“በኢትዮጵያ ነባር ሚዲያዎች ለጭቁን ሕዝቦች ጥላቻ ስላላቸው ለጉዳያቸው ትኩረት አይሰጡም”፣ “በትግራይ ጦርነት እናትና ልጅ ሚዲያም ዘምተዋል። አሁን ቅኝቱ ተቀይሯል”፣ “የመንግስት አፈናም የሚዲያዎች ሥርዓት አልበኝነት መቀነስ አለበት” ለምን ? ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ምላሽ አላቸው 👇

እንደተለመደው የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ከፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ ማድረግ ልዩ ዝግጀት አሰናድተው እነሆ እንደሚከተለው አቅርቧል ተጋበዙልን🙏
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንግዳችን እንደወትሮው ጥሪያችንን ተቀብለዉ እንኳን ደህና መጡ። ያዉ ባለፈዉ እንዳሉት የሚዲያችን ቤተሰብ ስለሆኑ ቀጥታ ወደ ጥያቄ መግባት እችላለሁ ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ተፈቅዷል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ዛሬ ስለ ሚዲያዎች እናወራለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ደስ ይለኛል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ለመግቢያ ያክል ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ያሉት የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ከፈደራል ሥርዓቱ እና ከሐገረ መንግስት ግምባታ አንጻር የነበራቸዉ ሚና ምን እንደሚመስል በአጭሩ ቢያስቀምጡልን?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በአጭሩ ማለትህ በጀ እንጂ ይህ በጣም ሰፊ ጥያቄ ነው። በዋናነት የፈደራል መንግስት ብቸኛ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በብሔራዊ ሚዲያዎች ከመጀመሪያ ጀምሮ አማርኛ ቋንቋ የበለጠ ቦታ አግኝቷል። በመንግስትም በግልም። የመንግስት ሚዲያዎች በቀጥታ የኢህአዴግ ልሳን ነበሩ ማለት ይቻላል።
በግሉም ዘርፍ የተቃዋሚ ልሳን የነበሩ አለ። በሕትመትም ሆነ በኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሚዲያዎች መደበኛ የመንግስትን እንቅስቃሴ ከመዘገብ ባለፈ ጥልቀት ያለዉ ነገር የማይሰሩ ከባለሙያነት በላይ ካድሬነት የሚንጸባረቅባቸው ናቸዉ ማለት ይቻላል።
ነገር ግን ደግሞ አንድ መዘንጋት የሌለብን አወቃቀራቸዉ ከድሮ ሥርዓቶች ብዙ የተለዬ አይደለም። የተወሰነ የተሻሻለ ነገር በተዋጽኦ ረገድ ቢኖርም አመራሩና ነባሩ የሐገሪቷ የሚዲያ ቅኝት አንቀዉ የያዙት ነው።
“ነጻዉ ፕረስ” የሚባለዉ የግል የሕትመት ሚዲያ የደርግን የፕሮፖጋንዳ መስመር መልክ ቀይሮ እንደ አሸን የፈላበት ነው። ቅኝታቸዉ የፈደራል ስርዓቱን መጥላት፥ የብሔር መስመር ላይ ያለዉን አመራር በጅምላ ያለ ችሎታ በኮታ የሚመጡ አድርጎ መፈረጅ በህወሓት አስታኮ የትግራይ ሕዝብ ላይ ጥላቻ መቀስቀስ፣ የዘዉድና የደርግ ናፋቂነትን በስዉር ማቀንቀን ነበረ።
መንግስታዊ ሚዲያዎች ደግሞ እነኝህን እንቅስቃሴዎች መከላከል በሚገባቸዉ ልክ ካለመከላከላቸዉም በተጨማሪ የተወሰኑ ጽንፈኛ ጋዜጠኞች በማሰር መንግስት ስማቸዉ እንዲገን ያደርግ ነበረ። በሐቀኝነት የፈደራል ሥርአቱን እሴቶች ተቀብሎ የሚሰራ የግል ሚዲያ ነበረ ማለት አይቻል። የተወሰኑ ቢኖሩም ከመንግሥት ጋር ያላቸዉ ሽርክና ስለሚታወቅ ተአማኒነትና ተቀባይነታቸዉ የተገደበ ነው የነበረዉ።
በርግጥ የነበረዉም ሁኔታ ምቹ አልነበረም፥ የተወሰነ ሚዛናዊ ነገር ለመስራት የሚሞክሩ ጫናዉ ስለሚበዛባቸዉ አይዘልቁም፦ ካልሆነ በጣም ለዘብተኛ ሆነዉ በፍርሃት ይሰሩ ነበረ። እኔ ግምገማዬ መንግስትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ሕገመንግሥቱ መሠረት አድርገዉ ለሐገር ግምባታ የተጫወቱት ሚና አፍራሽነቱ ይጎላል ባይ ነኝ። በተለይ ዘግይተዉ ከዉጭ ሐገራት መሰራጨት የጀመሩ ሚዲያዎች በጣም አፍራሽ ሚና የተጫወቱ ይመስለኛል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ከለዉጡ በሁዋላስ?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ በርግጥ ከለዉጡ በሁዋላ በሩ ለሁሉም ተከፍቶ ነበር። በተለይ ከዉጪ የመጡ ና በሐገር ዉስጥ ኢሳት፣ አስራት፣ ድምጸ ዎያኔና OMN ከፍተኛ አፍራሽ ሚና ነበራቸዉ። የመንግስት ክልል ሚዲያዎችም ወደነሱ ወሰድ መለስ ያደርጋቸዉ ነበረ። በርግጥ በሚዲያዎቹ የሚንጸባረቀዉም ሐገሪቷን የሚንጣት የሐገረመንግስት ግምባታ አቅጣጫ አለመስማማት ነው። የመንግስት ግልጽ አፈና ቢታይም ሚዲያዎችም ከፍተኛ ከሙያ ስነምግባር ያፈነገጠ ዉምብድና ይፈጽሙ ነበር። Amateurishness በጣም ያጠቃቸዉ ይበዛሉ ሚዲያና ጋዜጠኞችም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ አሁን ላይ የተስፋፋዉ የማህበራዊ ሚዲያስ ?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ እሱ የባሰ ይመስለኛል፥ ግን የተደበላለቀ ነው። ከዉጪም ከሐገር ዉስጥም ጥሩ ጥረቶችን የሚያደርጉ አሉ ከነችግራቸዉም ግን የፖለቲካዉ አለመረጋጋት ጥላ አጥልቶባቸዋል። በሐገሪቷ የተካሄዱ እና እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶች በጣም ከመሥመር ወጥተዉ በጥላቻ እንዲነከሩ አድርገዋቸዋል።
በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ጥሩ ጅምር አሳይተዉ የጠፉም አሉ።
ለምሳሌ Ubuntu ሚዲያ በጣም ጥሩ ጀምሮ ተበታትኗል፣ እነ ታጁራ የተሰደዱበት። ያንተም ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በአካባቢው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ነበረ፥ ሁኔታዉ ስለማይመች ነው ስደቱ የመጣዉ። በአጠቃላይ both main stream and social media የሐገሪቷ የፖለቲካ ችግር ተጭኖት የሙያ ሥነምግባር ጎድሎት ብዙ ጋዜጠኞች ተሰድደዉበት ተዳክሞ ያለ ይመስለኛል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በፈደራልም ሆነ በክልል የሚገኙ የመንግስት ሚዲያዎች ሚናቸዉ ምን መሆን ያለበት ይመስለሃል?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ እነሱ ሕገመንግሥቱን ተከትለዉ በሙያ ሥነምግባር የታነጸ የሕዝብን ድምጽ እያሰሙ ገንቢ ሚና መጫወት ነበረባቸዉ። ነገር ግን ፍጹም የካድሬ መፈንጫ የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚ ሆነዉ ከርመዋል።
በተለይም በትግራይ ጦርነት ጊዜ በሽብርተኝነት ደረጃ የሚገለጽ ሚና ተጫዉተዋል። የክልሎቹም በጥብቅ ጫና ሥር ሆነዉ እንደሚሰሩ ይታወቃል። የኢትዮጽያ ቴሌቪዥን በዎላይታ ሕዝበ ዉሳኔ ላይ ዉጤት የሚያዛባ ዘገባ በዋዜማዉ መሥራቱ ይታወሳል። ሚዲያዉ የፖለቲከኞች መጫወቻ መሆኑ ግልጽ ነዉ።
እኔ የበለጠ ተስፋ የማደርገዉ ሕገመንግሥቱን የሚያከብር፣ ሚዛናዊ የሆነ ሐገራዊ፣ የግል፣ Main Stream ሚዲያ እንዲፈጠሩና እንዲያድጉ ነው። ያኔ የመንግስቶቹም ይሻሻላሉ፥ በዋናነት ግን አሁን ላይ የሰላምና የፖለቲካዉ ሁኔታ ካልተሻሻለ ብዙ ተስፋ አይታየኝም።
በፖለቲካ ኃይሎች መሐል በሐገረመንግስት ግምባታ አቅጣጫ ላይ ያለዉ አለመስማማት በከፍተኛ ሁኔታ ከፋፋይ ሆኖ በሚዲያዎች እየተንጸባረቀ ነው። ሕዝቡ የበለጠ እየተከፋፈለ ነው በሚዲያዎች ምክንያት። የመንግስት ሚዲያዎች ከኢህአዴግ እስከ ብልጽግናም ለሕገመንግስታዊ ሥርዓቱ ታማኝ አይደሉም። ለዚህ ምክንያቱ የፖለቲካ ፈቃደኝነትና የሚዲያዎቹ አወቃቀርና ተዋጽኦ ይመስለኛል።
በፍልስፍናም ደረጃ መንግስት ሚዲያ በባለቤትነት እንዳይይዝ የሚሉ ሰዎች ቢኖሩም እኔ ሐሳባቸዉን አልገዛምና አስፈላጊነታቸዉን አምንበታለሁ። በተለይ በሐገራችን ቦርዶቻቸዉ የበለጠ አካታች ቢሆን ባይ ነኝ። በግልም በመንግስትም በኩል በተቻለ መጠን ነጻ እና ገለልተኛ የሆነ ጠንካራ ሚዲያ ባለመኖሩ የመንግስቶቹ ተአማኒነት በማጣት የግሎቹ ደግሞ ሕዝቡ ስለ ሐገሪቷ ችግር ሙሉ ምስል እንዳይኖረዉና በአንዳንድ ሕዝቦች ላይ ጥላቻ እንዲያሳድሩ እየሆነ ነዉና አሳሳቢ ነው።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ አሁን ያለዉ መፋጠጥ፣ መፈራረጅ፣ መጠላላት፣ ዉግንና ከፖለቲካዉ ወደ ሚዲያ የመጣ ነው ወይስ ከሚዲያ ወደ ፖለቲካ የመጣ ነው?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ ተወራራሽ ይመስለኛል፥ ፖለቲካ ቢመራዉም። ያዉ የአዲስ አበባ ኤፍ.ኤም ረዲዮችን እንዲሁም አንዳንድ የግል ቴሌብዥኖች፣ በተወሰነ ደረጃ የመንግስት ሚዲያዎችም በግልጽም ሆነ በዘዴ የቀኝ አክራሪ ኃይሎች ጋር የፍላጎት አንድነት እንዳላቸዉ ይታወቃል፥ ያ ሕዝቡ ላይ የሚያሳድረዉ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም።
በትንሹ በትግራይ ጦርነት ላይ እናትና ልጅ ተሰብስበዉ ዘምተዋል። አሁን አማራ ክልል ላይ ተመሳሳይ ነገር አይታይም። ያ የሚነግረን ነገር አለ። በኦሮሚያ ወይንም ሌላ አካባቢም ግጭት ቢፈጠር የአዘጋገባቸዉ ቅኝት እንደሚቀየር እሙን ነው። ይህችን እዉነት ማወቅና በሕገመንግስቱ የሚያምን ጠንካራ የግል ሚዲያ ያስፈልጋል፤ ሁሉንም ሕዝብ ወገኔ የሚል ሚዲያ።
ነባሮቹ ሚዲያዎች በአብዛኛው ወገንተኛ ካልሆነም በሕዝብ ጉዳይ ለዘብተኛ ናቸዉ። ሚዲያው በ27 ዓመት ጎልተዉ ከወጡት ተግባራት የጭቁን ሕዝቦች ጥላቻና የትግራይ ጥላቻ አንዱ ነው። አሁን ደግሞ ኦሮሞ ላይ ያነጣጠረ ጥላቻ በጅምላ እየተካሄደ ነው። እኔ ያ አደገኛ ይመስለኛል፤ በሂደት የሕዝብን አመለካከት ይመርዛል። ስለዚህ የሚሻለዉ በተቻለ መጠን ከጥላቻና ከዉግንና ወጥቶ የሙያ ሥነምግባር አክብሮ መሥራት ነው።
የመንግስት አፈናም የሚዲያዎች ሥርዓት አልበኝነት መቀነስ አለበት። በተለይ መንግስት ሕግና ሥርዓት አክብረዉ የሚሰሩት ሚዲያዎች ላይ የሚያደርገዉ ጫና መቆም አለበት። ነጻና ገለልተኛ ጠንካራ ሚዲያ አለመኖሩ ሐገሪቷን ከሚገባዉ በላይ ዋጋ እያስከፈላት ነው። የፖለቲካዉንም ችግር ሕዝቡ በቅጡ እንዳይገነዘብና በጅምላ ሕዝብን እንዲጠላ እያደረገ ቀጥሏል።
፨💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ። ይህ ቃለምልልስ በስደት ላላችሁ ጋዜጠኞች፦ ናትናኤል ጌቾ ቤታሎና ታጁራ ላምቤቦ ጎታ ይሁንልኝ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረበ የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።
WolaitaTimes , በህብረተሰብ ውስጥ🙏 እናመሰግናለን🙏 #Ethiopia
በናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ዘገባ ነው