
ሰሞኑን ከሚኒስትርነት ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት በተጨማሪ የአንድ ቢሮ ኃላፊ ተደርገው የተሾሙት ግለሰብ ማናቸው ❓ከዚያ ባሻገር ለመሆኑ ክልሉ ገና በጅምሩ በበርካቶች ከህዝብ ተጠቃሚነት አንፃር “ኢፍትሐዊነት እየተስተዋለ ነው” እያሉ ባለበት የሹመታቸውን አንደምታ የአከባቢው ምሁራንና በቅርበት የሚያውቃቸው ፓለቲከኞች ምን ይላሉ❓

እኚህ ሰው አቶ ገብረመስቀል ጫላ ማጣሎ ይባላሉ። የተወለዱት በዎላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ ጋቼኖ ቀበሌ ሲሆን በ1976 ዓ.ም በቦዲቲ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ካመጡት 4 ብቻ ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አምስት ኪሎ በመከታተል የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በስታትስቲክስ ትምህርት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ እንዲሁም በተጨማሪ በ1992 ዓ.ም በህንድ ሀገር ኒው ደልሂ ዩኒቨርስቲ 2ኛ ድግሪ ትምህርታቸውን በኢኮኖሚክስ (በምጣኔ ሀብት) ትምህርት በመከታተል ያገኙ ስለመሆኑ ከግል ማህደራቸው ለማወቅ ችለናል።

ከትናንት በስትያ በይፋ በክልሉ ምክርቤት ቀርበው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዲሁም የንግድና እንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ በመሆን መሾማቸውን በቃለ መሃላ ያረጋገጡት አቶ ገብረመስቀል ጫላ ማጣሎ ከዚህ በፊት የነበራቸውን የፓለቲካ ተሳትፎና ልምድ ስንመለከት 🕕📝👇
✅ ከ1993-1995 ዓ.ም የደቡብ ክልል ስነ-ህዝብ እና ስታትስቲክስ ቢሮ ኃላፊ በመሆን፤
✅ ከ1995 – 1998 ዓ.ም የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ፤
✅ ከ1998- 2000 ዓ.ም የደቡብ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን፤
✅ ከህዳር 2000- 2003 ዓ.ም የደቡብ ክልል ንግድ ኢንዱስትሪ ቢሮ ም/ኃላፊ እና የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ኃላፊ በመሆን፤
✅ ከህዳር 2003 እስከ 2008 ዓ.ም የፌደራል የጥቃቅንና አነስተኛ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር፤
✅ ከህዳር 2008 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 2013 ዓ.ም የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ በመሆን፤
✅ ከመስከረም 2014 ዓ.ም – ሰኔ 2016 ዓ.ም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ሚኒስቴር በመሆን ማገልገላቸውን ከግል ማህደራቸውና በቅርበት ከሚያውቃቸው ሰዎች የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከዚያ ባሻገር ለመሆኑ ክልሉ ገና በጅምሩ በበርካቶች ከህዝብ ተጠቃሚነት አንፃር “ኢፍትሐዊ አሰራሮች እየተስተዋለ ነው” እያሉ ባለበት ወቅት የሹመታቸውን አንደምታ የአከባቢው ምሁራንና በቅርበት የሚያውቃቸው ፓለቲከኞች ምን ይላሉ❓
አንድ የክልሉን ፓለቲካ በቅርበት የሚከታተል ምሁር በጉዳዩ ዘሪያ ስንጠይቅ “በክልሉ ፍትሀዊ እና ተመጣጣኝ መንግስታዊና ፖለቲካዊ ዉክልና ባለማግኘቱ አንኳር በሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ለማስገኘት እንዲሁም የልማት ፍትሃዊነት ለማስጠበቅ ግልፅ እና አሳታፍ የህግ ሥርዓት ተዘርግቶ እንዲመራ መስራት ሲገባ በአሁኑ ወቅት ከዚያ እውነታ በተቃራኒው ተጨባጭ እንቅስቃሴ መኖሩን በመጥቀስ አዲስ ከፌደራል በገለልተኝነት የመጡ ግለሰብ በመሆናቸው የመጀመሪያ እርምጃ በአስተባባሪ ደረጃ ይሄንን አንገብጋቢ ጉዳይ እንደ ዋና አጀንዳ ተይዞ እንዲፈታ በኃላፊነት ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ክልሉ በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ያሉበት የብዝሐ ብሔር፣ ባህል፣ ቋንቋ ታሪክ ያለው ክልል በመሆኑ ችግሮች በጊዜው መቅረፍ ካልተቻለ እንዲሁም ከነበሩት ነባር ችግሮችና ጥያቄዎች በተጨማሪ በአደረጃጀት ሂደቱ ላይ የነበሩ ጉልህ ስህተቶችና ክልሉ ከተደራጀም በኋላም እየተስተዋለ ያለው የመልካም አስተደዳር ጉድለቶች፣ የሥልጣን ላይ ብልግናና ሽኩቻ፣ የሕግ የበላይነት መጥፋት፣ የክልሉ አስተዳደር ወሳኔዎች መርህ የለሽ መሆን፣ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋው ሙስና እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ክልሉን ለመፍረስ አደጋ ከመጋረጣቸው በላይ አሁን ሀገሪቱን በሌሎች ክልሎች እየገጠማት የሚገኘው አይነት የፀጥታና የፖለቲካ ችግር ተጨማሪ ራስ ምታት ወደ መሆን እየደረሰ ያለው ጉዳይ መቅረፍም የቅድሚያ ትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበትም በአፅንኦት አሳስበዋል።
ህገመንግስት ያጎናፀፈውን ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ ህጎች በህገ-መንግስት ጭምር እንዲካተት በማድረግ አዋጆች፤ ደንቦች እና መመሪያዎች ተዘጋጅተዉ ወደ ተግባር መገባቱን በመግለፅ በተለይም በክልሉ ሀብት የሚያስተዳድሩ ቢሮዎችን በመደልደል ሂደት የተፈጠሩ አድሏዊና ግልፅነት የጎደለ አሰራር ጎልተው የሚታየውንና የፖለቲካ ሥልጣን ክፍፍልና የአኮኖሚ ተጠቃሚነት ኢፍትሐዊነት የመሳሰሉ ችግሮች ጫፍ ደርሰው በአከባቢው ቀውስ ከመከሰቱ በፊት የእርማት እርምጃ እንዲወስድና ሕዝቡም ችግሮቹ የሚከሰትባቸውን ሁኔታ ተገንዝቦ በአከባቢው የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በአስቸኳይ መፍትሔ ለማበጀትና ከፌደራል መንግስት ጋር ያለውንም ጤናማ ግንኙት በማጠናከር አዲሱ የተሾሙት አቶ ገብረመስቀል መዘጋጀት እንዳለባቸውም ምሁሩ ጠይቀዋል።
አንድ ሌላኛው የአከባቢው ፓለቲካኛ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚህ ዙሪያ ተጠይቆ ሀሳብ ሲስጥ “በተለይም የዎላይታ ህዝብ ይሄኛው ክልል ከመደራጀቱ በፊት በትልቁ ከ56 ብሄር ብሄረሰቦች በላይ አብሮ በአንድ ክልል መዋቅር በሚኖሩበት ወቅት የገዥው ፓርቲ ወይንም የመንግስት መሪነት ሚና ነበራቸው፥ በነበረው አደረጃጀት ውስጥም ከህዝብ ቁጥር፣ ከኢኮኖሚው ገቢ ማመንጨት አስተዋጽኦ እንዲሁም ተያያዥ ተጨባጭ እውነታ አንፃር በአመዛኙ ውክልናና ተገቢ ተጠቃሚነት የነበረ ቢሆኑም አሁን ይባስ ብሎ አዝማሚያዎች በተቃራኒው እየሄዱ በመሆኑ በርካቶች ከፍተኛ ቅሬታ እያቀረቡ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ከዚህ አከባቢ የወጡት አቶ ገብረመስቀል ጫላ ኃላፊነታቸውን የበለጠ የህዝብ አደራና ኢፍትሀዊ አሰራሮች እንዲስተካከሉ የማድረግ ኃላፊነት በድርብ ተጥሎባቸዋል” በሚል ገልጸዋል።
ፓለቲከኛው አክለውም የአዲሱ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በአከባቢው ከዚህ በፊት በፓለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት የተራራቁና ለህብረተሰቡ በጎ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉትን የህዝብ አንድነት ለማጠናከርና የህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚገባ እንዲረጋገጥ ለማድረግ ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ልዩነቶችን በእርቅና በይቅርታ ለመፍታት የሚያስችል መድረክ እንዲመቻች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም ተማፅነዋል።
ከዚያ ባሻገር የፍትሐዊነትና የዕኩልነት መርሆዎች በሚነሱበት ወቅት አንዱን የህብረሰብ ክፍል አለአግባብ በመጥቀም ሌላውን አለአግባብ የሚጎዳበት አደገኛ ሁኔታ ስለሚፈጥር የመንግስትና የሕዝብ ሀብት እንዲሁም የአስተዳደር ፖለቲካ የመምራት ኃላፊነት ተቀብለው እየሰሩ የሚገኙ አካላት የፍሐዊነትና የዕኩልነት መርሆዎችን በተገቢው ተረድተው “ለራስ በልዩነት” ከሚለው አስተሳሰብና ድርጊት በመታረም በክልሉ ለሚገኙ ሁሉም ህብረተሰቡ ክፍሎች የሚገባቸውን ጥቅምና ክብር እንዲያገኙ በትብብር መንፈስ መስራት እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም አቶ ገብረመስቀል ጫላ ማጣሎ ጋር በቅርበት የሰራና የሚያውቀው ግለሰብ ከላይ የተጠቀሱ በክልሉ እየተስተዋለ የሚገኘውን ችግር በተመለከተ ሲያስረዳ “በጠረጴዛ ዙሪያ አጀንዳዎችን አቅርበው ተመካክረው ለመቅረፍና የበኩላቸውን ሚና ለመጫወት ለረጅም አመታት በተለያዩ አመራርነት ደረጃዎች ባካበቱት ልምድና እውቀት ተጠቅመው በክልሉ በርካቶች የሚጠብቁት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመዘገብ የማድረግ አቅም ያላቸው ትሁት፣ ቅን፣ ስራ ወዳድ፣ በጋራ የመስራትና አመራር መስጠት የሚችል በሳል ሰዉ” በማለት ስለእሳቸው በመመስከር ኃላፊነታቸውን በአገባቡ እንደሚወጡ ተስፋ እንደሚያደርግም አስረድተዋል። #WolaitaTimes
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው