
አንድ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣን በሆቴል ተኩስ በመክፈት በሦስት ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል።
“አመራሩ በስልጣን በመባለግ በንጹሃን ዜጎች ላይ ሽጉጥ ተኩሶ አካል ቢያጎድልም፤ ጥፋቱን ለመሸፋፈን ምርመራ የጀመሩ ፖሊሶችን ማሳሰር መጀመሩ በክልሉ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት የሚጎዳ አደገኛ አዝማሚያ ነው” በሚል የፀጥታ አካላት ተነግሯል።
አቶ ዳዊት ገበየሁ የተባሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ረዳት ተጠሪና አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ባለፈው ሳምንት በዎላይታ ሶዶ ከተማ በሚገኘው አንድ ሆቴል ከመጠን በላይ ጠጥተው በመስከሩ በቦታው በመዝናናት ላይ ከነበሩ ግለሰቦች ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ እሱና ጠበቂው በንጹሃን ግለሰቦች ላይ ተኩስ በመክፈት በሦስት ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የአይን እማኝ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተዋል።
ይህንን ወንጀል ድርጊት ለማጣራት ምርመራ የጀመሩ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት እና የዎላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊሶችን “ለምን ምርመራ ጀመራችሁ፤ በማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃው እንዲሰራጭ አድርጋቸዋል” በማለት ትጥቅ አስፈትተው እስካሁን በደረቅ ፖሊስ ጣቢያ ማሳሰሩን አንድ የተጎጂ ቤተሰብ ገልጸዋል።
በተቃራኒው በጥይት የተመቱ ግለሰቦች በየቤተሰቦቻቸው ጥረት እየታከሙ ሲሆን “ለመክሰስም ሆነ መረጃውን ሚዲያ ላይ ለማውጣት የሚፈልግ አካል ካለ የማያዳግም እርምጃ እወስድባችኋለሁ” በማለት ዛቻ በመድረሱ በፍርሀት ላይ እንደሚገኙም ሌላኛው የተጎጂ ቤተሰብ አባል ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ጠቁመዋል።
የክልሉ ፓሊስ አባል እስር በተመለከተ አንድ በቅርበት የሚያውቀው ባልደረባ ሲገልፅ “የታሰረው ኮማንደር በቀድሞ ደቡብ ክልል እያለም የሕዝብ መብት እንዲከበር በቁርጠኝነት የታገለ እና ልዩ ፖሊሳዊ ጥበብ የታደለ ደፋር ፖሊስ ነበር። ነገር ግን የፓሊስ ግዴታ እንዳይወጣ የፓለቲካ ስልጣን የያዙ አካላት ለፍትህ በገለልተኝነት ሙያውን እየሰራ የነበረውን ማሳሰሩ አስነዋሪና በክልሉ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት የሚጎዳ አደገኛ አዝማሚያ ነው” በሚል አስረድተዋል።
የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉ ፓሊስ ኮምሽን አመራሮችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው ያልተሳካ ቢሆንም ምላሽ ካገኘን መረጃውን እንደምናደርስ ከወዲሁ እንገልፃለን።