1000022061

ለመሆኑ ዜጋህን እስከመቼ ታባርራለህ ? ወዴትስ ታባርረዋለህ? ዜጋ ተኮር የተባለ የብልፅግና ፖሊስ በመዋቅራዊ ጫና የሚንከራተቱ ዜጎችን ለምን ያሳድዳል? በሀገራቸው ስደተኛ ስለሆኑ ዎላይታዎች እና ለሌሎች እንደወትሮው ሁሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና በዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ለተነሱ ለዚሁ እና ለተያያዥ ጉዳዮች ምላሽ አላቸው፥ ዘገባውም ቀጥታ እንደሚከተለው ቀርቧል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በአዲስ አበባና በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በስፋት ሕገወጥ የጎዳና ንግድ ይስተዋላል። በዚህም በብዛት የዎላይታ ልጆች ይሳተፋሉ ስለዚህ ጉዳይ ያሉዎትን ምልከታ ቢያጋሩን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አዎ እንዳልከዉ አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች ሕገወጥ የጎዳና ንግድ ይስተዋላል፥ የዎላይታም ልጆች በስፋት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ከሌሎች በበለጠ ሁኔታ ይሳተፋሉ። በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ የዎላይታ ልጆች ቁጥር በ100ሺዎች እስከ ሚሊየን ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። በግርድፉ ስናስቀምጥ ንግዱ ሕገወጥ ከመሆኑም በላይ ጸሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸዉ የፖሊስ ዱላ እና የንብረት ነጠቃ እየደረሰ፣ በሽሽትም ሲሮጡ ከመንገድ ላይ ጉድጓዶችና አደጋ ሊያስከትል ከሚችል መኪና ጋር የሚጋፈጡበት ፈታኝ ሥራ ነው።

አንዳንዶቹ የሚሸጧቸዉን በራሳቸዉ ገዝተዉ ለትርፍ ሲሸጡ፣ ሌሎች ደግሞ የሌሎች ነጋዴዎችን እቃ በአነስተኛ ክፍያ በየጎዳናው እያዞሩ ይሸጣሉ። በርግጥ ስራዉ ሕገወጥ እና ግብር የማይከፈልበት ነው። መንግስትም ግብር ከፍለዉ የሚሰሩ ሕጋዊ ነጋዴዎችን ይጎዳል ብሎ ለመከላከል መንቀሳቀሱ በመሠረታዊነት ከሕግ አንጻር ካየነዉ ልክ ነው። ነገር ግን ይህ በሚሊየን የሚቆጠረዉ በየከተሞቹ በሕገወጥ የጎዳና ንግድ ላይ የሚሳተፈዉስ ዜጋ አይደለም ወይ? እንደ ዜጋ በሕጋዊ ንግድ እንዲሳተፉ ምን የተመቻቸ ነገር አለ የሚለዉ መጠየቅ አለበት?

በነገራችን ላይ ከዜግነትም አንጻር በተለይ የዎላይታ ልጆች ነገር ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በአዲስ አበባ በዚህ ደረጃ በቁጥር በዝተዉ ያሉት የዎላይታ ልጆች የከተማው ነዋሪነት መታወቂያ የላቸዉም፣ በምርጫ አይሳተፉም ማለት ነው ጉዳያቸዉን እንደአጀንዳ የሚያነሳ ፓርቲም የለም። በጣም የሚገርመዉ እነዚህ በየከተማዉ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚኖሩ የዎላይታ ልጆች በቅርቡ በዎላይታ በተካሄደዉ “ሕዝበ ዉሳኔ” አልተሳተፉም።

በሚኖሩበትም በዎላይታ ዞንም በኩል የዜግነት መብታቸዉን የሚጠቀሙበት እድል የላቸዉም፣ ይህ እንግዲህ “ማነዉ ኢትዮጵያዊ?” የሚለዉን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በሌላዉ አለም Absentee voting የሚባል አሰራር አለ ዜጋ መሰል መብቶቹን እንዲጠቀም የሚደረግበት አሰራር፤ በእኔ እምነት እነኝህ በየከተማዉ እንደሁለተኛ ዜጋ የሚኖሩ የዎላይታ ልጆች የእዉነትም ዜጋ ናቸዉ ተብሎ ከታመነ ወይ በሚኖሩበት መታወቂያ እና የሥራ ቦታ የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፣ ካልሆነም የዎላይታ ዞን ነዋሪ ከተባሉ በምርጫም ሆነ በሕዝበ ዉሳኔ መሳተፍ አለባቸዉ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ይህ መጥፎ እጣ ለምን በብዛት የዎላይታ ልጆች ላይ የወደቀ ይመስልዎታል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ነገሩ ሰፊ ና ጥልቅ ጥናት የሚፈልግ ነው ፣በየከተሞቹ በብዛት የዎላይታ ልጆች በመሰል ሥራዎች ላይ መሰማራታቸዉ አዉነት ነው። በአዲስ አበባም ከፖሊስና ደምቦች ዱላ ሽሽት ሲሮጡ ብዙዎቹ ዎላይትኛ ሲነጋገሩ መስማት የተለመደ ነው። የዎላይታ ልጆች በዘርፉ ስለመብዛታቸዉ በግሌ ግን የተለያዩ መላምታዊ ግምቶችን ማስቀመጥ የሚቻል ይመስለኛል።

ያዉ እኔ የዎላይታ ሕዝብ በሐገረ መንግስት ግምባታ አቅጣጫ ላይ ከጥንት ጀምሮ ባለዉ ልዩነት ምክንያት ሲቀጣ የኖረና አሁንም የሚቀጣ ሕዝብ ነው ብዬ አምናለሁ። ሕዝቡ ለዘመናት ብዙ ፖለቲካዊ ተንኮሎች ተሰርተዉበት፣ ለዘመናት ለፖሊሲ ክፍተት ተጋልጦ ኖሯል።

የአስተዳደር መዋቅሮች ሆን ተብለዉ ሕዝቡን ለመጉዳት በማለም ይደራጃሉ፣ የሕዝብ ብዛቱን በሚቃረን መልኩ በቀየዉ ሕዝቡ ትልቅ ከተማ እንዳይሰራ ለዘመናት የዘለቀ ጫና አለ፣ የመንግስታቶቻችን አግላይነትም ድርሻዉ ብዙ ይመስለኛል። የኢትዮጵያ መንግስታት የሚጠቀሙት የሕዝቡ ቁጥርም ከጥንትም አጠራጣሪ ነገሮች የሚበዙበት (በማስረጃ የተደገፉ) ነው። ሌላዉ ደግሞ የብሔር ጭቆና መልክና ደረጃዉን ቀይሮ የመቀጠል እድሉ ሰፊ ከመሆኑን በላይ ሕዝባዊ ጠባሳዉም በቀላሉ ከትዉልድ ትዉልድ ሊሸጋገር ይችላል።

በአካባቢው ለድሕነት ቅነሳ በቂ ትኩረት አለመሰጠቱ ካለዉ ሕዝብ ብዛት አንጻር የሥራ እድል አለመኖሩ። በተለይ መንግስት አንድን ችግር አይቶ በሚመጥን ደረጃ ትኩረት አለመስጠቱ፣ መዋቅራዊ ጫና፣ የኢኮኖሚ አቅም ጉዳይ እና የመሳሰሉ ሊሆኑ ይችላል። ነገሩ ሰፊና ጥልቅ ጥናት ይፈልጋል አዝማሚያዉም እየተባባሰ የመሄድ ነገር ይታይበታል።

አንድ ግን አጽንኦት ሰጥቼ ማስተላለፍ የምፈልገዉ መልዕክት ዜጋን ማሳደድ ተገቢ አይደለም!! መፍትሔም አይደለም!! መንግሥት ይሄ ሁሉ የኔ ዜጋ የተሠማራበት ዘርፍ አንዳች ወደ ሕጋዊ መሥመር የሚመጣበትን አግባብ መፍጠር አለብኝ የሚል አስተሳሰብ ሊኖረዉ ይገባል። ይሄን ሁሉ ሰዉ የደምብ ቁጥር በማብዛት እቆጣጠራለሁ ማለትም ስህተት ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ባለድርሻ አካላትንና መፍትሔዎች የሚሏቸዉን ነገሮች ቢጠቁሙን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ የዞኑ፣ የክልሉና የፈደራል መንግስት፣ ሚዲያዎች፣ ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ የፖለተካ ፓርቲዎች እና የመሳሰሉት ጉዳዩን የኔ ሊሉት ይገባል። በተረፈ ይህ በጣም ሰፊ እና ጥልቅ ጥናት ላይ የተመሠረተ እርምጃ የሚፈልግ ነው። ይሕ ጉዳይ አጀንዳ መሆን አለበት፣ መንግስት ይሄ ሁሉ ዜጋ የተሠማራበትን ዘርፍ በደምብ አስከባሪዮች እቆጣጠራለሁ አጠፋለሁ ብሎ ካሰበ ስህተት ብቻ ሳይሆን ዜጋ ተኮር ያልሆነ አካሄድ ነው።

በእዉነት ደምቦች ሲያባርሯቸዉ ልጆቹ ላይ የመኪና አደጋ እንዳይደርስም በጣም ያሰጋል። መንግስት በጥብቅ የሚያስጠብቃቸዉ አካባቢዎች ላይ ሲጠፋ ቀንሶ ሳይሆን ቦታ ቀይሮ ንግዱ ቀጥሏል። መዝግቦ አደራጅቶ ወደ ሕጋዊ መሥመር ማስገባቱ አስፈላጊ እርምጃ ነው። ተጨማሪ ወጣቶች ደግሞ ወደ ዘርፉ እንዳይቀላቀሉም፤ በተለይ በዎላይታ አይነት አካባቢዎች የድኅነት ቅነሳ ፖሊሲዎች በትኩረት ተነድፈዉ ወደ ሥራ መግባት አለባቸዉ። ዜጋህን እስከመቼ ታባርራለህ ? ወዴት ታባርረዋለህ?

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።

WolaitaTimes , በህብረተሰብ ውስጥ🙏 ስለአብሮነታችሁ እናመሰግናለን🙏 #Ethiopia #Wolaita #Tigray #Amhara #Oromia #addisababa

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመየቅ ተደርጎ የተሰራ ዘገባ ነው