
“እባካችሁ በዎላይታ ዞን ቦምቤ ወረዳ ህብረተሰቡ በወባ ወረርሽኝ እያለቀ ነው ለሚመለከታቸው አካላት አድርሱ። ትናንትና በወረዳው ሁለት ወንድማማቾች በዚሁ በሽታ ሞተው በአንድ ቀን በአንድ መቃብር እንዲቀበሩ ተደርጓል። ህዝብ እያለቀ ነው። ባለፈው በእናንተ ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በአከባቢያችን የወባ ወረርሽኝ ህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ስለመሆኑ መዘገቡን ተከትለው የተወሰኑ የሚመለከታቸው አካላት የሁለት ቀን ዘመቻ ያደረጉ ቢሆንም አሁን ላይ ህብረተሰቡ ባለቤት አጥተው በበሽታው በየቀኑ እየሞተ ነው እባካችሁ አሁንም እንደወትሮው ድምፅ ሁኑልን” በሚል የአከባቢው ነዋሪዎች ተማፅነዋል።
በተጨማሪም ነዋሪዎቹ “ለሌላው ደግሞ አያይዘን ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስ የምንፈልገው በአከባቢው ያለው ጤና ጣቢያ እና ጤና ኬላ ላይ መድሀኒት የለም፣ ባለሙያዎች የሶስት ወር ደመወዝ አልተከፈለም በሚል የሉም እየገቡ አይደለም። ህብረተሰቡ ወደ ግል ጤና ጣቢያዎች በውድ ዋጋ ለመታከምና የወባ መድሀኒት ለመግዛት ሲሄዱ አብዛኞቹ የተሳሳተ መድኃኒት በእርካሸ እንሸጣለን በሚሉ ተታልለው ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ። እባካችሁ ህብረተሰቡ እያለቀ ነው ድምፃችን አሰሙልን” በሚልም አሳስበዋል።
በሌላ በኩል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ ከ650 በላይ ዜጎች ህይወት መቅጠፉን ከስፍራው በተደጋጋሚ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በአከባቢው ባለው በጤና ተቋማት ላይ የህክምና ቁሳቁስ ያለመኖሩ ወረርሽኝ እንዲስፋፋና በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲያደርስ ምክንያት ስለመሆኑ ነዋሪዎቹ ከስፍራው ያደረሱት መረጃ ይጠቁማል።
አንድ የአከባቢው ነዋሪ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ሁኔታውን ሲገልፅ “ከሰኔ ወር ጀምሮ በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ጥዮ፣ ጫማ እና ማጣላ ሂምቤቾ ቀበሌዎች ህብረተሰቡ በወባ ወረርሽኝ እየተሰቃየ ነው” በሚል ገልጸዋል።


በዚህ ወባ በሽታ የተጠቃውን ቤተሰብ አባል ሶስት ጊዜ ወደ ሀኪም ቤት መውሰዱን የገለፀው አስተያየት ሰጪው በአከባቢው ባለው ጤና ጣቢያ ማስገባቱን ተናግሮ በቂ ህክምና አቅርቦት ባለመኖሩ ወደሌላ ሀኪም ቤት መውሰዱን አስረድተዋል።
“በሚያሳዝን ሁኔታ በአከባቢው ዘንድሮ በወባ በሽታ ተጠቅተው ከሁለት ጊዜ ያላነሰ ሀኪም ቤት ያልገባ ሰው የለም፥ አሁን ደግሞ ብዙ ሰዎች በቂ ህክምና ባለማግኘታቸው እየሞቱ ነው እባካችሁ ይሄንን የህዝብ ስቃይ ይፋ ተደርጎ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጉ” ሲል ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተማፅነዋል።
ሌላኛው በኪንዶ ኮይሻ ወረዳ በማንኣራ ቀበሌ ወላጅ እናቱንና ወንድሙን በወባ በሽታ ወረርሽኝ ታመው በአከባቢው የህክምና አቅርቦት ባለመኖሩ በሌ ከተማ የመጀመሪያ ሆስፒታል ቢያመጣቸው እናቱን ማዳን እንዳልቻለ በመግለፅ በቀበሌያቸው ባለፍው ሰኔ እና ሐምሌ ወር እናቴን ጨምሮ 10 ሰዎች በወባ በሽታ ሞተዋል፥ አሁንም ህክምና ማግኘት ስላልቻሉ ታመው በቤታቸው የሚገኙ ሰዎች እንዳሉ አስረድተዋል።


በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ አንድ ጤና ጣቢያ ባለሙያ በማገልገል ላይ የምትገኝና ስሜ አይጠቀስ ያለች የህክምና ባለሙያ” በጤናው ዘርፍ መረጃ በየጊዜው ሪፖርት የሚደረግ ቢሆንም መንግሥት አስፈላጊውን የጤና ግብዓት እያቀረበ ወረርሽኙ ለምን ተከሰተ የሚል ተጠያቂነትን ለመሸሽ ሲባል በወረርሽኝ የተጠቁ ህብረተሰብ ክፍሎች በሽታና ሞት በበላይ አካላት እንዲሰወሩ ተደርጓል” ስትል ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ገልፃ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
በተጨማሪም በአከባቢው በርከት ያሉ አዋቂዎችና ህፃናት በሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ህክምና የሚከታተሉ፣ የሞቱ እንዲሁም ወደ ጤና ተቋማት መምጣት ያልቻሉት በየቤታቸው እንዳሉ በመግለፅ በወረርሽኙ ምክንያት እየተሰቃዩ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጂት፣ ሚዲያዎችና ጉዳዩ የሚመለከተው ሁሉ በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ጥሪ አቅርባ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም በዎላይታ የህብረተሰቡን ጤና “አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር” በሚል በመቶ ሚሊዮኖች ከዓለምአቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የሚመደበው ገንዘብ ለሌላ አላማ እየዋለ በመሆኑ የወባ፣ የኩፍኝ እና ሌሎች የወረርሽኝ በሽታዎችን መቆጣጠርና መከላከል ስራ አስቸጋሪ እያደረገና በርካቶች እንዲሞቱ እያደረገ ስለመሆኑ በዎላይታ ዞን በተለያዩ መንግስት ሆስፒታሎች የሚሰሩ ዶክተሮች ያደረሱት መረጃ ያመለክታል።
በዞኑ በአብዛኛው ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ስራ አስቸጋሪ ከማድረጉ ባለፈ ከዞን ባለሙያዎች ጭምር ወረርሽኝ ወደተከሰተበት አከባቢ በጊዜው ለመሄድ የተመደበው ገንዘብ ለሌላ አላማ በመዋሉ በየአካባቢው የሚከሰቱ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እያደረገ እንደሆነም የጤና ባለሙያዎች ያደረሱት መረጃ ያመለክታል።
ሰሞኑን በዞኑ በተለይም በቦሎሶ ቦምቤ፣ ክንዶ ኮይሻ፣ ክንዶ ዲዳዬ፣ በዳሞት ፑላሳ፣ ሁምቦና አባላ፣ ቦሎሶ ሶሬ እንዲሁም በሌሎች አንዳንድ ወረዳዎች ስለተከሰተው የወባ ወረርሽኝ በተመለከተ ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሚመለከታቸውን አካላት ለማግኘት በድጋሚ ያደረገው ጥረት ያልተሳካ ቢሆን ምላሽ እንዳገኘን እንመለስበታለን።
ያም ሆነ ይህ በዞኑ የተከሰተው አስደንጋጭና ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ በቀላሉ መቆጣጠርና መከላከል እየተቻለ በርካቶችን ለሞት እየዳረገ ነውና የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ትኩረት ይሻል። #Ethiopia #Wolaita #Malariaoutbreak #WHO
በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው