


ዎህዴግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ጨምሮ ለሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በፃፈው ይፋዊ ደብደቤ በጋሞ ዞን የሚገኙ በከፍተኛ አመራሮች የሚደገፉ ፅንፈኞች የራሳቸውን መብት ለመጠየቅ ከጉዳዩ ጋር በምንም አይነት ግንኘነት የሌለውን የዎላይታ ብሄር ማንነትን በአደባባይ እየጠሩ መዝለፋቸው ዘላቂ የህዝብ ለህዝብ ግንኘነት የሚያሻክርና ከፍ ያለ ቀውስ በአከባቢው የሚያስከትል በመሆኑ በአስቸኳይ የህግ ተጠያቂነት እንዲኖር ጠይቋል።
በተለያዩ አከባቢዎች ብሄር ብሄረሰቦች ዎላይታን ጨምሮ የአደረጃጀት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ህገመንግስታዊ እና ተፈጥሯዊ መብት ባለቤት መሆናቸውን ለማረጋገጥ በተገኘው አጋጣሚ እና አደረጃጀት እየጠየቀ እና በሰላማዊ መንገድ እየታገለ እንደሚገኝ ዎህዴግ በመግለጫው ገልጿል፡፡
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህግን ባልተከተለ እና ፖለቲካዊ አፋኝ በሆነ ውሳኔ የደ/ብ/ብ/ህ/ክልል መንግስትን ለሁለት ቦታ በማካፈል ዎላይታ እና ለሎች ብሄር ብሄረሰቦች ፍላጎት ውጪ ደቡብ ኢትዮጵያ በሚል አዲስ አደረጃጀት እየተዋቀረ እንደሚገኝም ፓርቲው አብራርቷል።
ይህንን ኢፍትሐዊ እና አግላይ የሆነ ፖለቲካዊ አደረጃጀትና ውሳኔውን በተመለከተ እንድሻርና የብሄሩ ጥያቄ ምላሽ እንድያገኝ ፓርቲያችን ዎህዴግ እና ዎብን ብሄሩን በመወከል በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ መስርተን ጉዳዩ በፍ/ቤት በክርክር ሂደት በቀጠሮ ላይ መሆኑንም አስታውሷል።
ይሁን እንጂ “ከአዲሱ ደቡብ ኢትዮጵያ የተሰኘ አደረጃጀት ጋር በተያያዘ አንዳንድ መዋቅሮች ውስጥ በተለይም በጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ፣ ጨካምባ ከተማ እና በዞኑ ለሎች ወረዳ እና ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች በርካታ ሰዎች አደባባይ በወጡበት ወቅት የተከበረውን ዎላይታን ብሄር ክብር በሚነካ እና የሚያንቋሽሹ እንዲሁም ብሄርን ከብሄር ጋር ሊያጋጩ የሚችሉ ስድቦችንና ዘለፋዎችን ተፈጽመዋል” ስል ዎህዴግ ከሷቸዋል።
በተጨማሪ ፓርቲው “የብሄሩ ተወላጆች እንደአንዳንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሰላም ወጥቶ እንዳይገቡ እና የመንቀሳቀስ ሰብዓዊ መብት በመገደብ ጥቃት ሲያደርሱ ቆይተዋል” ስል ሁኔታውን ገልጿል።
“የጋሞ ዞን አስተዳደርም ሆነ በዞኑ ያሉ የሥር መዋቅር አመራሮችም በወቅቱ የዚህ ወንጀል ተሣታፊዎች ከድርጊታቸው እንድቆጠቡ እና የወንጀል ፈፃሚዎች በህግ እንዲጠየቁ በማድረግ ህገመንግስታዊ ግዴታቸውን ካለመወጣታቸው በተጨማሪ አንዳንድ አመራሮች በወንጀል ድርጊቱ ላይ መሰለፋቸውን ፓርቲው በፃፈው ደብዳቤ ማረጋገጡን አስረድቷል።
ስለሆነም “ይህ ድርጊት የብሄሩን አካላዊ እና ህሊናዊ ጤንነት የጎዳ በመሆኑ በወንጀል ህግ አንቀጽ 269 መሠረት በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠይቅ በመሆኑ በወንጀል ህግ አንቀጽ 274 መሠረት ይህንን ወንጀል ድርጊት እንድፈጸም በአደባባይ ሆነ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ በንግግር፣ በስዕል ወይም በጽሑፍ በአደባባይ የገፈፈ ወይም ያደፋፈሩ ግለሰቦች የወንበዴ ማህበር እንዲሁም አመራሮች ወደ ህግ ፊት ቀርቦ እንዲጠየቁ እንድደረጉ እና የህግ በላይነት እንድከበር እናመለክታለን” ስል ፓርቲው አጥብቆ ጠይቋል፡፡
ዎህዴግ ይሄንን በጋሞ ዞን የዎላይታ ብሄር ማንነት ላይ አስነዋሪ ድርጊት ፈፃሚዎች በህግ እንዲጠየቁ በይፋዊ ደብዳቤ የጠየቀው ኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት፣ ኢፌዴሪ ፍትህ ሚንስትር፣ ኢፌዴሪ ፌደሬሽን ም/ቤት፣ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ችለናል።