1000020709

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ጥንቅር ነው። “Oromia+Tigray+Amhara = Ethiopia ነውን” ? “በኢትዮጵያ የ3ቱ ብሄሮች ንትርክ መቼ ቆመው ሀገሪቱ ሰላም ታገኛለች? 80ዎቹ ተረስቶ በ3ቱ ብቻ እንዴት መፍትሔ ይመጣል?” ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ምላሽ አላቸው፥ ዘገባው እንደሚከተለው ቀርቧል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ሰላም ብለናል ፕሮፌሰር።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ሰላም ብያለሁ ቤተሰቦቻችን እኔም።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ዛሬ በቀጥታ አጭር መልስ የሚሰጡበትን ጥያቄ በመጠየቅ ልጀምር። እንደሚታወቀው አንዳንድ አካላት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሶስቱ ብሔር፣ ማለትም ( አማራ፣ ኦሮሞና የትግራይ ) ሊህቃን ብቻ ይዘወራል ይላሉ፥ እርሰዎ በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በተወሰነ ደረጃ እስማማለሁ፥ ነገር ግን በጣም አምርሬ የምቃወመዉ ነገር ነው። በጣም ትልቅ ችግር ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ለምን እንደዛ የሆነ ይመስልዎታል? የፈደራል ሥርዓቱ ይህንን ማስቆም እንዴት ተሳነዉ? የሚጎዳዉስ ማንን
ነው ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ የሚጎዳዉ ሁሉንም ኢትዮጵያዉያንን ነው። ያለአካታችነት የተረጋጋች ሐገር መፍጠር ዘበት ነውና። መነሻዉ ደግሞ ፖለቲካችን በአቢዮታዊም ሆነ በጥገናዊ መንገድ ተለዉጦ ሁሉንም ዜጋ የሐገር ባለቤት በሚያደርግ መልኩ በማያዳግም ሁኔታ አለመዘመኑ ወይንም የሐገረመንግሥት ግምባታዉ እና የብሔረ መንግስት ግምባታዉ አንካሳነት የፈጠረዉ ነው። ሕገመንግስታዊነት በሌለበት ሕገመንግስታዊ ሥርአት ማለት የይስሙላ ነው የሚሆነዉ። በእዉነቱ ከፈደራል አንጻር የክልሎች ሥልጣን በሕገመንግስቱ መሠረት ትንሽ ቢሆንም ክልሎች በነጻነት ያለ ጫና ሥራ እንደማይሰሩም ይታወቃል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ለዚህ አስቻይ የሆኑ ፣ወይንም መደላደል የፈጠሩ ምክንያቶች ምንድናቸው፣ በተለይ ከፈደራል ሥርዓቱ መምጣት በሁዋላ እንዴት ቀጠለ ችግሩ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ወታደራዊዉ አገዛዝ በዘዉዳዊዉ መንግስት ታፍነዉ የቆዩ የሕዝብ ጥያቄዎች አቢዮቱ መልስ ሊሰጣቸዉ ሲገባ የተወሰነዉን መልሶ ቀሪዉን አፍኖ በጉልበት በመቀጠሉ ሲወድቅ በሐገሪቷ ብዙ የታጠቁ የብሔር ድርጅቶች ነበሩ።

ህወሓት ጠንክሮ በመዋጋት የትግራይን መልከአምድር አመቺነትም በመጠቀም ከሻዕቢያ ዉጪ ከባድ ኃይል ገንብቶ ብአዴንን እንደ አጋር ይዞ አዲስ አበባ ገብቷል። እንግዲህ ህወሓት መራሹ የሽግግር መንግስት በሐገሪቷ ታሪክ ብዙዎቹ የፖለቲካ ኃይሎች የተስማሙበት ሕገመንግሥት ማዋለድ ችሏል።

ነገር ግን ቁልፍ የሚባሉ ሥልጣኖች በሕወሓት የተወሰነዉ ደግሞ በብአዴን ተያዘ። ኦነግ ከሂደቱ በጊዜ ከመገፋቱ በተጨማሪ ሰፊዉ ደቡብ በኢህአዴግ ተላላኪ ሰዎች መተዳደር ጀመረ። ሕገመንግሥቱን በቻርተር ደረጃ እዉቅና የሰጠዉ ኦነግ ተገፍቶ የአብዛኛው የኦሮሞ ሊህቃንን ድጋፍ እንደያዘ የሥርአቱ ተቃዋሚ ሆነ።

በኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት እራሳችንን እንገልጻለን የሚሉ ሕገመንግሥቱን የማይወዱ ኃይሎች ከዉስጥም ከዉጪም በተለያዬ መንገድ የሚቃወም የአማራ ብሔረተኛ ሊህቅ ፈጠሩ። በዘህ ሂደት መሐል ነው በዎላይታ ዎጋጎዳ ትግል አገዛዙን በሰላማዊ ትግል በማስገደድ ክልል አልሞ ዞን መመሥረት የቻለዉ።

እንግዲህ ይህ ትግል በወቅቱ የተለያዩ ኃይሎች በአድናቆት ቢያዩትም አገዛዙን በመጋፈጡ እንጂ የፖለቲካ መብት ሕዝቡ ለመጎናጸፍ የሚያደርገዉ ትግል መሆኑን ተገንዝበዉ የሰጡት እዉቅና አይደለም። እንግዲህ ሕወሓት ጥቂት ሥልጣን ለብአዴን አጋርቶ የተቀረዉን ጠቅልሎ በያዘበት ሲቀጥል የአማራና የኦሮሞ ሊህቃንም ሕወሐትን እናጠፋለን የሚለዉን ቅስቀሳ አባብሰዉ ቀጥለዋል።

የሕወሓት በነሱ እዉቅና መነፈግ የበለጠ ስልጣንን ጠርንፎ እንዲይዝና ተቋማትን በሕገመንግስቱ መሠረት እንዳይገነባ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ሁዋላ ላይ ሕወሓት የዎላይታዉ ዎጋጎዳ በከፈተዉ በር እዉቀት ላላቸዉ የደቡብ ሰዎች ትርጉም ባለዉ ደረጃ የፖለቲካ ሥልጣን ቢያጋራም የአማራና የኦሮሞ ሊህቃን ዎያኔ ከሚለዉ ከፍረጃቸዉ ሊቆጠቡ አልቻሉም፥ ሕወሓትም በተለይም መከላከያና ደኅንነቱ ጠርንፎ ቀጠለ።

በተለይ የኦሮሞና አማራ ሊህቃን ከመነሻዉም ፖለቲካዉን የሶስቱ ብሔሮች ጨዋታ አድርገዉ ማሰባቸዉ ትልቅ ችግር ነው። ሕወሓት ደግሞ ስልጣኑን ያገኘዉ በደምና አጥንት ክፍያ በመሆኑ የእዉቅና መነፈግ ተጨምሮ ጥርነፋዉን እንዲያባብስ የራሱ ሚና ነበረዉ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ አሁንስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች ከዚህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ወጥተዋል ማለት ይቻላል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አይቻልም። ለምሳሌ የጠቅላይ ሚኒስተሩ አማካሪ የሆኑት ሙአዘ ጥበባት ዳንኤል በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አድናቆት ታጅቦ በተመረቀዉ መጽሐፉ በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ልዩነቶችን በኦነግ፣ በሕወሓት እና “ጃዉሳ” (ፋኖን ማለታቸዉ ነው ) መሐል ያለ አድርገዉ አቅርበዋል።

ጃዋር መሐመድ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሶስቱ ብሔር ሊህቃን መስማማት አለባቸዉ እያለ በአደባባይ ያወራል። 80ዎቹን ከመርሳቱ በተጨማሪ በቁጥር ሶስተኛ የሆነዉ ሱማሌ ምን ይሰማዋል ብሎ አለማሰቡ ይገርማል።

በጣም የሚያሳዝነዉ ደግሞ አንጋፋዉ ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በቅርቡ በሰጡት ቃለ ምልልስ የሶስቱ ብሔር ሊህቃን መቀራረብ ስላልቻሉ አገዛዙ እየቀጠለ ነው ብለዋል። ይህን ለማሳያነት ጠቀስኩ እንጂ አብዛኛው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የሚዲያ ኃይሎች ኢትዮጵያን እንደ ሶስቱ ብሄሮች የግል ንብረት ይመለከቷታል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ይህ የሚፈጥረዉ ችግር ቢጠቅሱና መፍትሔውንም ቢጠቁሙን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ችግሩ ግልጽ ነው። ሁሉም የሚገባዉን ቦታ ካልያዘ ሰላም አይመጣም። መገፋት በበዛ ቁጥር ጥገኝነት እየበዛ ሄዶ ለአንዱ እየተደረቡ ሌላዉን የሚያጠቁ ኃይሎች እየበዙ ነው። የተገፉ ሕዳጣን ጉዳይ ደግሞ አሳሳቢ ነው። የታጠቁ ኃይሎች እንዳይበዙና የኮንፌደሬሽን አቀንቃኝ ሊህቃን እንደ አሸን እንዳይፈሉም ያሰጋል።

በመሰላቸዉ መንገድ መሔድ የሚፈልጉ ብሔሮች እየተቀጡ ነው። በቂ ትኩረት ባላገኙ አካባቢዎች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተባባሱ ነው። አስታራቂ ሐሳብ ለማመንጨት እንኳን ለተቀሩ ብሔር ሊህቃን የሚሆን ቦታ የለም፤ ለእገሌ ወግነሐል እገሌን የበለጠ ትወዳለህ የማለት ነገር ስላለ ብዙዎች ዝምታን መርጠዋል።

መፍትሔው ከሶስቱ ብሔሮች ዉጪ ያሉ ሊህቃን ለመብታቸዉ መታገል አለባቸዉ። በሐቀኝነት ለሁላችንምየምትሆን ኢትዮጵያ እንገንባ የሚል ሁሉ የሶስቱን ብሔር ሊህቃንን ፈላጭ ቆራጭነት መታገል አለበት። በሕጋዊ ማዕቀፍ ዉስጥ ሆኖ የራስን ድምጽ ማሰማት ያስፈልጋል።

በጦርነት አታምንም ማለት ጦርነቱን የሶስቱ ብሔር ሊህቃን ፈጠሩ ማለት አንተን የጦርነቱ ወላፈን አይነካህም ማለት አይደለም። ስለዚህ ይህንን የሶስቱን ብሔር ሊህቃን የሐገሩ የኛ ብቻ ነውን አስተሳሰብ አምርሮ መታገል ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የሶስቱ ብሔሮች ብቻ አይደለችምና።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረበ የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።

WolaitaTimes , በህብረተሰብ ውስጥ🙏 እናመሰግናለን🙏 #Ethiopia #Tigray #Amhara #Oromia

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ጥንቅር ነው