በሀገሪቱ ለሁሉም የሚፈቀድ ባንክና በከተማ ዋና ጎዳናዎች የሚገነቡ የጀግኖች መታሰቢያ ሀውልቶች በዎላይታ ለምን ተከለከሉ? ጥያቄ ቀጥሏል።
በአከባቢው ዘርፍብዙ ጠቀሜታ አለው ተብሎ ተጠንቶ “ዳሞታ” በሚል ስያሜ ላለፉት አራት ዓመታት ገደማ የምስረታ አክሲዮኖች ሽያጭ ሲያከናውን የቆየው ባንክ፤ የማደራጀት ሂደቱ ተቋርጦ መፍረሱን የአደራጅ ኮሚቴው እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቀው ነበር።

ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ባለው መረጃ መሠረት የዳሞታ ባንክ የአክሲዮን ማህበር በማቋቋም የአዲስ ባንክ ምስረታ እንቅስቃሴውን የጀመረው በጥቅምት 2013 ዓ.ም ሲሆን የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ በወቅቱ ለብሔራዊ ባንክ በጻፈው ደብዳቤ፤ የፋይናንስ ተቋሙን ለማደራጀት የሚያስችሉ ዝግ የባንክ ሂሳቦችን ለመክፈት ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት አግኝተው ነበር።
የዳሞታ ባንክ በወቅቱ በስራ ላይ በነበሩ 17 ባንኮች የአክሲዮን ሽያጭ ለማከናወን በአዲስ አበባ እና ዎላይታ ሶዶ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቶችን ከፍቶ ሲንቀሳቀስና ሲሸጥ የነበረ ቢሆንም የማደራጀት ሂደቱ ተቋርጦ መፍረሱን የአደራጅ ኮሚቴው እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማስታወቁን ተከትሎ በበርካቶች ዘንድ ጥያቄ ፈጥሯዋል።
ሌላኛው ጉዳይ በተመሳሳይ ደግሞ ልክ በዚያን ዳሞታ ባንክ ምስረታ ወቅት ከህዝብ ጥያቄ መነሻ በብዙ ጥናቶች ላይ ተመርኩዞ በዎላይታ ታሪክ ትልቅ አስተዎፅኦ ላበረከቱ መሪዎች ማለትም ለንጉስ ሞቶሎሚ፣ ለንጉስ ጦና እና ለክቡር አቶ ፍሬው አልታዬ መታሰቢያ የሚሆን ሐውልት በዎላይታ ሶዶ ከተማ እንዲሠራ መወሰኑ ተወስኖ ወደ ተግባር መገባቱ ይታወቃል።

ይሄው ከ4 ዓመት በፊት በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ለመገንባት ሁሉም ነገር ተጠናቅቆ ከተገመተው ግንባታ ወጪ ከግማሽ በላይ ተከፍሎ ግንባታ ከጀምሩ በኃላ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ቆም ቀርቷል።
የጀግኖች መታሰቢያ ሐውልት ሥራ ጨረታውን ያሸነፉ ጉራማይኔ የስነ ጥበብ ማዕከልና ተስፋዬ ገብሬ የቅርፅና የስዕል ስራ ድርጅት “በተደጋጋሚ ሥራውን ለመጨረስ በአካልና በደብዳቤ ብንጠይቅም ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም” ብሏል።
ድርጅቶቹ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ባሉበት ቦታ ሥራቸውን አስገምግሞ ወደ መትከሉ ለመግባት ተዘጋጅቶ ቢጠባበቁም ምክንያቱ ባልታወቀ መልኩ ሥራው መሃል ላይ ሊቆም ችሏል።
“በተደጋጋሚ በደብዳቤና በአካል ቀርቦ ቢያሳውቁም ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም” የሚሉት ድርጅቱ አሁንም ሐውልቶችን ለመስራት ዝግጁ ነን፣ የሚመለከተውን አካል ምላሽ እየተጠባበቅን ነው” በማለት ጉዳዩን ይገልፃሉ።
በየትኛውም አከባቢ በህዝብ ዘንድ የሚወደዱና በጎ ተፅዕኖ ሰርተው ያለፉትን በአደባባይ መታሰቢያ አድርጎ መገንባት ታሪክን ለትውልድ ጠብቆ ለማቆየት እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ታሪክ ከማስተላለፍ ከታሪካዊ ፋይዳቸው በተጨማሪ ለቱሪዝም ፍሰትና ገቢ እንዲሁም ለከተማው ውበትና ምልክት ሆኖ ማራኪ እይታ በመስጠት ከፍ ያለ ሚና ይጫወታል፡፡
የአከባቢው ተወላጆች በጉዳዩ ዙሪያ ሀሳብ ሲሰጡ “አከባቢውን ለመጎብኘት ብሎም በአጋጣሚ የመጣ ሰው ሁል ጊዜ የሚጠይቀው የዎላይታ ነገስታት ቤተመንግስትና ሐውልታቸው የት ነው? የሚል ነው፡፡ ታዲያ ምን እናሳይ? ምንስ እንበል?
ጅማ ሲንሄድ የአባ ጅፋርን፣ ጎንደር የአፄ ቴዎድሮስን፣ ሸዋ ላይ የአፄ ምንልክን፣ ሐረር ላይ የአቡዱላሂን፣ ትግራይ ላይ የአፄ ዮሐንስን፣ ከፋ ላይ ጋኪ ሻሬቾን ተመልክተን መጥተን ወደ እኛ ሲመጡ ምን እናሳያቸው? ምን እንበላቸው? ለልጆቻችንስ ምን እናውርስ? በሚል ይጠይቃሉ።

ለመሆኑ “በሀገሪቱ ለሁሉም አከባቢ የሚፈቀድ ባንክና በከተማ ዋና ጎዳናዎች የሚገነቡ የጀግኖች መታሰቢያ ሀውልቶች በዎላይታ ለምን ተከለከሉ?” የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ሆኖ ዘልቋል።
ነገር ግን በተለይም ከ50% በላይ ክፍያ ተፈፅሞ በመሀል ባለቤት አጥተው የቆመው የጀግኖች መታሰቢያ ሀውልቶች ግንባታ የቆመበት ምክንያት በገንዘብ እጥረት ከሆነ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የአላማው ደጋፊ የሆኑ በርካቶችን በማስተባበር ቀሪ የግንባታ ወጪ ለመሸፈን ዝግጁ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን። #Ethiopia #Wolaita #Sodotown
በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው