1000016202

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሰረተ በዛሬው ዕለት የተመሠረተበትን አንደኛ አመት በዎላይታ ሶዶ ጉተራ አዳራሽ አክብሯል።

ይሄንን በማስመልከት የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የዚሁ ክልል ጉዳይ በቅርበት እንደሚከታተለው ክልሉ ከህዝብ ተጠቃሚነት አንፃር በፓለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚው ዘርፍ የተስተዋሉ ማነቆዎችን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜ ከተለያዩ ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉ ምሁራን ያሰባሰብናቸውን መረጃዎችን መነሻ በማድረግና አስተያየቶችንም አካቶ ተጨባጭ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እንደሚከተለው ተመልክቷል።

👉 በአደረጃጀት ሂደቱ ላይ የነበሩ ጉልህ ስህተቶችና ክልሉ ከተደራጀም በኋላ እየተፈፀሙ ያሉ የመልካም አስተደዳር ጉድለቶች፣ የሥልጣን ላይ ብልግና፣ የሕግ የበላይነት መጥፋት፣ የክልሉ አስተዳደር ወሳኔዎች መርህ የለሽ ሆኖ መቀጠል፥

👉 የክልሉ መንግስት በተለያዩ ደረጃ መገለፅ በሚችል በዞኖቹ ውስጥ ጉዳዮች በመግባት የህዝብ ፍላጎት እንዳይሳካና በአከባቢው የውስጥ አንድነት እንዲጠፋ ለማድረግ መሞከር፥

👉 የክልሉ የፖለቲካ እና የአመራር ብልሽት ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የፀጥታ ራስ ምታት እንዲሁም ህዝባዊ የመልካም አስተዳደር ቁጣ የሚያስነሳ ከፍተኛ አዝማሚያዎች መኖሩ፥

👉 የክልሉ የፓለቲካና የአስተዳደር መዋቅር ማዕከል በሆነው ዎላይታ ሶዶ ከተማ ላይ የተወሰኑ መዋቅሮች ቢሯቸውን ለመገንባት ከዞኑ መሬት በመውሰድ እንቅስቃሴ እያደረጉ ቢሆንም የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ጨምሮ ዋናዎቹ በክራይና ቀድሞ በዞኑ በጀት በተገነቡ ቤቶች ላይ ማድረግ፥

👉 ለምሳሌ በጋሞ ዞን በ2010 እስከ 2014 ዓ.ም በዞኑ አስተዳዳሪ በነበሩት እንዲሁም የወቅቱ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ በአቶ ብርሃኑ ዘዉዴ ከክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት እውቅና ውጪ መሬት በምደባ ማስተላለፍ (የተላለፈላቸው የመሬት መጠን 103,410.3 ካሬ ሜትር የተመዘገበ ካፒታል 1,111,249,297 ስራ ላይ የዋለ 24,764,800 )፤

👉 በኮንሶ፣ ዘይሴ፣ ቁጫ፣ ጉማይዴና ሌሎች ቦታዎች ከአመራር ጉድለት ምክንያት የተስፋፋው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አይነት የፀጥታና የፖለቲካ ችግር ለክልሉ ተጨማሪ ራስ ምታት ወደ መሆን መድረስ፥

👉 የክልሉ ማዕከል ከተሞች መብዛትና የክልሉ ቢሮዎች ተበታትነው በመገኘታቸው በሕዝቡ፣ በክልሉ ሠራተኞች ያስከተለው እንግልትና ከፍተኛ የሆነ የበጀት ብክነት መጋለጥ፥

👉 የክልሉ መንግስት መቀመጫ ከተማ በውል ለይቶ ባለማስቀመጥ በክልሉ ህገ-መንገስትም ጭምር ብዥታ በመፍጠር የክልሉ መንግሥት መቀመጫ በሆቴል ማድረግ፥

👉 በክልሉ ምላሹ ባላገኙ የአስተዳደር እና የማንነት ጥያቄዎች ምክንያት እየተፈፀሙ የሚገኙ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለምሳሌ ግድያዎች፣ የዘፈቀደ እስራት እና መፈናቀል መበራከት፥

👉 በክልሉ ሀብት የሚያስተዳድሩ ቢሮዎችን በመደልደል ሂደት የተፈጠሩ አድሏዊና ግልፅነት የጎደላቸው አሠራረሮች ጎልተው መታየት፥

👉 በክልሉ አብዛኞቹ ከተሞቹን ለይስሙላ ብቻ አልፎ አልፎ ስብሰባ ከማድረግ ውጪ በግልጽ በአደባባይ በሚገለፅ ደረጃ በአድሎ ለአንዱ ብቻ በህገወጥ መንገድ መጥቀም፥

👉 በክልሉ የፖለቲካ ሥልጣን ክፍፍልና የአኮኖሚ ተጠቃሚነት ኢፍትሐዊነት፤ የክልሉ አስተባባሪ አካላት ለሁለት በመሰንጠቅ ጎራ ተለይቶ መካረር መጀመሩ እና ይህም እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ መዝለቅ፥

👉 በክልሉ ፌዴራል ባለሥልጣናት ተዋናይ እንደሆኖቡት የሚጠረጠረው ከጥቂት ዘራፊ ባለ ሀብቶች ጋር በመመሳጠር በፕሮጀክቶች፣ ከድንጋይ ከሰልና ከሌሎች ማዕዳናት፣ የእርሻ መሬትና የከተማ መሬት ምዝበራ፣ የሆቴል መስተንግዶዎች ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ አሻጥሮች መብዛት፥

👉 የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ምድብ ችሎት ዎላይታ ሶዶ የተቋቋመው የፍትሕ አገልግሎቱን ለአብዛኛዉ ክልሉ ሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ በቀድሞ ክልልም አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ቢሆንም ግልጽ ባልሆነ መንገድ አንስቶ ህብረተሰቡን ለተለያዩ እንግልት ማጋለጥ፥

👉 ህገመንግስት ያጎናፀፈውን በቁጥር ብዙ የሆኑ ህዝቦች ጥቅም ልጎዱ የሚችሉ ህጎች በህገ-መንግስት ጭምር እንዲካተት በማድረግ አዋጆች፤ ደንቦች እና መመሪያዎች ተዘጋጅተዉ ወደ ተግባር መግባት፥

👉 ዎላይታ ዞን “ደቡብ ኢትዮጵያ” በሚል የተዋቀረ ትንሹ ክልል ከመደራጀቱ በፊት በትልቁ ከ56 ብሄር ብሄረሰቦች በላይ አብሮ በአንድ ክልል መዋቅር በሚኖሩበት ወቅት የገዥው ፓርቲ ወይንም የመንግስት መሪነት ሚና ነበራቸው፥ በነበረው አደረጃጀት ውስጥ ከህዝብ ቁጥርና ተያያዥ እውነታ አንፃር ውክልና ተገቢ ተጠቃሚነት የነበረ ቢሆኑም አሁን በትንሹ ክልል ያንን ማሳጣት፥

👉 በተለይም በዎላይታ አከባቢ ማዘጋጃ ቤቶችን ምርመራ አለ በሚል በየጊዜው አገልግሎት በማቋረጥ ግብር የሚሰበሰብበት እየታወቀ ግብር ለመሰብሰብ ያቀዱ ያዘጋጁ በተገቢው እንዳይሰበሰቡ መዋቅር ላይ ያሉትን በሙሉ በትነው በአዲስ መተካት እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰበንና ባለሀብቶችን የማሳደድና ተረጋግተው እንዳይሰሩ ማድረግ፥

👉 በኢኮኖሚው ረገድ በተለይም በዎላይታ አከባቢ የነበረውን ልማት በመንጠቅ ራሱን እንዳይችል የተጠና ሴራ በማስላት ነጋዴውን ከንግድ ዓለም ማውጣት በከባድ ግብር፣ መንግስት ሠራተኛው ደመወዝ አዘግይተው እንድጎሳቆል ማድረግና ቤቴሰብ መበተን ለሆዱ ብቻ የሚጮህ ትውልድ መፍጠር፣

👉 የአለም ባንክ የከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ፕሮግራም ( UIIDP) ማዕቀፍ ተጠቃሚ የነበሩ ቦዲቲ እና አረካ ከተማ በ2020 ዓ.ም አሁን ላይ አለም ባንክ ያወጣውን መስፈርት በተገቢው በማሟላትና የተሻለ አፈፃፀም በየጊዜው በማሳየት በክልሉ ከፕሮግራሙ ከፍተኛ ተጠቃሚ እየሆነ የሚገኘው ዎላይታ ሶዶ ከተማ የታለመውን አላማ ሲያሳካ ባላቸው አፈፃፀምና በየጊዜው በሚያሳዩት የተግባር መሻሻል መነሻ የሶዶ ከተማ ደረጃ ስለሚደርሱ ቦታውን የሚተኩ ናቸው” ተብለው ታቅደው የነበረ ቢሆንም ከተሞቹ እንዲሰረዙ ማድረግ፥

👉 የፍትሐዊነትና የዕኩልነት መርሆዎችን በመጣስ አንዱን የህብረሰብ ክፍል አለአግባብ በመጥቀም ሌላውን አለአግባብ የሚጎዳበት አደገኛ ተጨባጭ አዝማሚያዎች መኖር፥

👉 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕረዚዳንት አቶ ጥላሁን ከበደ ለትውልድ አካባቢያቸው በክልሉ ካብኔ የጋራ ውሳኔ ባልተሰጠበት ለአርባምንጭ ከተማ ስታዲየም ግንባታ በሚል ከመንግሥት በጀት 500 ሚሊዮን ብር መስጠት፥

👉 በዎላይታ አረካ አቅራቢያ ለመገንባት በይፋ የተጀመረው የአውሮፕላን ማረፊያ ጉዳይ ሲሆን ተቋራጮቹ ክልሉን “በአንድ አመት አጠናቀን እናስረክባለን ከይገባኛል ነፃ አድርጉልኝ” ካሉ 5 ወር ቢያልፍም ከክልሉ እንዲሸፈን የተጠየቀው 130 ሚሊየን ብር ብቻ የካሳ ገንዘብ ቢሆንም ባለመሰጠቱ ግንባታው መቆም እና የመሳሰሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

በማጠቃለያው ከተመሰረተ በዛሬው ዕለት የተመሠረተበትን አንደኛ አመት ያከበረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም ለዎላይታ ህዝብ ያመጣው አስተዋጽኦ ምንድነው በሚል አንድ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን ስንጠይቀው “ዎላይታ ዞን ከነሐሴ እስከ ነሐሴ ስቃኝ በፖለቲካ የመደራደር አቅሙን በገዛ ልጆቹ መገፋፋት ምክንያት ለሶስተኛ ወገን በክብርና በፍጹም ፍቃደኝነት አስረክቧል” ብለዋል።

“(የዎላይታ ሕዝብ ፖለቲከኛ ሳይሆን እራሱ ፖለቲካ የሆነ ሕዝብ መሆኑ ይሰመር) በክልል በሚገኙ ቢሮዎች ዎላይታ ጠል ስርዓት እንድፈጠር በጊዜ የለኝም መንፈስ ተሰርቷል ፍሬም አፍርቷል፣ የፖለቲካ መሀንድስ የሆነው ሕዝብ ተገፍቶ በበታችነት የተጠቁ የቢሮ አመራሮችን ሰብስቧል ዎላይታ ከመጣ ከምድረ-ገጽ ትጠፋለህ የሚል ስውር ትርክት ተፈጥሯል ተግባራዊም ተደርጓል። ክልሉ አቅጣጫውን እንደሳተ መርከብ በወጀብ ተመቷል” በሚል በቁጭት ገልጸዋል።

ቀጥለውም “በማህበራዊ ዘርፍ የዎላይታ ሕዝብ ሕልውናውን የምፈታተኑ ዘርፈ ብዙ ዘመቻዎች ተደርጎበታል። “ዎላሞይ ኑና ሻሜና”፣ “ጋሞይ ኑስ አዋ፥ ኑን እንቴስ ናታ” “ጋሞ ልማቴ ኑጋ” የመሳሰሉ ስውር አጀንዳ የያዙ ንግግሮችና ተግባራት ተስተውለዋል። በአንድነት ስም የዎላይታ ሕዝብ አንገቱን እንድደፋ በማንነቱ እንድያፍር ተሰርቷል” ብለዋል።

በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ በተመለከተ “የክልሉን በጀት ከአስፈጻሚዎች እውቅና ውጪ ለአንድ አከባቢ ስተላለፍ ከመቃወም ይልቅ የጋሞ ልማት የእኛም ነው የሚል ርካሽ ተወዳጅነት ለማትረፍ መንቀሳቀስና በስልጣን ጥማት ስካር ውስጥ መመላለስ። የአመራሮቻችን ንቃት ማጣትና ፍዘት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሀብትን ማባከንና ማግበስበስ። በተቃራኒው የዎላይታ ዞን አስተባባሪ ከተግባር በላይ የፎቶ ጋጋታ፣ ምግብ ቤቶች ምረቃ ላይ ተጠምደዋል” ሲል አብራርተዋል።

የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከዚህ በፊት በሰራው ምርመራ ዘገባው “የአዲሱ ክልል ከህዝብ ፍትሃዊና ዕኩል ተጠቃሚነት አንፃር ምሁራንና የአከባቢው ነዋሪዎች ምን ይላሉ?” በሚለው አንድ የክልሉን ፓለቲካ በቅርበት የሚከታተል ምሁር “ፍትሀዊ እና ተመጣጣኝ መንግስታዊና ፖለቲካዊ ዉክልና ባለማግኘቱ አንኳር በሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ለማስገኘት እንዲሁም የልማት ፍትሃዊነት ለማስጠበቅ ግልፅ እና አሳታፍ የህግ ሥርዓት ተዘርግቶ እንድመራ መግባባት ተፈጥሮ መስራት ሲገባ በአሁኑ ወቅት ከዚያ እውነታ በተቃራኒው ተጨባጭ እንቅስቃሴ መኖሩን በመጠቆም እንዲስተካከል የሚመለከተው የፈደራል አካል ጠልቃ እንዲገባም መጠየቁ አይዘነጋም። Wolaita Times #Ethiopia