ከሶስት አመት በፊት የዎላይታ ህዝብ ህገመንግስታዊ በክልል የመደራጀት መብት ጥያቄ እንዲመለስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ “ህገመንግስትንና ህገመንግስታዊ ስራዓትን በኃይል ማፈረስ” በሚል ከሌሎች ጋር ከስልጣናቸው እንዲነሱ ተደርጎ ለእስርና ከስራ ተባረው የነበሩት የቀድሞ የዎላይታ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፊ የነበሩ አቶ ጥበቡ ዮሐንስ ውዝፍ ደሞዝ ከሁለት ዓመት በላይ ከታገደ በኃላ እንዲከፍል በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከተሰጠ የቆየ ቢሆንም በትናንትናው ዕለት አዲሱ በተደረሰው ስምምነትና አቅጣጫ መሠረት መከፈሉን አንድ ሁኔታውን በቅርበት የሚያውቅ አመራር ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተዋል።

እንደ መረጃ ምንጫችን ከሆነ “ባለፈው ሳምንት ከፌደራል ጀምሮ በተለያዩ ደረጃ በአመራርነት የሚገኙ የአከባቢው ተወላጆች በዎላይታ ሶዶ ከተማ ከዞን እና ከክልል አመራሮች ጋር ባደረጉት ምክክር መድረክ ባለፉት ሶስት አመታት በፓለቲካ ልዩነት ምክንያት ከስራቸው የተፈናቀሉና የተሰደዱ ወደ ስራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶት ተግባራዊ እንዲሆን በተደረሰው ስምምነት መነሻ ያንን የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱንም” ገልጸዋል።

በአከባቢው በተለይም ባለፉት አራት አመታት ህገመንግስታዊ በክልል የመደራጀት መብት እንዲከበር ወጣቶች፣ ምሁራን፣ በመንግሥት መዋቅር የሚገኙ ባለስልጣናት፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የትግሉ አካል በመሆን የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል፣ አካል በማጉደል፣ ከስራና ከስልጣን በመነሳት፣ ለእስርና ለስደት ህይወት በመዳረግ መስዋዕትነት የከፈሉ ሲሆን እስከዛሬም በዛ ምክንያት ከስራቸው ተፈናቅለው ቤተሰብን ለችግር አጋልጠው የስደት ህይወት እየገፉ የሚገኙ በርካቶች መሆናቸው ይታወቃል።

በመሆኑም ምሁራን፣ ፓለቲከኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም በየደረጃው ተሰምነት ያላቸው ግለሰቦች በዞኑ የፓለቲካ አካሄድ ልዩነት ምክንያት ብቻ ዳርና ዳር ሆነው የሚገኙ ወገኖች ወደ አንድነት፣ መደማመጥ፣ መተባበር እንዲሁም በጋራ ጉዳይ በሆኑ የህዝብ የልማት ፍላጎቶች ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡና በአንድነት በመሰለፍ ለአጎራባች ህዝቦች ጭምር በጎ ሚና ሊወጡ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ አሁን የተጀመሩ በጎ እንቅስቃሴ አይነት ከማን ምን ይጠበቃል የሚለው ሀሳብም ለጊዜው ምላሽ አላገኘምና በያለንበት እንወያይበት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *