
የቁጫ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ ዎዳላ ጋዜ በዓል በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ ተገልጿል።
የቁጫ ብሄረሰብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኝ ብሄረሰብና ከሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንዱ ከሆነው ከኦሞዓዊ ቋንቋ ቤተሰብ የሚመደብ ሲሆን የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያለው እንዲሁም የተለያዪ ባህሎች እና ስርአቶች ከጥንት ጀምሮ ያሉት እንደሆነ የታሪክ አዋቂዎችና ሰነዶች ያረጋግጣሉ።

በዎዳላ ጋዜ በዓል ወቅት ከቅድመ ዝግጅት ጊዜ ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍፃሜ ድረስ ብዙ ሂደቶች ያሉት ሆኖ ለምሳሌ የባህላዊ ምግብና መጠጥ ዝግጅት፣ የሀብት አሰባሰብ፣ የእርቅና የይቅር መባባል፣ ለሌለው ማካፈል፣ ወዘተ መርሃ ግብሮች በዎዳላ ጋዜ ወቅት የሚከናወኑ ተግባራት ሲሆኑ ከዚህ በተለየ አንዱና የበዓሉ ዋና ተግባር ተደርጎ የሚወሰደው አዲሱ ዓመት ከመግባቱ በፊት ያዘነን ቤተሰብ የማፅናናት ሥርዓት መኖሩ እንደሆነ ይገለጻል።
በዚህ ሥርዓት መሠረት በአሮጌ ዓመት መጀመሪያ፣ መሃል ወይም መጨረሻ ላይም ይሁን ብቻ ከቤተሰቡ ሰው የሞተበት ሰው በሰፈሩ ካለ ለቅሶ በአዲስ መልክ ይደረስና ያ ቤተሰብ ዳግም ሀዘን ውስጥ እንዳይገባና የነበረበትን የሀዘን ድባብ በጭራሽ እንዲረሳ የሚደረግበት ሥርዓት ነው።


ይህ የዎዳላ ጋዜ በዓል የቁጫ ሕዝብ እንደ ሕዝብ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሲያከብረው የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደብዘዝ የማለትና እንደቀደሙት ጊዜያት ያለመከበር ሁኔታ ላይ የነበረ ቢሆንም ከ2013 ጀምሮ ግን በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ እንደሚገኝ ተገልጿል።
“ዎዳላ ጋዜ” የተሰኘው የቁጫ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል አምና ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ እንግዶች፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ የተለያዩ ብሔርና ብሔረሰቦች ተወካዮችና የቁጫ ብሄረሰብ ተወላጆች በተገኙበት በአዲስአበባ በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት የተከበረ ሲሆን የዘንድሮውን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ አስተባባሪ ኮሚቴ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የላከው መረጃ ያመለክታል። #Ethiopia