
በዎላይታ ከጦርነት በላይ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘው አስደንጋጩ በሽታ ምን እንደሆነ ጥናት ተደርጎ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠየቀ።
“በአሁኑ ወቅት የህብረተሰቡን ህይወት በከፍተኛ ሁኔታ እየቀጠፈ የሚገኘው እውነትም የወባ ወረርሽኝ ስለመሆኑ በገለልተኛ የአለም ጤና ተቋም ወይንም በሲዲሲ ምርመራ ተደርጎ መረጋገጥ መቻል አለበት። በጣም አስደንጋጭ ሁኔታ ላይ ደርሷል። በዎላይታ የአሁኑ ዓይነት የወባ ወረርሽኝ የተከሰተው ከሚኒሊክ ወረራ ማግስት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ” ስል በዞኑ ተዘዋውረው ትዝብቱን እንዲያካፍል የተባበሩ አንድ ግለሰብ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የጉዳቱን መጠን ጠቁመዋል።
ግለሰቡ አክለውም “ይህ በዎላይታ ደጋማው ክፍልን ጨምሮ በተለምዶ ወባ በብዛት ተከስቶ በማይታወቅ አከባቢዎች ተሰራጭቶ ሕዝቡን እየጨረሰ የሚገኘው በትክክል ወባ ብቻ ነው ለማለት እቸገራለሁ። በክስተቱም የሰው እጅ ስላለመኖሩ እየተጠራጠርኩ ነው” በሚልም ስጋቱን ገልጸዋል።
“ሰዎች በበሽታው እየሞቱ በአይኔ ተመልክቻለሁ፥ በአከባቢው ያሉ አብዛኞቹ ህብረተሰብ ክፍሎች መጠቃታቸውን እንዲሁ፦ በሽታው ራሱ ወባ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በልዩ ሁኔታ በዎላይታ ዞን ብቻ እንዴት ሊከፋ ቻለ የሚለው ጥያቄ የሚጭር ነው” ስልም ሁኔታውን አብራርተዋል።
ሌላኛው በዞኑ በስራ ምክንያት በየአካባቢው በዞረበት ወቅት የታዘበውን ለWT ሲያስረዳ “በዎላይታ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ላይ አደገኛ ወረርሽኝ በመከሰቱ ምክንያት ህብረተሰቡ በበሽታው መሰቃየትና በሺዎች የሚቆጠሩት ህይወት መቅጠፍ ከጀመረ ወራቶች ከተጎጂ ሰዎች አረጋግጫለሁ። ነገር ግን እስካሁን ዞኑ ሆነ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሽታውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረትም እንቅስቃሴ ካለመኖሩ ባሻገር የመንግስት ጤና ጣቢያዎች ባዶ ናቸው፤ መድኃኒት የላቸውም በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎች ደሞወዝና የትርፍ ሰዓት ክፍያ በጊዜ ያልተከፈለላቸው በስራ ገበታቸው ላይ ስለማይገኙ ህብረተሰቡ በወረርሽኙ በመታመሙ ወደ ጤና ጣቢያ እየጎረፈ ቢሆንም የሚያስተናግድ የለም። ህብረተሰቡ በዚህ ክፉ ወረርሽኝ ህይወቱ ተቀጥፈው ከማለቁ በፊት የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ምላሽ መስጠት አለባቸው” በሚል ተማፅነዋል።
የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግምባር የሥራ አስፈፃሚ ጥቅምት 3/2017 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በላከው መግለጫ ላይ በዎላይታ ውስጥ በሁሉም ወረዳዎች የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈና የበርካቶች ህይወት እንዲናጋ ምክንያት መሆኑን እንዳሳሰበው የዎህዴግ የሥራ አስፈፃሚ ገልጾ መንግስት የሚከተለው የጤና ፖሊሲ የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ እንኳን የሚያስችል አቅም የሌለው መሆኑ ማሳያ ነው” በሚል መተቸታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም መንግስት የጤና ባለሙያ ደመወዝና ጥቅማጥቅም በጊዜ ባለመክፈሉ፣ ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢዎችና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፊታሎች ምንም ዓይነት መድኃኒት ባለመኖራቸው ምክንያት በበሽታው የተያዙ ሰዎች መዳን እየቻሉ በመድኃኒት እጥረት እየሞቱ መሆኑ እጅግ በጣም እንደሚያሳዝንና እንደሚያሳፍርም በመግለፅ መንግስት በአስቸኳይ የህዝባችን ሕይወት እንዲታደግ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ከዚህ ውጭ በህዝባችን ላይ በሚደርሰው አደጋ መንግስት ራሱ ተጠያቂ መሆኑንም እንዲሁ ዎህዴግ አሳስቧል።
“እባካችሁ በዎላይታ ባልታወቀ በሽታ በየአካባቢው ህዝብ እያለቀ ነው። ባለፈው በእናንተ ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በአከባቢያችን የወባ ወረርሽኝ ህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ስለመሆኑ መዘገቡን ተከትለው የተወሰኑ የሚመለከታቸው አካላት የሁለት ቀን ዘመቻ ያደረጉ ቢሆንም አሁን ላይ ህብረተሰቡ ባለቤት አጥተው በበሽታው በየቀኑ እየሞተ ነው እባካችሁ አሁንም እንደወትሮው ድምፅ ሁኑልን” በሚል የአከባቢው ነዋሪዎች ተማፅነዋል።
አክለውም “ለሌላው ደግሞ አያይዘን ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስ የምንፈልገው ህብረተሰቡ ወደ ግል ጤና ጣቢያዎች በውድ ዋጋ ለመታከምና የወባ መድሀኒት ለመግዛት ሲሄዱ አብዛኞቹ የተሳሳተ መድኃኒት በእርካሸ እንሸጣለን በሚሉ ተታልለው ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ። እባካችሁ ህብረተሰቡ እያለቀ ነው ድምፃችን አሰሙልን” በሚልም አሳስበዋል።
ሌላኛው አንድ የአከባቢው ነዋሪ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ሁኔታውን ሲገልፅ “በሚያሳዝን ሁኔታ በአከባቢው ዘንድሮ በበሽታው ተጠቅተው ከሁለት ጊዜ ያላነሰ ሀኪም ቤት ያልገባ ሰው የለም፥ ሁሉም ጋ ለቅሶ አለ፣ አሁን ደግሞ ብዙ ሰዎች በቂ ህክምና ባለማግኘታቸው እየሞቱ ነው እባካችሁ ይሄንን የህዝብ ስቃይ ይፋ ተደርጎ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጉ” ሲል ተማፅነዋል።
በዞኑ ቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ አንድ ጤና ጣቢያ ባለሙያ በማገልገል ላይ የምትገኝና ስሜ አይጠቀስ ያለች የህክምና ባለሙያ” በጤናው ዘርፍ መረጃ በየጊዜው ሪፖርት የሚደረግ ቢሆንም መንግሥት አስፈላጊውን የጤና ግብዓት እያቀረበ ወረርሽኙ ለምን ተከሰተ የሚል ተጠያቂነትን ለመሸሽ ሲባል በወረርሽኝ የተጠቁ ህብረተሰብ ክፍሎች በሽታና ሞት በበላይ አካላት እንዲሰወሩ ተደርጓል” ስትል ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ገልፃ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
በተጨማሪም በአከባቢው በርከት ያሉ አዋቂዎችና ህፃናት በሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ህክምና የሚከታተሉ፣ የሞቱ እንዲሁም ወደ ጤና ተቋማት መምጣት ያልቻሉት በየቤታቸው እንዳሉ በመግለፅ በወረርሽኙ ምክንያት እየተሰቃዩ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጂት፣ ሚዲያዎችና ጉዳዩ የሚመለከተው ሁሉ በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ጥሪ አቅርባ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም በዎላይታ የህብረተሰቡን ጤና “አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር” በሚል በመቶ ሚሊዮኖች ከዓለምአቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የሚመደበው ገንዘብ ለሌላ አላማ እየዋለ በመሆኑ የወባ፣ የኩፍኝ እና ሌሎች የወረርሽኝ በሽታዎችን መቆጣጠርና መከላከል ስራ አስቸጋሪ እያደረገና በርካቶች እንዲሞቱ እያደረገ ስለመሆኑ በዎላይታ ዞን በተለያዩ መንግስት ሆስፒታሎች የሚሰሩ ዶክተሮች ያደረሱት መረጃ ያመለክታል።
በዞኑ በአብዛኛው ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ስራ አስቸጋሪ ከማድረጉ ባለፈ ከዞን ባለሙያዎች ጭምር ወረርሽኝ ወደተከሰተበት አከባቢ በጊዜው ለመሄድ የተመደበው ገንዘብ ለሌላ አላማ በመዋሉ በየአካባቢው የሚከሰቱ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እያደረገ እንደሆነም የጤና ባለሙያዎች ያደረሱት መረጃ ያመለክታል።
ሰሞኑን በዞኑ በተለይም በቦሎሶ ቦምቤ፣ ክንዶ ኮይሻ፣ ክንዶ ዲዳዬ፣ በዳሞት ፑላሳ፣ ሁምቦና አባላ፣ ቦሎሶ ሶሬ እንዲሁም በሌሎች አንዳንድ ወረዳዎች ስለተከሰተው ያልተረጋገጠ ወባ መሠል ወረርሽኝ በተመለከተ ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሚመለከታቸውን አካላት ለማግኘት በድጋሚ ያደረገው ጥረት ያልተሳካ ቢሆን ምላሽ እንዳገኘን እንመለስበታለን።
ያም ሆነ ይህ በዞኑ የተከሰተው አስደንጋጭና ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ በቀላሉ መቆጣጠርና መከላከል እየተቻለ በርካቶችን ለሞት እየዳረገ ነውና የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ትኩረት ይሻል። #Ethiopia #Wolaita #Malariaoutbreak #WHO
በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው