ሶዶ የሚገኘውን ዋና ቢሮ በመዝጋት ከሌላ ሀገር እየሰራ ከሚገኘው የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ መስራችና ባለቤት ጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ጋር በጥምረት የተለያዩ ፕሮግራሞችና ዜናዎችን በተደራጀ መንገድ ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱንም በዚሁ አጋጣሚ እንገልፃለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *