1727630626273

ዳሞታ በዎላይታ ትልቁ ተራራ ቢሆንም፤ በርግጥ ተራራ ብቻ አይደለም። ከተራራ በብዙ ይልቃል። እጅግ አስደናቂ ታሪክ፤ የማይጠገብ ውበት፤ “የታላቅነታችን መለያ፤ የኩራታችን ምንጭ፤ የማንነታችን መገኛና የጀግንነታችን ምልክት ነው” የምለውን የህዝቡን ታሪክ ያረጋግጣል።

ለበርካታ ክፍለ ዘመናት፤ በተጠቀጠቀ ሀገር በቀል ዛፎች አሸብርቆ፤ ቁጥር ስፍር ለሌላቸው አእዋፋትና የዱር አራዊት መኖሪያ በመሆን፤ ከታች ወደ ላይ አንጋጦ ለሚመለከተው የዎላይታ ሶዶ ከተማ ንጹሑ አየር እየለገሰ፤ ከሰባት ላላነሱ ትላልቅ ወንዞች መነሻ መሰረት የሆነው ዳሞታ ተራራ ብቻ አይደለም ስንል እልፍ ምክንያት አለን!

አዎ.. ዳሞታ ተራራ ብቻ አይደለም!

አባቶቻችን እነ ካዎ ጦና፤ አድዋ ላይ ጣሊያንን ድባቅ ለመምታት፤ የጦር ስትራቴጂ የነደፉት ዳሞታ ግርጌ ነበር። ከ18,000 በላይ የሚሆን የዎላይታ ጦር ጣሊያንን ለመግጠም ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እንደ ንብ የተመሙት ዳሞታ ግርጌ ተሰባስበው ነበር።

ዚአድባሬ ኢትዮጵያን ሲወራት ኢትዮጵያችንን ለመመከት ካራማራ ግንባር ላይ አጥንታቸውን የከሰከሱ የዎላይታ ጀግኖችና በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ባድሜና ናቅፋ ላይ ደማቸውን ያፈሰሱ የዎላይታ ቆራጦች፥ ቤተሰቦቻቸውን የተሰናበቷቸው ዳሞታ ግርጌ ስር ነበር።

ለዚህ ነው… ዳሞታ ከተራራ በላይ ነው የምንለው። ከደምስራችን የተቆራኘ የታሪካችን ደማቅ አሻራ፤ የስንቃሎቻችንና የሙዚቃችን ልዩ ተወዳሽ.. በዋናነት ደግሞ፥ የታላቁ ንጉሳችን የካዎ ሳሶ ሞቶሎሚ የንግስና መናገሻ!

የዳሞት ስረወ መንግስት ንጉስ በመባል የሚታወቀው ካዎ ሳሶ ሞቶሎሚ፤ ጀግንነቱ የማይዋጥላቸው አንዳንዶች “እንቡዝ” በማለት ሊያጥላሉት ቢሞክሩም፤ ካዎ ሳሶ ሞቶሎሚ ግን፥ በወቅቱ (በ12ኛው መቶ ዓመት ገደማ የነበሩ) የስካንዲቪያ #vikingsን ጨምሮ በመላው አፍሪቃ ውስጥ ያሉ ነገስታት እጅ የሚነሱለት የነገስታት ውሃልክ፤ እጅግም የተፈራ ንጉሰ ነገስት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት በሚገባ ከትበውታል። ይኼውም ንጉስ በዎላይታ ከነበሩት ሦስት መናገሻ ቤተመንግስቶቹ አንደኛው ያለው ዳሞታ ተራራ ላይ ነው። መናገሻውም፥ በዎላይትኛ “ጣዛ ጋሩዋ” (xazaa garuwa) ይባላል።

ዳሞታ ሲወሳ “ጦሳ ፔንጊያ”ን ማንሳት ይኖርብናል..

ስለ “ጦሳ ፔንጊያ” ሲነሳ ብዙ መቶ ዓመታትን ታሪክ የኋሊት እንድንጓዝ ያስገድደንና በኦርቶዶክስ ሐይማኖት ዘንድ እጅግ ትልቅ ቦታ ካላቸው ከአቡነ ተክለሃይማኖት ጋር ያገናኘናል። አቡነ ተክለሃይማኖት በ12ኛው ክፍለ ዘመን በዳሞታ ተራራ አናት ላይ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በተደጋጋሚ የሚመላለሱበት መንገድ ላይ የሚገኝና ዘወትር ሲደክማቸው አረፍ የሚሉበት ስፍራ “ጦሳ ፔንጊያ” እንደተባለ ይታመናል፡፡ የስፍራው ቀጥተኛ ትርጉም ”የእግዜር መተላለፊያ” የሚል ነው።

አሁን ደግሞ ዳሞታ.. ጉዞ ሞቼና ቦራጎ ዋሻ

የዛሬ 300,000 ዓመት ገደማ አዳዲስ አይነት የድንጋይ መሳሪያዎችን በአፍሪካ መስራት ተጀመረ፡፡ ይህ ልዩ የሆነው አዲሱ አይነት የድንጋይ መሳሪያ የታየበት ጊዜ ‹‹የመካከለኛው የድንጋይ ዘመን›› በመባል ይታወቃል። በዚህ ዘመን የተሰሩት የድንጋይ መሳሪያዎች ቀደም ባለው ጊዜ ከነበረውና ‹‹አሹሊያን›› በመባል ይታወቅ ከነበረው ዘመን ይልቅ አይነታቸው የበዛ ነበር።

በመካከለኛው የድንጋይ ዘመን የተሰሩ የድንጋይ መሳሪያዎች የዓይነታቸው መብዛት ምክንያቱ በወቅቱ የተለያዩ ቁሳዊ ባህሎች የነበሩ ለመሆኑ ይታሰባል፡፡ በድንጋይ መሳሪያዎች አይነቶች ውስጥ ልዩነቶች ቢኖሩም ሁሉም የድንጋይ መሳሪያዎች የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ነበሩ። እነዚህም መመሳሰሎች ሁሉም ‹‹ለቫሉዋ›› እየተባለ በሚጠራው ዘዴ በመጠቀም ሰራተኛዉ የመሳሪያውን ቅርፅ አስቀድሞ የሚወስንበትና ለመውጋት የሚያስችል ሹል ቅርፅ ያላቸው መሆናቸው ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ የተገኙት የመካከለኛው የድንጋይ ዘመን መካነ ቅርሶች በውስጣቸው የተገኙት ቅርሶች ጥንታዊው ሰው የቀደምት መንፈሳዊ መሰል ስርዓት ያከናውን እንደነበር ያሳያሉ፡፡ እነዚህ ቅርሶች ሰውነትን ለማስዋብ አገልግሎት የዋሉ ለምሳሌም አንደ ዶቃ ያገለግሉ የነበር እንቁላል ቅርፊት፣ ሰውነትን ለመቀባት የሚውል ቀለም ያለው ድንጋይ የተፈጨበት ድንጋይ እና በእንቁላል ቅርፊት ላይ የተገኙ የመቦርቦር ምልክቶችን ይይዛሉ፡፡

አነዚህ የደቡብ አፍሪካ መካነ ቅርሶች በተጨማሪም የጥንቱ ሰው የተለያየ አይነት ምግቦች ይመገብ እንደነበር ያሳያሉ፡፡ አንዲሁም የድንጋይ መሳሪያዎችን ከእንጨት ጋር በማዋደድ ያድኑ እንደነበርና ከአጥንት የተሰሩ መሳሪያዎችንም ይሰሩ አንደነበር ያሳያሉ፡፡

በምስራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያው የዳሞታ መካነ ቅርስና በኬንያ የሚገኘው የካፕቴሪን መካነ ቅርስ በአለም እጅግ እረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ የመካከለኛው የድንጋይ ዘመን ቴክኖሎጂ የተገኘባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙት የፓርክ ኤፒክ ዋሻ (ድሬዳዋ) እና #ሞቼቦራጎዋሻ (ዎላይታ) የመካከለኛው የድንጋይ ዘመን ሰዎች ለረጅም ጊዜ ኖረውባቸዋል። ከዳሞታ የተገኙት ሹል የድንጋይ መሳሪያዎች የጥንቴ ሰው ከእንጨት ጋር አዋዶ እንደ ጦር እንደ ተጠቀመባቸው የሚጠቁም የአለማችንን ጥንታዊውን የመካከለኛውን የድንጋይ ዘመን መረጃ ሰጥተዋል።

‹‹ሆሞ ሳፒያንስ›› የተባለው የአሁኑ የሰው ዘር የተነሳበትና ወደ አለም የተበተነበት ቦታ ኢትዮጵያ በመሆኑ የኢትዮጵያ የመካከለኛው የድንጋይ ዘመን መካነ ቅርሶች ልዩ ትኩረትን ይስባሉ፡፡

ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከአስተባባሪዎች የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው መስከረም 26/2017 ዓ.ም የአፍሪካ ኩራት ወደሆነው ወደ ሞቼና ቦራጎ ዋሻ (ዳሞታ ተራራ) ለሚደረገው ጉዞ ተዘጋጅቷል።

የጉዞው ቲሸርት እየተሸጠ ሲሆን፤ የሚገኝባቸውም ቦታዎች፦ በዎላይታ ሶዶ ከተማ 👇

👉 Downtown Cafe & restaurant
👉 Roadhouse Cafe & restaurant
👉 BossYoss Tour & Travel office

መስከረም 26/2017 አብረን ይህንን የአሁኑ ሰዉ ዘር የተነሳበትን እና ወደ አለም የተበተነበትን ታሪካዊ ዋሻ ለመጎብኘትና ኩነቱን ለተቀረዉ ዓለም ለማሳወቅ በሚደረገው ጉዞ አካል እንሁን ይላሉ አስተባባሪዎቹ🙏 Wolaita Times