ሰበር መረጃ

የዳውሮ እና ኮንታ ህዝብ በአዲሱ ክልል ለመደራጀት ጥያቄ አቀረቡ

ከአንድ አመት በፊት ከነባሩ ደቡብ ክልል አዲስ ወደ አዲሱ “ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል” በሚል ቦንጋ ከተማ ማዕከል አድረጎ በተደራጀው ክልል የተቀላቀሉ ዳውሮ እና ኮንታ ዞኖች ለታሪካዊ ወቀሳ፣ ችግርና መከራ ተጋልጠናል” በሚል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታ ማስገባታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

አንድ ሂደቱን በኮሚቴ ደረጃ እየመራ የሚገኝ ምንጭ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደገለፀው ዳውሮ እና ኮንታ ቦንጋ ከተማን ማዕከል ባደረገው ክልል ላይ በመደራጀቱ “ህብረተሰቡ አገልግሎት ለማግኘት ሆነ ከመጀመሪያውም በጥቂት ግል ጥቅመኞች ሴራ የተወለደ አብዛኛውን ህዝብ ከፍተኛ ቅሬታ ውስጥ ያስገባ ውሳኔ በመሆኑ መንግስት ውሳኔውን እንዲያጤነው” በሚል ለመጠየቅ ያለመ ህዝባዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል።

“የዳውሮ እና ኮንታ ህዝብ በአጠገቡ ያለውን በሁሉም ማህበራዊ መስተጋብር ከተጋመዱ ወንድማማች ህዝቦች ተለይቶ በሌላ መዋቅር መግባቱ ታሪካዊ ስህተት ነው” በሚል አሁን ላይ ይሄንን ውሳኔ መንግስት እንዲያሻሽል በኮሚቴ ደረጃ ተደራጅቶ የሚጠይቅ በአከባቢው የህዝብ ድጋፍ ፊርማ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ ሊጀመር እንደሆነም የመረጃ ምንጩ ገልጸዋል።

እንደ መረጃ ምንጫችን ያደረሰን መረጃ እንደሚያስረዳው “ዳውሮ እና ኮንታ ህዝብ አሁን ባለው ካፋ፣ ሾኮ እና ሌሎች ብሄረሰቦች ጋር በአንድ ክልል መደራጀቱ የሚጠላ ባይሆንም የክልሉ ማዕከል ያለበት ከቀድሞ ደቡብ ክልል ሀዋሳ የሚርቅ፣ አገልግሎት ለማግኘት ለመመላለስ የማይመች፣ ለዘመናት የተገነባ ቤተሰባዊ ወንድማማቾች ኡማ አከባቢ ህዝብ ጋር ያለውን ተፈጥሯዊ ግንኘነት እንዲሻክር የሚያደርግ እንዲሁም እውነትን የሚቃረን አደረጃጀት” በመሆኑ የተጀመረ አሳማኝ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ጊዜ ኮሚቴው ይሄንን ሀሳብ ከሁለቱም ዞኖች የተወጣጡ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች የተካተቱበት ልዑክ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ድረስ በማድረስና በመወያየት አውንታዊ ምላሽ እንዳገኙ በቦታው የነበሩ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ገልጸዋል።

እንደ ባለስልጣኑ መረጃ ከሆነ ልዑኩ “በወቅቱ ዳውሮ እና ኮንታ ህዝብ ወደ ደቡብ ምዕራብ ክልል ይደራጅ ተብሎ የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ በችኮላ የተወሰነ፣ ህዝብ ለሌላ ምርጫ በወሰደው ካርድ መልሶ እንዲመርጥ የተገደደበት፣ መላውን ህብረተሰብ ክፍል ያልተወያየበት እንዲሁም ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሽማግሌዎች፣ ከነጋዴዎች እና ወጣቶች የክልሉ አደረጃጀት ከሌሎች ህዝቦች ጋር እንዲሆን ከተወሰነ በሁሉም መስተጋብር ከተጋመዱ ህዝቦች ጋር መሆን አለበት” የሚል ከፍተኛ ተቋውሞ እየተሰማ በአፈና ተግባራዊ የሆነ ውሳኔ ነው ስል ልዑኩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስረዳታቸውን አስረድተዋል።

“የኮንታ እና የዳውሮ ህዝብ በወረቀት ላይ በተፃፈው ህግ ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሄዷል ተብሏል እንጂ አሁንም የህዝብ ልብ ከዎላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ እንዲሁም ሌሎችም ወንድማማች ህዝቦች ጋር እንደሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጥቀስ… ቃል በቃል “በእርስዋ ስልጣን ጊዜ ይሄ ታሪካዊ ስህተት ተብሎ ለትውልድ እንዳይተላለፍ” በሚል ልዑኩ ለጥያቄው አውንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ መማፀናቸውን የመረጃ ምንጩ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አክለው ገልጸዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ እንደሚናቀርብ ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: