
በዎላይታ ሶዶ ከተማ ዋና ጎዳናዎች ተጀምሮ ለረጅም ጊዜ የቆሙ የጀግኖች መታሰቢያ ሀውልቶችን ህብረተሰቡን በማስተባበር ለማጠናቀቅ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ገልጿል።
ፓርቲው በተለይም የዎላይታ ሕዝብ አምባሳደር በሆነው ልማት ማህበር በኩል የታቀዱ ዕቅዶችን ህዝብን በማሳተፍ መስራት ለትውልድ የሚወረስ አሻራ በሚያደርገው ሁሉም ያለልዩነት የየድርሻቸውን ሚና እንዲጫወትም ጥሪ አቅርቧል።

የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ፓርቲ ሀገራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ለሕዝብ አለኝታ ለሆነው የዎላይታ ልማት ማህበርን ቀጣይነት ባለውና በተደራጀ መልኩ በውጭ ሀገራትና በሀገር ውስጥ የሚገኙ አባላትን፣ ህዝብንና ደጋፊዎችን በማስተባበር ድጋፍ እንደሚያደርግ በማረጋገጥ ለአሁኑ የማህበሩን ዓላማ ለመደገፍ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ቀጣይነት ባለው መንገድ በጋራ ለመስራትም ከስምምነት መደረሱን ፓርቲው ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።

“የዎላይታን ህዝብ ሁለንተናዊ ልማት እና ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መላው ዎላይታዊያን አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ ያለ ልዩነት በዎላይታቴታ አንድ በመሆን ለጋራ ዓላማ ቅድሚያ በመስጠት መረባረብ፣ መትጋት እና ድጋፍ በማድረግ ለህዝባችን ለውጥ መስራት እንዳለብን ዎሕነን ያምናል” በሚል ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በላከው መግለጫ አስረድቷል።
“ዎሕነን ሀገራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ለዎላይታ ሕዝብ አለኝታ ብሎም ከህዝብ ለህዝብ ለሆነው የዎላይታ ልማት ማህበር ቀጣይነት ባለው መልኩ ለቀጣይ ግዚያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ተበታትኖ የሚኖረውን የዎሕነን አባላትንና የዎላይታን ህዝብን በማስተባበር ድጋፍ እንደሚያደርግ በማሳሰብ ለአሁኑ የማህበሩን ቅዱስ ዓላማ ለመደገፍ የበኩሉን ገንዘብ በመለገስ ከማህበሩ ጋር አብሮ በቀጣይነትም እንሰራለን” በሚል አረጋግጧል።

አክለውም “ፓርቲያችን፥ የዎልማ ፍሬ የሆኑት የተለያዩ ተቋማት ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ እና የዎላይታ ሕዝብ አምባሳደር በመሆናቸው ሁሉም ዎላይታዊያን ያለ አንዳች ልዩነት ለማህበሩ ድጋፍ በማድረግ ለማህበሩ አጋር በመሆን ከጎኑ መቆም አለብን፤ የልማት ማህበሩ ከፖለቲካ፣ ከሐይማኖት፣ ከዘረኝነት ገለልተኛ በመሆኑ የትኛውም የፖለቲካ፣ የሐይማኖት እና ሰብዓዊነት የሚሰማው ግለሰብ ሆነ ቡድን በተለይ በዎላይታ የልማት ክፍተቶችን ለመድፈን ሁሉ-አቀፍ ጥረት ማድረግ ግዜ የማይሰጥበት እና አንዱ የትግል ዓላማችን አካል እንደሆነ ያምናል” ብሏል።
ፓርቲው “በቀጣይም በልማት ማህበሩ ስር ሊሰሩ የታቀዱ እና በተለያዩ ምክንያቶች የተስተጓጎሉ ልማቶች፥ ለአብነትም የዎላይታዊያን የታሪካዊ ታላቂነት እና ስልጣኔ ምክንያት የነበሩ ከ50 በላይ ነገስታት ምድር የሆነችው ዎላይታ የነገስታቷ እና የጀግኖቿ መታሰቢያ ሀውልቶችን ጨምሮ ያሉ ልማቶችን ህዝብን በማሳተፍ መስራት ለትውልድ የሚወረስ አሻራ ማኖር ስለሆነ ያለልዩነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለመላው ዎላይታዊያንና ወዳጆች ጥሪ ያቀርባል” ሲል በላከልን መግለጫ ላይ አትቷል። #WolaitaTimes