የ14 ዓመት ታዳጊዋን አስገድዶ የደፈረ ፖሊስ በ8 ዓመት ፅኑ እሥራት ተቀጣ፡፡


የዎላይታ ሶዶ ማረሚያ ተቋም ፖሊስ አባል የሆነው ምትኩ ገዛኸኝ ነው ታዳጊዋን አስገድዶ በመድፈር ወንጀል የስምንት ዓመት ፅኑ እስራት የተወሰነበት፡፡

ተከሳሹ ቀድሞ በመዘጋጀት ተማሪ የሆነችሁን 14 ዓመት ታዳጊዋን ለጊዜው ታርጋ ቁጥር ባልታወቀው ሞተር ሣይክል እሱ ወዳለበት ሞተረኛው ይዟት እንዲያመጣ በማድረግ በታህሳስ 22/2013 ዓ.ም ታዳጊዋን አስገድዶ መድፈር ወንጀል በመፈፀም በታዳጊዋ የአካልና ሥነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባት ማድረጉን ፍርድ ቤቱ አብራርተዋል፡፡

የሶዶ ከተማ አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ተከሳሹ ህግን የማስከበር ኃላፊነት የተጣለበት ፖሊስ አባል ሆኖ ግን ተግባሩንና ኃላፊነቱን ወደ ጎን በመተው ወንጀል መፈፀሙ ወንጀልን የሚያከብድ መሆኑና ታዳጊዋ ተማሪ ስትሆን ግን ትምህርቷ እንዲስተጓጉልና የአካልና አዕምሮ ሥነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባት ማድረጉ ወንጀሉ የከፋ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ማንኛውም አካል ከእንደዚህ ዓይነት ወንጀልና እኩይ ተግባር ራሱን በመጠበቅ ህግን ለማስከበር ተግባር የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ያለዉ ፍ/ቤቱ ለወንጀሉ ግን ተመጣጣኝና አስተማሪ ቅጣት የመስጠት ህግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በዚህም የዎላይታ ሶዶ ከተማ አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ከዐቃቤ የቀረበውን የወንጀል ማክበጃና ከተከሳሹ የቀረበውን ወንጀል ማቅለያ በማገናዘብ ተከሳሹ ለፖሊስ እጅ ከሰጠበት ጊዜ ጀምሮ የሚቆጠር የስምንት ዓመት ፅኑ እስራት ውሳኔ አስተላልፏል ሲል የከተማው ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ዘግቧል፡፡