“የዎላይታ ሶዶ፣ የቦዲቲና የአረካ የተናጠል ጉዞ ብዙ አዋጭ አይደለም ከተሞቹ በዙሪያው ያሉትን ቀበሌዎችን ጨምሮ ከሚሰፉ ይልቅ በዙሪያቸው ያሉትን ከተሞች በማካተት አንድ ላይ የሚያድጉበት አሰራር መዘርጋት አለበት…. ከተሞቹ ለውጤታማነት በጀታቸዉ ከአንድ ማዕከል በአንድ አመራር ሥር ( ከንቲባ ስር ) በተቀናጀ ሁኔታ ይመራ” —— እንዴት፣ ለምን፣ በማን፣ መቼ እና በምን ለሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎች ምላሽ ይዘናል ቀጥታ ወደ ጥንቅራችን እንግባ👇

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንግዳችን እንደወትሮው ጥሪያችንን ተቀብለዉ በድጋሚ እንኳን ደህና መጡ። ያዉ ባለፈዉ እንዳሉት የሚዲያችን ቤተሰብ ስለሆኑ ቀጥታ ወደ ጥያቄ እንግባ።
በቅርቡ በዎላይታ የሚገኙ ሶስት ትልልቅ ከተሞች፣ ዎላይታ ሶዶ፣ አረካ እና ቦዲቲ የተወሰኑ የገጠር ቀበሌዎችን በማካተት የቆዳ ሥፋታቸዉን ጨምረዋል። ይሄን እንዴት ያዩታል? ከዚህ የተሻለ የሚሉት ሌላ አማራጭ ሐሳብ ካሎትም መግለጽ ይችላሉ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሺ አመሰግናለሁ። እነዚህ ሶስቱ ከተሞች ለየት የሚያደርጋቸዉ በጣም በቅርብ ርቀት የሚገኙ መሆናቸዉ ነው። የሚስፋፉበትም መንገድም የተቀናጀና ተገናኝቶ አንድ ትልቅ ከተማ መፍጠርን ያለመ መሆን አለበት ባይ ነኝ። አሁን ግን የተደረገዉ መስፋፋት አስፈላጊ ባልሆኑ አቅጣጫዎችም ጭምር የተደረገ ነው ሶስቱም ጋር።
በተናጠል ሶስት ትልቅ የተለያዬ ከተማ መፍጠር በነባራዊዉ የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚቻል አይደለም። ለዎላይታ አይነት በሐገረ መንግስት ግምባታ አቅጣጫ ላይ ልዩነት ላለዉ ብሔር አይመከርም። ከዛ ቀጥሎ ሶስቱም ከተሞች ከቋንቋ፣ ባህልና ማንነት ጀምሮ የእድገት ደረጃቸዉም ተመጣጣኝ እና የተያያዘ የሚባል ነው። ስለዚህ እነሱን አንድ ትልቅ ከተማ ለማድረግ አልሞ መንቀሳቀሱ አዋጭ ይመስለኛል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በምን አይነት መንገድ ነው አንድ ከተማ አድርገን ልናደራጅ የምንችለዉ የሚለዉ ላይ በስፋትና በዝርዝር ቢሄዱበት?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በርግጥ የተለያዩ ሰዎች የተለያዬ ሐሳብ ሊያመነጩበት እንደሚችሉና ያም በደምብ መደመጥና ለዉይይት ክፍት መሆን አለበት የሚለዉን እንየዝ። እኔ የከተማዉ ስም “ዎላይታ ሶዶ ከተማ!” መሆን አለበት ባይ ነኝ። ለምሳሌ ( ዳሞት፣ ጦና፣ ዲቻ፣ ቦዲቲ፣ አረካ፣ ጉኑኖ፣ ዳልቦ፣ ሁምቦ ) ክፍለ ከተሞች። ሆስፑን ዳናን ወይንም ላፑን ዎይሻን ለማስታወስ፣ በስምንት ወይንም ሰባት ከፍለ ከተማ ደረጃ ማደራጀት ይቻላል፣ ሌላም Symbolic ነገር መጠቀም ይቻላል።
የዎላይታ ዞን በገዥዎች ችሮታ ሳይሆን በሕዝባችን መራራ ትግል የተቋቋመ ነው። ይህ ዞን ሕዝቡንና ምሁራንን እያማከረ፣ ለሕዝቡ የሚጠቅሙ እርምጃዎችን መዉሰድ አለበት ብዬ አምናለሁ። በአሁኑ ሰአት ዎላይታ ሶዶ በራሷ እያደገች ነው፣ በጣም በቅርብ እርቀት ላይ የሚገኙት ቦዲቲና አረካም በጥሩ ሁኔታ እያደጉ ነው። በተናጠል እየወሰድን ግን ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ስናወዳድር ለዎላይታ ሊኖራት የሚገባትን ቦታ አያገኙም፣ የተናጠል ጉዟቸዉ ብዙ ርቀት አይወስድም።
በቅርቡ እንኳን የዎላይታ ሶስት ከተማ እንዴት ይገባል ተብሎ እየተገባቸዉ ከአለም ባንክ ድጋፍ አይናችን እያዬ ቦዲቲና አረካ ተገፍተዋል። በጋራ በአንድ ከተማ ዎላይታ ሶዶ ሥር ታሪካቸዉንና መረጃዎቻቸዉን እንደያዙ ክፍለከተማ ቢሆኑ የከተማዋ ሕዝብ ቁጥርም ሆነ የቆዳ ሥፋት ይጨምራል፥ በተናጠል ከተሞቹ የሚከብዳቸዉ ነገር በጋራ ቢደራጁ በጣም ቀላል ነው። በጋራ ቢደራጁ ዎላይታ ሶዶ ዉድድሯ ከነ አዲስ አበባ፣ ሸገር፣ መቐለ፣ ባሕር ዳር ጋር ይሆናል።
ይህ ሁሉ ሕዝብ ተሰባስቦ በጋራ የሚኖርባት አንድ ከተማ ስትሆን የሚገነባባት አየር ማረፊያ አለም አቀፍ መሆን አለበት። እንደ አንድ ከተማ በመሠረተ ልማት በመተሳሰር ከአንዱ ወደ ሌላዉ ለመጓጓዝ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል። ዋናዉ Connectivity መጨመር ነው። እንደ አደጉ ሐገራት ወደፊት የዋሻ ሥር የሚሄድ ከተማ ባቡር metro በመሥራት ከአንዱ ወደ ሌላዉ የከተማ ክፍል በቀላሉ ሰዉ ተጉዞ ሰርቶ ዉሎ ሊመለስ ይችላል፣ ያም ከመኪና በፈጠነ ሰዓት በፍጥነት ለመጓጓዝ ያግዛል።
ከተቀሩ የዎላይታ ወረዳዎችም ለሚመጡ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የመጀመሪያ ምርጫ ትሆናለች። የአሁኗን ዎላይታ ሶዶ ለሁለት ብንከፍል ዳሞት ክፍለ ከተማ እና ጦና ክፍለከተማ ወይንም ዲቻ ክፍለ ከተማ በማለት። ቀጥሎ በተጨማሪ ቦዲቲ ክፍለከተማ፣ አረካ ክፍለከተማ፣ ዳልቦ ክፍለ ከተማ፣ ጉኑኖ ክፍለከተማ፣ ሁምቦ ከፍለ ከተማ በማለት ብንከፍል ( በጥናትና ዉይይት መዳበር ያለበት ሐሳብ ነው ) የተሻለ ይሆናል።
በሁሉም አቅጣጫ የሚሰሩ መንገዶች ይህንን ታሳቢ አድርገዉ ተገንብተዉ፣ የባስ ትራንስፖርት በስፋት እንዲጀመር፣ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች፣ መንግስታዊ ተቋዋማት ሲገነቡ ይህንን አንድ ከተማነት ታሳቢ አድርገዉ እንዲሰሩ ማድረግ። እንደ አዲስ አበባዉ ሁሉ በሁሉም ክፍለከተሞች ወደፊት ተመሳሳይ ሕንፃዎችን ገንብቶ የክፍለ ከተማ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ማድረግ።
በመንግስት በኩል የሚመቻቹ የብድር አቅርቦቶችን ከሁሉም የዎላይታ ወረዳዎች በተወሰነ መጠን ወጣቶችን እያመጡ በከተማዋ የሥራ ዕድል መፍጠር።
በኢትዮጵያ ዎላይታ ሶዶ ከ12ኛነት በተከታታይ ከ31ና 32 ያሉትን አረካ እና ቦዲቲን ከሁምቦና ጉኑኖ ጋር ይዛ በኢትዮጵያ ከ1-5 ካሉ ከተሞች ተርታ ትሰለፋለች። በዚህም የሚገባትን መሠረተ ልማት ለማግኘት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፤ ዎላይታ ደግሞ የሚገባት ያ ነው።
በየኢትዮጽያ ከተሞች ከተማረዉ እስካልተማረዉ እየተበተነ ከሚንገላታ የራሱን ቋንቋ እያወራ የሚኖርበት ከተማ መገንባት ለነገ ሊባል አይገባም። ከዚህ በላይ ማርፈድ የለብንም። እነ ገሱባ፣ ባዴሳ፣ ሻንቶ፣ በሌ እንዲሁም የመሳሰሉትም ከሌሎች የኢትዮጵያ ወረዳ ከተሞች ጋር እድገታቸዉን ይቀጥላሉ።
አርሶ አደሩ በቂ ካሳ አግኝቶ የከተማዉ ነዋሪ ሆኖ የሚቀጥልበት አሰራር ከተዘረጋ፣ የሕገወጥ ግምባታ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ከተደረገና ከተሞቹ የማስተሳሰር ዘመኑን የዋጀ ፕላን ከተነደፈ ታላቋ ዎላይታ ሶዶ እዉን የማትሆንበት ምክንያት የለም። አሁን ባለዉ ሁኔታ እንኳን ዎላይታ ሶዶ የዞንና በከፊልም የክልል ከተማ ነች፤ የሚቀላቀሉ ከተሞች የወረዳ መቀመጫነታቸዉ ሊቀጥልም ይችላል፦ የሸገር ቢሮዎች አዲስ አበባ ዉስጥ እንደተገነቡት ማለት ነው።
እነኝህ ከተሞች በጀታቸዉ ከአንድ ማዕከል በአንድ አመራር ሥር ( ከንቲባ ስር ) በተቀናጀ ሁኔታ ከተመራ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ወጤታማ የመሆን እድሉ ይሰፋል። በዚህ ደረጃ ከወዲሁ ማሰብ አለብን፤ በተለይ የዎላይታ ሶዶ፣ የቦዲቲና የአረካ የተናጠል ጉዞ ብዙ አዋጭ አይደለም፣ በጋራ እንደ አንድ ከተማ በቀጣይ ቢጓዙ የተሻለ ይሆናል። ሕዝቡ የሚንቀሳቀሰዉ እንደ አንድ ከተማ እያሰበ ነው ማለት ይቻላል። በአንዱ ሰርቶ ሌላዉ ላይ ወዳለዉ ቤቱ ሄዶ ያድርራል። ዞኑ በዋናነት በዚህ ከተማ ላይ ትኩረት አድርጎ የከተማ ልማት ሥራን ቢያከናዉን የተሻለ ነዉ እላለሁ።
የዳሞት ተራራንም የከተማዉ አካል በማድረግ በጣም በጥሩ ሁኔታ በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ 5ጂ ኔትወርክ ማስፋፋት ቢካሄድ ዎላይታ ሶዶ እንደ ክልል ከተማ ቢካሄድባት ቦዲቲና አረካ የወረዳ ከተማ ተብለዉ ረዥም ጊዜ መጠበቃቸዉ አይቀርም። አንድ ከተማ ከሆኑ ግን በጋራ ያድጋሉ። በተለይ ይህ ብዙ ሕዝብ ቁጥር ያለዉ አንድ ትልቅ ከተማ የመፍጠሩ ነገርም በመንግስትም ሆነ በግል ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ስለ ጥልቅ ማብራሪያው እናመሰግናለን። ነገር ግን በፌደራል መንግስት በኩል ይህ ዘርፈብዙ ጥቅም ያለበት ግዙፍ አላማ በጥሩ አይን ይህ በጥሩ አይን ወይንም በአዎንታ የሚታይ ይመስልዎታል ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኛ እንግዲህ የምንመራዉ በሕገመንግስቱ ነው። ይህ የዎላይታ ዞን መብት ነዉ፥ የፈደራል ሥርአቱ የፈጠረዉ አንዱ እድል ይሄ ነው፤ ይሆነኛል የምትለዉን አጥንተህ ትወስናለህ። ከዛ ዉጪ ይሄ መንግስት “የሕልም ጉልበት፣ ለእመርታዊ እድገት” እያለ ይሄንን ሐሳብ ከተቃወመ የሚገርም ነው። የሚቃወምም አካል ካለ ሕገ መንግስታዊ መብታችን ነውና ለሰፊው ህዝብ ዘላቂ ጥቅም መፍተሔ ብለን መጋፈጥ አለብን። የዎላይታ ሕዝብ የሚበጀዉን አስቦ የመወሰን ሕገመንግሥታዊ መብቱን መጠቀም አለበት።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
WolaitaTimes ሚዲያ, ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን, ስለዘውትር አብሮነታችሁ እናመሰግናለን🙏
#Ethiopia #southethiopia #Wolaita
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የቀረበ ዘገባ ነው