የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ “ገበታ ለአባያ የሀይቅ ልማት ፕሮጀክት” ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለፀ

በዎላይታ ውስጥ በሚገኘው አባያ ሀይቅ ላይ ተግባራዊ የሚወነው የ”ገበታ ለአባያ የሀይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት” በሚፈለገው የጥራት ደረጃ እንዲተገበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አሳወቀ።

በዩኒቨርሲቲው አስተባባሪነት በወላይታ ዞን አበላ አባያ ወረዳ ሊተገበር የታቀደው “ገበታ ለአባያ የሀይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት” በዛሬው እለት በዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት ተጎብኝቷል።

የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለውና ለስራ እድል ፈጠራም የሚኖረው ፋይዳ ጉልህ መሆኑን በመረዳት መንግስት ለዘርፉ እድገት ትኩረት በመስጠት ዘርፈ-ብዙ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡

መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ ልማት ትኩረት በመስጠት በአዲስ አበባ ውስጥ የእንጦጦ፣ የሸገርና የዩኒቲ ፓርኮችን ማልማት የቻለ ሲሆን፤ በሀገሪቱ የቱሪስት መስህብ በሆኑ የጎርጎራ፤ የኮይሻና የወንጪ የቱሪስት ስፍራዎችን “በገበታ ለሀገር ብሮጀክት” እያለማ ይገኛል።

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በመንግስት የተጀመሩ የቱሪዝም የልማት ፕሮጀክቶች ለሀገር እድገት የሚኖራቸውን ፋይዳ በመገንዘብ እንደ አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የትኩረት መስኩም የቱሪዝም ልማት ላይ በማድረግ የአካባቢውን እምቅ የተፈጥሮ መስህቦችን ለማልማት እቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል።

መንግሥት በተለያዩ አከባቢዎች ለማሳያ ያህል የጀመራቸው የቱሪዝም ልማት ስራዎች በሌሎች አከባቢዎች በማስፋት ለመተግበር ትምህርት ሊወሰድባቸው እንደሚገባ በማመን የዩኒቨርሲቲው አስተዳር በወላይታና አካባቢው የሚገኙ እምቅ የመስህብ ስፍራዎችን በማስጠናት ላይ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩትን የቱሪዝም ልማት ስራዎች ልምድ በመውሰድ በራስ አቅም ሕዝብን እና የመንግስት ተቋማትን በማስተባበር ለማስጀመር ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።

በወላይታና አከባቢው ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን በማልማት የቱሪዝም መስህቦችን ማልማት የሚቻልበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ትኩረቱን በአባያ ሐይቅ ዙሪያ በማድረግ በአካባቢው የቱሪስት ፍሰትን ማጠናከር የሚያስችል ተጨማሪ መዳረሻ ለመፍጠር የዩኒቨርሲቲው አስተዳድር የመጀመሪያውን ምእራፍ የቅድመ ጥናት ስራ ጀምሯል።

የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር/ማኔጅመንት አባላት በዛሬው እለት በወላይታ ዞን አበላ አባያ ወረዳ ሊተገበር የታቀደውን የ”ገበታ ለአባያ የሀይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት” የጎበኙ ሲሆን፤ በሐይቁ ዙሪያ እና አካባቢው የሚገነባውን Summer City Project አተገባበር ላይ ከተቋቋመው አብይ ኮሚቴ እና የፕሮጀክቱ አስፈጻሚ አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።

ፕሮጀክቱን እንዲያስፈጽም የተቋቋመው አብይ ኮሚቴ በ10 ቀናት ውስጥ ለፕሮጀክቱ አተገባበር አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በማደራጀት እና በማጠናቀር ፕሮጀክት ፕሮፖዛል/ንድፍ አዘጋጅተው ለማኔጅመንቱ እንዲያቀርቡ በውይይቱ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በዩኒቨርሲቲው ተነሳሽነት በአባያ ሐይቅ ዙሪያ ለሚተገበረው “ገበታ ለአባያ የሀይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት” መንግስት እና የአከባቢው ማህበረሰብ አባላት ባለሀብቶች፣ የአካባቢው ተወላጆችና ወዳጆች እንዲሁም ዳያስፖራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ተብሏል።

በፕሮጀክቱ አተገባበር የድጋፍ ማዕቀፍ ላይ የፌዴራል መንግስት ፤ የክልልና የዞን መንግሥት የድርሻቸውን እንደሚወጡ እንዲሁም ከልማት አጋሮች ሀብት የማፈላለግ ሥራዎች በስፋት እንደሚተገበር አቅጣጫ ተቀምጧል።

በአካባቢው የሚገኙ እምቅ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን በመለየት ማልማት ኢኮኖሚያዊ አቅምን ከመገንባት ባሻገር ለበርካቶች ምቹ የስራ እድል ለመፍጠር አጋዥ እንደሆነም ተጠቁሟል የተባለውን ከዩኒቨርስቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።