በዎላይታ ዞን የመንግስት ሠራተኞች ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግምባር(ዎህዴግ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ

በዚህ ዓመት በዎላይታ የመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ መጥፋት ጋር በተያያዘ እየተደረጉ ያሉ አደገኛ ሁኔታዎች በአጽንኦት እየተከታተልን መቆያታችን ይታወሳል። ይሁንና በዚህ ሶስትና አራት ወራት ሁኔታው እየተባባሰ መምጣቱን አስመልክቶ ዎሕዴግ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አወጥቷል።

  1. በቀን 8/9/2016 ዓ.ም ደመወዛችን ይከፈለን በራብ አንሙት እያሉ በሰላማዊ መንገድ የሠሩበትን ክፊያ ለመጠየቅ ወደ ክልል ቢሮዎች በመጡት ሠራተኞች ላይ ፖሊስ መንገድ በመዝጋት የወሰደው የእስራትና የድብደባ እርምጃ ፓርቲያችን አጥብቆ ያወግዛል፣
  2. የመንግስት ሠራተኞች በሚሰሩበት አከባቢ ተረጋግቶ እንዳይሰሩ ደመወዝና ጥቅማጥቅም በመከልከል አከባቢውን የሰላም እጦት ያለበት አከባቢ ለማስመሰል የሚደረግ አደገኛ የፖለቲካ ሴራ በአስቸኳይ እንዲቆም ዎህዴግ አጥብቆ ያሳስባል፣
  3. ሆን ተብሎ ከሌሎች አከባቢዎች በተለዬ መንገድ ህዝባችንን የሚገባውን በመከልከል ማስራብ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን እንገነዘባለን። በመሆኑም ዛሬ ነገ ሳይባል የተወዘፈባቸው ደመወዝ ተለቅቆ ሠራተኞች ቤተሰቦቻቸውን ተረጋግቶ እንዲመሩ እንዲደረግ ዎህዴግ አጥብቆ ያሳስባል፣
  4. ዎላይታ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ የገቢ ግብር የሚሰበሰብበት አከባቢ ሆኖ ሳለ ምንም እንደሌለው ለማስመሰል የሚደረግ ፖለቲካዊ ሸፍጥ ቆሞ ሠራተኞቹ በአስቸኳይ ጥቅማቸው ተከብሮ ሥራቸውን እንዲከውኑ እንዲደረግ ዎህዴግ ያስገነዝባል፣

በመጨረሻም የመንግስት ሠራተኞች የሚጠይቁትን ፊትኃዊና ህጋዊ ጥያቄዎችን ለማፈንና ደመዘዝ ለመከልከል የሚደረጉ አፈናዎች ቆሞ ለሠራተኞቹ ተገቢ ምላሽ የማይሰጥና እንግልቱ የማይቆም ከሆነ ሰላማዊ ትግሉ የሚቀጥል ከመሆኑም በላይ መላው የዎላይታ ህዝብን፣ የመንግስት ሠራተኞችን፣ እንዲሁም አባሎቻችን በቀጣይ ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራት የሚንገደድ ጭምር መሆኑን በጥብቅ ያስገነዝባል።
ከሠላምታ ጋር!

የዎህዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
9/9/2016 ዓ.ም
ዎላይታ ሶዶ/ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *