
“ሆቢቻ ላይ እኛን ለመዉጋት ከኦነግ ጋር ጦር እያደራጃችሁ ነው” -አቶ መለስ ዜናዊ፤ “በዞኑ ከፍተኛ የወያኔ እና የኦነግ ደጋፊዎችና አደረጃጀት አለ” -ዶከተር ዐቢይ አህመድ፥ ለመሆኑ የዎላይታ ልህቃን፦ የትግራይ እና የኦሮሞ ልህቃን ልዩነት እንዴት ይፈታ ? ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ምላሽ አላቸው
እንደተለመደው የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ከፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ ማድረግ ልዩ ዝግጀት አሰናድተው እነሆ እንደሚከተለው አቅርቧል ተጋበዙልን🙏
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንግዳችን እንደወትሮው ጥሪያችንን ተቀብለዉ እንኳን ደህና መጡ። ያዉ ባለፈዉ እንዳሉት የሚዲያችን ቤተሰብ ስለሆኑ ቀጥታ ወደ ጥያቄ መግባት እችላለሁ ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ተፈቅዷል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ አንዳንድ ሰዎች የዎላይታ ሕዝብ በማዕከላዊ መንግስት የሚደርስበት መገፋት በተጨባጭ ከኦሮሞና ትግራይ ሊህቃን አለመስማማት ጋር ይገናኛል ይላሉ፦ እርስዎ ይሄንን ጉዳይ እንዴት ይመለከቱታል?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ ምክንያቱ ይሄ ብቻ ባይሆንም የማይናቅ ሚና እንዳለዉ ግን መካድ አይቻልም።
ከሞላ ጎደል የኦሮሞና የትግራይ ልህቃን ሁለቱም እራሳቸዉን እንደ ፈደራሊስት ይገልጻሉ። ሲተቻቹም በጅምላ ወያኔ እና ኦነግ እየተባባሉ ይዘላለፋሉ እንጂ በተጨባጭ አንዳቸዉ የሌላቸዉን ጥያቄ እና ሕልሞች በተጨባጭ ሲያጣጥሉ አይስተዋልም። አንዳቸዉ የአንዳቸዉን ጥያቄ ሲደግፉ ባይገኙ እንኳን ሲቃወሙ ማየት የተለመደ አይደለም። የሁለቱም ሊህቃን የኢፌዴሪን ሕገመንግስት ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸዉ ብቻ ሳይሆን የሰነዱን ሐቀኛ ትግበራ እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ።
መነሻ የሆነኝን የዎላይታን ጉዳይ ላንሳ፦ ህወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ሁዋላ ላይ ከዎላይታ ጋር አብሮ ከመሥራቱ በፊት ከ1983 ጀምሮ ብዙ በደሎችን አድርሷል። ብዙ የፖለቲካ ሸፍጦችን ፈጽሟል። የዚህ አንዱ መነሻ ከኦነግ ጋር ሆነዉ ዎላይታዎች ከወጉኝ ስልጣን እነጠቃለሁ የሚል ስጋት መሆኑን ከመለስ ዜናዊ አንደበት በዎጋጎዳ ትግል ጊዜ አራት ኪሎ ከተላኩ የዎላይታ ሐገር ሽማግሌዎች ጋር ሲወያዩ ካሉት ሐረግ ተነስተን ነው “በዎላይታ ሆቢቻ በረሐ ላይ እኛን ለመዉጋት ከኦነግ ጋር ጦር እያደራጃችሁ መሆኑን መረጃዉ አለኝ።” ብሎ ስጋቱን እንደማስፈራሪያ ተንፍሶ ነበረ። አሁን ደግሞ ባለዉ ብልጽግና ዉስጥ የኦሮሚያ ብልጽግና ሰዎች ብዙዎቹ ዎላይታ ለህወሓት ይወግናል ብለዉ ብዙ በደሎችን አድርሰዋል። በሌሎች ዎላይታ ሲበደል ሽፋን ከመስጠት እስከ ዝምታ ተሳትፈዋል።
በእዉነቱ ሰፋ አድርገን ስናይ የኦሮሞም ሆነ የትግራይ ሊህቃን በአብዛኛው ዎላይታ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የሥነልቦና ዝግጁነት አከርካሪና የመጋፈጥ አቅም ያለዉ ሕዝብ መሆኑን ከማወቅ አልፈዉ ሕዝቡን ይወዳሉ። አንዳች ቁምነገር ማድረግ እንደሚችልም ያዉቃሉ። በአንጻራዊነት ካየነዉ የዎላይታን ጉዳይ ከሶስቱ ብሄሮች አተካራ ዉጪ እንደአንድ ሁነኛ የፖለቲካ ማህበረሰብ የራሱን ጡብ በሐገር ግምባታ ላይ እንደሚያኖር የሚተማመኑና ለሕዝቡም የሚቆረቆሩ ቁጥራቸዉ ቀላል አይደለም።
በተናጠል ዎላይታን ቢወዱም አንዳቸዉ ለሌላቸዉ የበለጠ ቦታ ይሰጣሉ እያሉ ዎላይታን ሲከሱም ይስተዋላል። ፕሮፌሰር ሕዝቄል ገቢሳ በቄሮ ትግል ጊዜ “ዎላይታዎች ለኦሮሞ ሕዝብ እንቅፋት ናቸዉ።” ብሎ ከሱ የማይጠበቅ ነገር ማለቱን ሰምቻለሁ ከሰዎች። ይህ ግን ሜጫና ቱለማን ከኦሮሞ ጋር የመሠረቱ ዎላይታዎችን ታሪክ የዘነጋ ነው። በኃይለስላሴ ጊዜ በኤርትራ ነጻ አዉጪ ድርጅት ሲመሠረት ኦሮሞና ዎላይታ ታፍሰዉ መታሰራቸዉን የዘነጋ ነዉ። የፍስሐ ደስታ ጦና የ40 ጅራፍ ግርፋት በጋራ ትግል መክሸፉን የዘነጋ ነዉ።
አሁንም በቄሮ ትግል ወቅት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አመጹን በወታደራዊ እርምጃ ከማቆም ይልቅ ፖለቲካዊ እርምጃን ማስቀደማቸዉ ለኦሮሞ ታዳላላችሁ የሚሉ የትግራይ ሊህቃንን አሳይቶናል። በቀጥታ ግን ከትግራይም ሆነ ከኦሮሞ ትጠሉናላቹ የሚል የለም። ኦሮሞ እንደጭቁን ብሄርነቱ ከዎላይታ ጋር ሰፊ የጭቆናን ታሪክ ይጋራል። ያም ደግሞ የሕዝቦቹን ፍላጎት አጋምዷል። ትግራይ ደግሞ እንደ ሕዝብ ቁጥሯ አነስተኛነት የዎላይታ አይነት ጠንካራ ፈደራሊስት ally ትፈልጋለች። ከዛ ባለፈ የትግራይ ሕዝብ የጭቆናዉ አይነት ይለያይ እንጂ እንደኛው ጭቁን ነው።
ኦሮሞም ቢሆን ፕሮፈሰር መረራ እንደሚሉት ቁጥሩ ብዙ ሆኖ እያለ እኩል እንሁን ሲል የኖረ ጭቁን ሕዝብ ነዉ። በእርግጠኝነት መናገር የምንችለዉ የኦሮሞና የትግራይ ሊህቃን ልዩነት የስልጣን ክፍፍል ነው እንጂ የመጨፈላለቅ እና የመዋዋጥ ፍላጎት አይደለም። ይህ የዎላይታን ሕዝብ እየጎዳ ነው ያልነዉ ልዩነት ሁለቱንም ሕዝቦች ጎድቷል፤ መፍትሔ ካልተበጀ ጉዳቱ ይቀጥላል። ድክመቱ ደግሞ የኦሮሞና የትግራይ ሊህቃን ነው። ከቂም በቀል በመዉጣት ተቀራርበዉ መነጋገር አለባቸው። ስለራሳቸዉ ሌሎችን ለመጉዳት መሆን የለበትም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በተጨባጭ ዎላይታን በዚህ ደረጃ በየጊዜዉ ሁለቱም ለእገሌ ከእኔ የበለጠ ትቀርባለህ ብለዉ እንዲጠምዱ ያደረጉ ምክንያቶች ምን ይመስልዎታል?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ ሁለቱም የዎላይታ ሕዝብ ያለዉ የራስገዝነት የረዥም ጊዜ ታሪክ እና ያ የሚፈጥረዉ አቅም ይረዳሉ። ከፖለቲካ ፍላጎት መቀራረብ ጋር በተያያዘ ከሁለቱም ጋር በቀላሉ ሊግባባና አብሮ ሊሰራ እንደሚችል ሁለቱም በተናጠል ይገነዘባሉ።
ሌላዉ ከስነልቦናዉ በየዘርፉ ካለ የትምህርት ዝግጅት እና ከመከላከያ ከፍተኛ ተሳትፎ እና በኢህአዴግ መጀመሪያም ሆነ በብልጽግና መጀመሪያ አመታት ላይ የተቀነሰ በርካታ ከፍተኛ የዉጊያ ልምድና ከፍተኛ ዉጊያን የመቋቋም አቅም ያለዉ ተሰናባች ሠራዊት መኖሩ ነው።
ሌላዉ የጸረ ጭቆና ትግል ታሪኮችና የሕዝቡ የፖለቲካ ንቃተ ሕሊና መዳበር እንዲሁም ለፈደራል ሥርአቱ ያለዉ ቀናኢነት ለቋንቋና ባህሉ ያለዉ ቀናኢነት ተደምሮ የዎላይታ በክልልም ሆነ በሐገር ደረጃ የሚያገኘዉ ቁልፍ ስልጣን በኃይል አስተላለፍ ለዉጥ ደረጃ የሚታይ በመሆኑ ነው።
ሁለቱም ያኔም ሆነ አሁን በራሳቸዉ ዎላይታን እንደጠላት በቀጥታ አይፈርጁም ግን የሁለቱ ልዩነት ላይ ጥግ ከያዘ የኃይል ሚዛኑ ይዛባል የሚል የተናጠል ስጋት የነበራቸዉና ያላቸዉ ይመስለኛል። ሁለቱም ከሌሎች ኃይሎች ጋር ተጣምረዉ አንዳቸዉ ሌላቸዉ ላይ ከባድ ጉዳት ለማድረስ ሲንደረደሩ ስለማንተባበራቸዉ ቀድመዉ ይገፉናል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ የዎላይታ ልህቃን ይህ በተደጋጋሚ የዎላይታ ሕዝብ እንዲገፋ የሚያደርግ የትግራይ እና የኦሮሞ ልህቃን ልዩነት ሕዝቡን እንዳይጎዳ ምን ማድረግ አለባቸዉ?
✅ ፕሮፈሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በእዉነቱ በዋናነት በፈደራል ሥርዓቱ የሚምሉና የሚገዘቱት የኦሮሞና የትግራይ ሊህቃን ለራሳቸዉ ሕዝብ ብለዉ ሊያስቡበት ይገባል።
የዎላይታ ልህቃን እኛ ማንንም ጠልፎ የመጣል እቅድ እንደሌለንና የሕዝባችንን ጥቅምና መብት በፌዴሬሽኑ ዉስጥ የማስጠበቅ እቅድ ብቻ እንዳለን ማስገንዘብ አለብን። ፖለቲካችንም ሆነ ሚዲያው በዚህ ቅኝት መሥራት አለበት። እኛንም መብትና ጥቅማችን በሕገመንግስቱ መሠረት እንጂ የኦሮሞም ሆነ የትግራይ ልህቃን በሚሰጡን ችሮታ መጠበቅ ስለሌለበት ለመብታችን በነጻነት መታገል አለብን። በእዉነቱ በሌሎች ጸብ መቀጣታችንን በጸጋ መቀበል የለብንም።
💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረበ የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።