በገናናው የዎላይታ ንጉሥ ሳሶ ሞቶሎሚ ታሪክ በተመለከተ ሁለቱ ሚኒስትሮች የሰጡት አስተያየት አነጋጋሪ መሆኑ ተገለፀ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዳንኤል ክብረት ከሁለት አመት በፊት በተረጋገጠ ፌስቡክ ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት “የያኔው ዳሞት የዛሬ ዎላይታ ማዕከል ያደረገ ጎጃምን ጨምሮ ከአባይ ወንዝ በታች ያለ መንግሥት ነበር። ሞቶሎሚ ደግሞ በ12ኛው መቶ ክ/ዘ የዳታ ንጉሥ የነበረ ሃያል ንጉሥ ነበር። ንጉሱም የማያደርገውን የማያውቅ “እምቡዝ” ነበር።” በሚል የንጉሡን ገናናነት ታሪክ ለማሳነስ በሰነዘሩት ሀሳብ በርካቶች በቁጣ ምላሽ ተሰጥተውታል።

ከሶስት ቀን በፊት ደግሞ አዲስ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዎላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ሀገራዊ የከተሞች ፎረም ማስጀመሪያ ፕሮግራም በማስመልከት በአደባባይ በተዘጋጀው መድረክ ላይ በ12ኛው ክፍለዘመን ገናና የነበረ የዎላይታ ንጉሥ ሞቶሎሚ በተመለከተ ታሪክን አጣቅሰው ባስተላለፉት መልዕክት “ዎላይታ ጥንታዊቷ ሥልጣኔ ባለቤት፣ የጠንካራው ዳሞታ ነገስታት መናገሻ፣ ስመ ጥሩው ንጉስ ሞቶሎሜ ምደር፣ ካዎ ጦና ምድር ናት” በሚል እውነተኛ ምስክርነት በመስጠት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዳንኤል ክብረት የጥላቻና የፈጠራ ንግግር ስለመሆኑ አረጋግጠዋል።

አንድ ዶክተር አበበ ሀረገወይን የሚባል ታዋቂ አማራ ተወላጅ የታሪክ ተማራማሪ ደግሞ ስለ ንጉሥ ሞቶሎሚ ሲያስረዱ ፦ “በ12ኛው ክፍለ ዘመን አጥቢያ የዳሞት (አሁን ዎላይታ ከሚባለው አካባቢ) ሞቶሎሚ የሚባል ሀይለኛ ንጉስ ተነስቶ ከፍተኛ ጦር ይዞ ወደ ሸዋ መዝመት ጀመረ። ቀስ እያለ ግን ወታደሩን እያበራከተ ቡልጋንና ሳልልሽን ድል አድርጎ ያዘ። ከቡልጋ ቀጥሎ ግዛቱን በማስፋፋት ደዋሮንና ደቡብ ሸዋን ድምጥማጡን አጠፋው። ሞቶሎሚ ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ለመያዝ የሚያስችል ጉልበት ነበረው” በሚል የታሪክ ድርሳናትን በማጣቀስ አረጋግጠዋል።

በዎላይታ የነገስታት ታሪክ ሞቶሎሚ የገነባው ሰራዊት በሀያልነቱ ይታወቃል:: በዳሞታ ተራራ ዙሪያ ባሉት ገደላ ገደሎችና ዋሻዎች ተጠልሎ ከዛ እየወጣ ይሰለጥን ነበር:: በታሪክ እንደሚነገረው የሞቶሎሚ ሰራዊት ገደል መዝለል፣ ሸርተቴ፣ የውሃ ሙላት ማለፍ፣ የጦርነት ታክቲክ የፈረስ ግልቢያ፣ አክሮባት፣ እርግጫና ጡጫ፣ ተራራው ላይ እንዲሁም በሜዳ ልምምድ ያደርግ ነበር::

ንጉስ ሞቶሎሚ በዚህ በሰለጠነ ሰራዊታቸው በሸዋ ሰሜናዊ አቅጣጫ እስከ ጎጃም ደጋ ድረስ፣ በሸዋ አገር ከጅሩ ወደ ግራ ታጥፈው ሞቶሎሚ ሰፈር የሚባለውን ጨምሮ ቡልጋ ፀላልሽ ወረዳ በዘመቻ እንደደረሱ ይነገራል:: የንጉስ ሞቶሎሚ መካነ መቃብር በአሁኑ አማራ ክልል ቡልጋ እንደሚገኝ ልብ ይሏል::

በዎላይታ ዞን ቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ አጆራ ቀበሌ በሚገኘወና የምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው የአጆራ መንትያ ፏፏቴዎች ላይ የዛሬ 800 ዓመታት አካባቢ ከታች በፎቶ የሚታየው የፃድቁ አባት የንጉስ ሞቶሎሚ ልጅ የአቡነ ተክለሃይማኖት እናት ቅድስት እግዛሪያንን በወቅቱ የዎላይታ ገናና ንጉስ ሞቶሎሚ በሰርግ ያገባበት እና ፃድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት የተፀነሱበት ታሪካዊ ስፍራ መሆኑን የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።

ቅድስት እግዛሪያን ስም በዎላይታ አካባቢ “ሳራ” ( ትርጉሙ ሰላም ሁኚ ማለት ነው) የምትባል ሲሆን አቡነ ተክለሃይማኖት ስም ደግሞ “ሹሙሩኮ” ( በዎላይታቶ) ተብሎ ይጠሩ ነበር::

ይህንን ታላቅ ትውፊታዊ ገድል እና ሌሎች የታሪክ ድርሳናትን ስናይ የጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት እናት እግዘሪያ በንጉሥ (ካዎ) ሞቶሎሜ ወታደሮች ተማርከው ወደ ዎላይታ የንጉሡ ቤተመንግሥት መቀመጫ ወደሆነው ወደ ዳሞት ተራራ እንደመጡና ከንጉሡ ጋር ለአያሌ ቀናት ከቆዩ በኃላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እንደሄዱ፣ እግዘሪያ በንጉሡ ወታደሮች ስማረኩ ቄስ የሆኑት ባላቸው ፀጋዘአብ መኻን በመሆናቸው ልጅ እንዳልነበራቸው እና ከምርኮ ስመለሱ ከንጉሥ ሞቶሎሜ አርግዘው ስለነበረ አቡነ ተክለሃይማኖትን እንደወለዱ ይገልጻል።

ይህ ግዜ ልክ የዛሬ 756 አመት አካባቢ ሲሆን አቡኑ አድገው ከጎለመሱ በኃላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የክርስትና እምነት ለንጉስ ሳሶ ሞቶሎሚና ለሕዝቡ ለማስተማር ብለው ከቡልጋ ወደ ዎላይታ እንደገቡ በታሪክና በአዛውንቶች ይነገራል::

ብፁዕ ወቅዱስ ለስብከት ስራቸው ወደ ተራራው ጫፍ ማለትም ወደ ንጉሱ ቤተ መንግስት የሚመላለሱበት መንገድ ከጋራው እግርጌ በስተደቡብ ከዳርና-ጉብታ በኩል በነበረው ጠመዝማዛ፣ አድካሚ ዳገትና ቀልቁለት በመውረድና በመውጣት ተመላልሰው ነበር የሰበኩት።

ከታች ወደላይና ከላይ ወደ ታች በእግር ጉዞ ወቅት ሲደክማቸው አርፈው የሚፀልዩበትን ዘወትር የሚመላለሱበትን መንገድ የአካባቢው ሰዎች እስከ ዛሬ ድረስ የእግዜአብሔር መተላለፊያ (ጦሳ ፔንግያ) በማለት ይጠሩታል::

የስያሜውን ምክንያትም ሲነግሩ የአቡነ ተክለሃይማኖትና የመነከሴዎቹ መመላለሻና መተላለፊያ ስለነበረ፣ እነሱንም ሕዝቡ እንደጻድቅ ስለሚቆጥራቸው ይኸው የተመላለሱበት ያረፉበት ቦታ የእግዜአብሔር መንገድ ተብሎ ሊጠራ ችሏል::

የአፍሪካ ገናናው ሞቶሎሚ የሚባል ሀያሉ ንጉስ በዎላይታ ከ1195 እስከ 1272 ለ77 አመታት እንደነገሰ ይነገራል። ንጉሱ በዎላይታ ሶስት የቤተ-መንግስት ማዕከላት ነበሩት:: እነዚህም፦ 1ኛ በኪንዶ ዜጌረ አካባቢ፣ 2ኛ በቦሎሶ ዛባ ተራራ ላይ የነበረው አፋማ ቤተመንግስት፣ 3ኛ በዳሞታ ተራራ ላይ አናት ያለው ጣዛ
ቤተመንግስት (ጋሩዋ) በመባል ይታወቃሉ።

ንጉስ ሳሶ ሞቶሎሚ የዎላይታ ንጉስ በነበሩበት ዘመን የዎላይታ ቆዳ ስፋት በተለያዩ አቅጣጫዎች እንዳሰፉ ይነገራል። በዳሞታ ተራራ ካላቸው ቤተመንግስት ተነስቶ በመዝመት በርካታ አካባቢዎችን በቁጥጥር ስራቸው እንዳዋሉ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድል የሚናገረውን ጨምሮ የተለያዩ የታሪክ መጽሐፍት ጠቅሰዋል። በርግጥ የንጉስ ሞቶሎሚ ታሪክ የሕዝቦች መልካም ታሪካቸው በሚገባ እንዳይፃፍና እንዳይነገር ግልፅም እንዳይወጣ ታፍኖ ተይዟል።

የዳሞታ ሥረ-ወመንግስት ‘ሀ’ ተብሎ የተጀመረበት፣ ታላቁ የዎላይታ ህዝብ ሥልጣኔ የተጠነሰሰበት፣ ንጉስ ሞቶሎሚ የተዋጋበት እና በአቡነ ተ/ኃይማኖት ክርስትና የተቀበሉበት፣ ጥንታዊ የቅድስት ስላሴ ቤ/ክን የሚገኝበት፣ ከ58 ሺህ አመት በፊት የሰው ልጅ መኖር የጀመረበት ሞቼና ቦራጎ ዋሻ፣ በ1279 ዓ.ም አቡነ ተክለ ኃይማኖት ጠመዝማዛና አድካሚ ዳገት በመውጣት ተመላልሰው ይሰብኩ የነበረው መንገድ “የጦሳ ፐንግያ” አልፎ ወደ ተራራው አናት በመውጣት ንጉሡንና ሌሎች ክርስትና እንዲቀበሉ ያደረጉበት፣ የዎላይታ ሶዶ ከተማን ቁልቁል እያየ የቆመ፣ የብዙ ቱሪስቶች ቀልብ መግዛት የቻለ፣ ባለ ግርማ ሞገሱ ”ዳሞታ ተራራ’‘ ከተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ካገኘነው መረጃዎች በተጨማሪ ለዚያ ሁሉ እውነተኛ ኢትዮጵያ በውስጧ ለዘላለም ደብቃ የያዘችው ታሪክ ህያው ምስክር ነውና ይጎብኙ፤ ሀገርዎን ይወቁ።

ለመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዳንኤል ክብረት ከሁለት አመት በፊት ገናናው የነበረውን የዎላይታ ንጉሥ ሳሶ ሞቶሎሚ በጥላቻ ተሟልተው “እምቡዝ” በሚል ታሪካቸውን ለማሳነስ ቢገልፁም ከሶስት ቀን በፊት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዎላይታ ሶዶ ከተማ በአደባባይ በተዘጋጀው መድረክ ላይ በ12ኛው ክፍለዘመን ገናና የነበረ የዎላይታ ንጉሥ ሞቶሎሚ በተመለከተ ታሪክን አጣቅሰው ባስተላለፉት መልዕክት “የጠንካራው ዳሞታ ነገስታት መናገሻ፣ ስመ ጥሩው ንጉስ ሞቶሎሜ ምደር” በሚል ታሪክ ሳያዛንፉ ምስክርነታቸውን መስጠቱ በቀደመው ዳንኤል ክብረት ንግግር የተቆጡት “ለማስታገስ ይሁን እውነተኛ ኢትዮጵያ ለመፍጠር ከተፈለገ እውነተኛ ታሪክ ሊነገርና ሊፃፍ ይገባል” ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው ለማለት እንደተፈለገ ለጊዜው ማወቅ አልተቻለም።

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቤታሎ የተጠናከረ ዘገባ ነው።

1 thought on “አነጋጋሪው በገናናው ዎላይታ ንጉሥ የሁለቱ ሚኒስትሮች አስተያየት

  1. wolaita the land of orgin “ዎላይታ ጥንታዊቷ ሥልጣኔ ባለቤት፣ የጠንካራው ዳሞታ ነገስታት መናገሻ፣ ስመ ጥሩው ንጉስ ሞቶሎሜ ምደር፣ ካዎ ጦና ምድር ናት”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *