




በጋሞ ዞን ሻራ ብሄረሰብ አከባቢ በተፈጠረው አለመግባባት 10 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 15 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
“በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሻራ ህዝብ “መሬታችን ተነጥቀን አልተደመጥንም ታፍነናል፣ ተገፍተን እየተሰቃየን እንገኛለን፣ መንግሥት ፈጥኖ ለጩሄታችን መፍትሔ ይስጠን” በሚል መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ መጠየቃቸውን ተከትሎ ፓሊስ በወሰደው የኃይል እርምጃ ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ 15 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው አርባምንጭ ሆስፒታል የገቡ ስሆን 10 ሰዎች የተገደሉ ቢሆንም የተገደሉ ሰዎች አካል እንኳን አልወሰድንም” ስሉ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አንድ የሟች አባት በስልክ አስረድተዋል።
የጋሞ ዞን አስተዳደር፣ አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ እና የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር በኢፌዴሪ መንግሥት ከፀደቀው የገጠር መሬት አስተዳደር አዋጅ ውጪ፣ ህገመንግስቱንም በሚፃረር መልኩ የሻራ ቀበሌ በአርባምንጭ ከተማ እንዲካለል በመወሰን ከፍተኛ ሽብር በዚህ አምራችና ልማታዊ ህዝብ መሀል በመፍጠር ህዝቡን በማሳደድ፣ በማሰር፣ በማፈን፣ በማስጨነቅ፣ ለእንግልት በመዳረግ ህዝቡ ተረጋግቶ የዘወትር የልማት ሥራውን እንዳያከናውን በማድረግ የልማት ሥራቸውንም ከማስተጓጎል አልፎ የሰው ህይወት እያጠፉ እንደሚገኙ ነዋሪዎቹ ቅሬታ አቅርቧል።
“በምክር ቤት ተወካዮቻችን በኩል ሳንወያይ፣ በሚመራን በጋሞ ዞን ሆነ በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ምንም ዓይነት ውይይት ሳይደረግ፣ እኛም የቀሌዋ ነዋሪዎች ተወያይተን ባልተግባባንበት ሁኔታ በድንገት ሻራ ቀበሌ “በአርባምንጭ ከተማ ተካልሏል” በሚል ከፍተኛ እስር፣ ጫናና አፈና ለምን አንቀበልም አላችሁ በማለት እያደረሱብን የእርሻ መሬት “ከወዲሁ ከአርሶአደሩ በመንጠቅ ለግል ባለሀብቶች እየቸበቸቡ እና ለራሳቸው እየተቀራመቱ ነው” በማለት በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የሻራ ቀበሌ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ለWT ሚዲያ ሰጥተዋል።
በጋሞ ዞን እና አርባምንጭ ከተማ አመራሮች ትዕዛዝ በሰላም እየኖረች ባለችው ሻራ ቀበሌ የተለያዩ የታጠቁ ፀጥታ አካላትን በማስፈር ከፍተኛ የሽብር እና የስነልቦና ጉዳት ተግባራቸውን በመፈፀም ተረጋግተው የእርሻ ሥራቸውን እንዳያከናውኑ በማድረጋቸው ተማሪዎች ጭምር ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው እና አጠቃላይ የመንግስት ሥራ ተቋርጦ ይገኛል ።
“ተረጋግተን ወደ እርሻ ሥራዎቻችን እንዲንመለስ ዘንድ ገለልተኛ ወገን ተቋቁሞ ተገቢዉ ማጣራት ተደርጎ መብታችንን በአስቸኳይ ያስከበርልን ብለን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ጥያቂያችን አልተመለሰም፤ አሁንም በበላይ ክልላችንም ሆነ በኢፌድሪ መንግስት ጉዳቱ ሳይብስብን ፈጣን ምላሽ ይሠጠን” በማለት ጠይቀዋል ሲል ከስፍራው የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ወኪል ታማኝ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ከጋሞ ዞን ዋና ከተማ አርባምንጭ በ 9ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሻራ ብሄረሰብ በጥንትም ራሱን ችሎ በራሱ መሪ ሲመራ የኖረ፣ በካዎ ሜንሳ ናኣ ሌቃ ሻራ በመመራት የኖረ ህዝብ፥ ሆኖም ግን በሴራ ታፍኖ ማንነታቸው እዉቅና ሳይሰጠዉ የኖረ ህዝብ ሲሆይ በአከባቢው የመብት ጥያቄ በማቅረባችን ምክንያት በአከባቢው የጎበዝ አለቆች ቀጭን ትዕዛዝ በርካታ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች፣ አርሶአደሮች፣ ነጋዴዎች፣ የኃይማኖት መሪዎች ጨምሮ ሌሎች በተለያዩ በአርባምንጭ ከተማ የሚገኙ ደረቅ ፖሊስ ጣቢያዎች እና በማረሚያ ቤት ታጉረው ሰብዐዊ እና ደሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተገፈው በእስር፣ በአፈና፣ በእስር እና በስደት እየተሰቃየን እንገኛለን ሲሉም ነዋሪዎቹ በምሬት አክለው ተናግረዋል። Wolaita Times