በዎላይታ በህግ መምረጥና መሳተፍ የማይችሉ የዩንቨርስቲ፣ የኮሌጅ ተማሪዎችና የአጎራባች ዞኖች ነዋሪዎች እንዲሳተፉ የውሸት መታወቂያ እየታደለ ነው” – የአይን እማኞች

በፓለቲካ ውሳኔ በድጋሚ በዎላይታ ዞን ይካሄዳል በተባለው “ህዝበ ውሳኔ” ላይ በህግ መምረጥና መሳተፍ የማይችሉ የዩንቨርስቲ፣ የኮሌጅ ተማሪዎች እንዲሁም የአጎራባች ዞኖች ነዋሪዎች እንዲሳተፉ የውሸት መታወቂያ ተዘጋጅቶ እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።

የአከባቢው አመራሮች ምርጫውን ህዝቡ “የእኔ ፍላጎት አልተካተተም” በሚል በሂደቱ ላይ ላለመሳተፍ እምቢተኝነት በማሳየቱ መጭበርበራቸውን ተከትሎ ውጤቱ ተሰርዞ ሰኔ 12/2015 ዓ.ም በድጋሚ ለማካሄድ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ባለው ሂደት ላይ አሁንም ተመሳሳይ ህገወጥ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ስለመሆኑ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከተለያዩ ምንጮች ያገኘው መረጃ ያረጋግጣል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዛሬው ዕለት የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው በድጋሚ በዎላይታ ዞን ይካሄዳል በተባለው “ህዝበ ውሳኔ” ላይ በህግ መምረጥና መሳተፍ የማይችሉ የዎላይታ ሶዶ የዩንቨርስቲ፣ የሶዶ ግብርና ኮሌጅ ተማሪዎች እንዲሁም የአጎራባች ዞኖች ነዋሪዎች እንዲሳተፉ የውሸት ነዋሪነት መታወቂያ ተዘጋጅቶ እየተሰጠ መሆኑን ተገልጿል።

በህዝበ ውሳኔ ሂደት ላይ የአከባቢው አመራሮች በሚፈልጉት መንገድ ድምፅ እንዲሰጡ በማለም ትምህርታቸውን ለመከታተል ከተለያዩ ሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ፣ የሶዶ ግብርና ኮሌጅ ተማሪዎች የውሸት የነዋሪነት መታወቂያ በገፍ እየተሰጠ ስለመሆኑ አንድ ስሙን ያልገለፀ የአይን እማኝ ከስፍራው ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አረጋግጧል።

እንደመረጃ ምንጩ ገለፃ በህግ በህዝበ ውሳኔ መሳተፍ የማይችሉ ከሌላ አከባቢ የመጡ ተማሪዎቹ እንዴት መምረጥ እንዳለባቸው ከመካከላቸው ተመርጠው የተወከሉ ግለሰቦች አደረጃጀት አማካኝነት የግንዛቤ ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑም አስረድቷል።

በሌላ በኩል በህግ በህዝበ ውሳኔ መሳተፍ የማይችሉ እንዲሁም የአከባቢ ነዋሪ ያልሆኑ ግለሰቦች ከአጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች አመቻች ኮሚቴ በኩል ተመልምለው ከምርጫው ዕለት በፊት ወደ አከባቢው ገብተው እንዲያድሩ ለማድረግ የውሸት የነዋሪነት መታወቂያ ተዘጋጅቶ ተመሳሳይ ህገወጥ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ስለመሆኑ ተነግሯል።

ዎላይታ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም አመራሮች መደበኛ የመንግስት ስራ በማቆም ቅድመ ምዝገባ በሚል ለቤት እየገቡ በግዴታ 1ለ 10 የሚል ህቡዕ አደራጅቶ “እርግብ ምረጡ ወይንም ጎጆ ምረጡ እኛ የምንፈልገው ህዝብ ቁጥር እንዲወጣ ነው፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መመስረት በመንግሥት የተቀመጠ አቅጣጫ ነው” እያሉ ነዋሪዎቹን እያስገደዱ መሆኑም የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከተለያዩ ምንጮች ያገኘው መረጃ ያረጋግጣል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: