

Fake News Alert ⚠️
“ሰሞኑን በዎላይታ ተካሄደ የተባለው ፓለቲካ “ህዝበ ውሳኔ” ውጤት ተብሎ የሚሰራጨው መረጃ ውሸት ነው” ምርጫ ቦርድ
ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ሰሞኑን በዎላይታ ተካሄደ የተባለው ፓለቲካ “ህዝበ ውሳኔ” ውጤት ተብሎ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ስለመሆኑ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ገልጿል።
እስካሁን በምርጫው ዕለት ባለው እስከ ስድስት ሰዓት እንዲሁም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ያለውን ውጤት ብቻ ከመግለፁ ውጪ አጠቃላይ ውጤት በተመለከተ ሰኔ 19/2015 ዓ.ም ይፋ ለማድረግ የድምፅ ቆጠራና ምርመራ እየተካሄደ ስለመሆኑ በማስረዳት ከቦርዱ እውቅና ውጪ የሚሰራጭ የትኛውም ውጤት ተቀባይነት አለመኖሩንም ቦርዱ አስታውቋል።
ከተለያዩ ምንጮች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በዚሁ ድጋሚ የህዝበ ውሳኔ ምርጫ ከሂደቱ ጀምሮ “የህዝብ ፍላጎት ያልተካተተበት ህገወጥ” በሚል በምርጫው ላይ ያልተሳተፉት ቁጥር መምረጥ ከሚችለው 55% በላይ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል።
በሌላ በኩል የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ እና የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በድጋሚ ለተካሄደው የፓለቲካ “ሕዝበ-ውሳኔ” ውጤት ዕውቅና እንደማይሰጡና ይሄንንም ለአለምአቀፍ ተቋማት ጭምር በተለያዩ መንገዶች እየገለፁ እንደሆነ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።



ፓርቲዎቹ በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ላይ ሕዝበ-ውሳኔው “የዎላይታ ክልላዊ መንግሥት ይቋቋም” የሚል አማራጭ ባለመቅረቡ ከፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት በክስ ሂደት ላይ ስለመሆኑ በመጥቀስ ወደፊትም የዎላይታ ህዝብ የራስ መስተዳድር ጥያቄ እስኪመለስ በሰላማዊና በህጋዊ የትግል ስልት ከመቸውም ጊዜ በላይ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አስታውቋል።
በተጨማሪም በድጋሚ ለተካሄደው ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት ዕውቅና እንደማይሰጡና በግዴታ የሚወሰን ውሳኔ ህዝባዊ ቁጣ ሊያስነሳ ስለሚችል የሚመለከተው አካል በሙሉ ከፍተኛ አደጋ ሳይከሰት አስቀድሞ ለጉዳዩ የተለየ ትኩረት መስጠት እንዳለበት እየተማፀኑ ይገኛሉ።