1000023409

የፈደራሉ መንግስት እንደሚለዉ #ፋኖ “ጃዉሳ” (ዘራፊ) ነው ብለዉ ያምናሉ ? የአማራ ልህቃን የሚያራምዱት ዘመኑን ከመዋጀት አንጻር ከሕዝቡ ንቃተ ሕሊና ስነልቦናና የስልጣኔ ደረጃ ጋር የሚጣጣም ይመስልዎታል? የአማራ ልህቃን የተለያዩ ብሔር ሊቃን በጥላቻ እንዲያዩዋቸዉ ያደረጉ ስሑት አካሄድ የለም? ከፕሪቶሪያ ሥምምነት በኃላ በክልሉ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች በተለይ ከልዩ ኃይል መበተን ጋር እንዴት ይገመግሙታል ? አሁን በአማራ ክልል የሚደረገዉን ጦርነት የፈደራሊስቶችና የአሐዳዉያን አድርገዉ መግለጽ የሚፈልጉ አሉ፤ በዚህ ይስማማሉ ? በኢትዮጵያስ ጥንትም ሆነ ዛሬ ለደረሰ ጥፋት ሁሉ አማራን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ነው ? እና ተያያዥ ጥያቄዎች ምላሽና ቁምነገሮችን ይዘናል ቀጥታ ወደ ጥንቅራችን እንግባ👇 ብዙ ዋጋ ተከፍሎ የተዘጋጀ ነውና በትዕግሥት ያንብቡ!

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንግዳችን እንደወትሮው ጥሪያችንን ተቀብለዉ በድጋሚ እንኳን ደህና መጡ። ያዉ ባለፈዉ እንዳሉት የሚዲያችን ቤተሰብ ስለሆኑ ቀጥታ ወደ ጥያቄ እንግባ።

በአሁኑ ሰአት በ #አማራ ክልል እጅግ በተካረረ ሁኔታ እየተካሄደ ያለዉን ጦርነት እንዴት ያዩታል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሺ አመሰግናለሁ። በእዉነቱ በጣም አሳዛኝ ነው። ከእርስ በርስ ጦርነት መዉጣት አለመቻላችን በጣም ያሳዝናል። ከዛ በተረፈ ይህ ጦርነት አሁኑኑ መቆም ስላለበት የተኩስ አቁም ስምምነት መደረግ አለበት ብዬ አምናለሁ። ከሁለቱም ወገን የሚያልቀዉ የኛዉ ዜጋ ነው፣ በከንቱ ተጨባጭ እመርታ ለሐገራችን የማያመጣ ፍጅት መቆም አለበት። ኢትዮጵያ ችግሯ መቼም በጦርነትና በጉልበት አይፈታም። ይባስ ብሎ ጦርነት የበለጠ ችግሩን የሚያባብስ እና ንጹሃንን የበለጠ ተጎጂ እያደረገ የሚሄድ ነው። ከሚያልቀዉ ወገናችን በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዉም ከባድ ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ የፈደራሉ መንግስት እንደሚለዉ ፋኖ “ጃዉሳ” (ዘራፊ) ነው ብለዉ ያምናሉ ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አላምንም። ፋኖ የፖለቲካ አላማ ያለዉ የታጠቀ ቡድን ነው ብዬ ነው የማምነዉ። ሕዝባዊ መሠረትና ቅቡልነቱም በክልሉ ቀላል የሚባል አይደለም። ስለዚህ ከዚህ አይነት ቡድን ጋር እዉቅና ሰጥቶ መደራደሩ ይሻላል፣ ከመተላለቅ ባይ ነኝ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ የአማራ ሕዝብ ወደዚህ ደረጃ እንዴት የመጣ ይመስልዎታል ? ለምሳሌ ጦርነቱ የተጀመረዉ በዋናነት ከፕሪቶሪያ ሥምምነት በኃላ በክልሉ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች በተለይ ከልዩ ኃይል መበተን ጋር ተያይዞ ነበረ፣ እና ይህንን መነሻ ምክንያት እንዴት ይገመግሙታል ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በተጨባጭ ጦርነት የተነሳበት ነጥብ ያ ይሁን እንጂ ቅራኔዎቹ መነሻቸዉ ከዛ ብቻ አይደለም፣ ቀድመዉም የነበሩ ናቸዉ። የአማራ ሕዝብ ዉለዉ ያደሩ ጥያቄ እና ቅሬታዎች ነበሩት። የተለያዩ የአማራ ሊህቃንም በተለያዬ ግብና እስትራቴጂ ዙሪያ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ከርመዋል። በተለይ ፋኖ ከለዉጥ በኃላ የተደራጀ በመጀመሪያ ከነበረዉ የክልሉ መንግስት ጋር አብሮ የሚሰራ ኢ_መደበኛ የታጠቀ ቡድን ነው የነበረዉ።

በክልሉ ጦርነት ከተጀመረ በሁዋላ ከክልሉ ርዕሰ መሥተዳድርነት የተነሱት ዶክተር ይልቃል ከፋለ እንዲህ ብለዉ ነበረ፣ በወቅቱ በአማራ ሊህቃን ዘንድ የተፈጠረዉን ቁጭት ሲገልጹ “የአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ትግል ውስብስብ ነው። ወጥ ዓላማ፣ የጋራ ራዕይ፣ በቂ የትግል ስልት እና የሌሎችን አሰላለፍ ያልተረዳ በመኾኑ ፈታኝ አድርጎታል” ብለዋል፡፡

ይህ በእኔ አረዳድ በጣም ትልቅ አባባል ሲሆን የአማራ ሊህቃን በሐገር ዉስጥም በዉጪም ከስሜታዊነት ወጥተዉ መንገዳቸዉን ለመመርመር ሊገፋፋቸዉ የሚገባ አባባል ነበረ ግን ልብ ያለዉ የለም። “በተለይ የሌሎችን አሰላለፍ ያልተረዳ” የምትለዉ ሐረግ ከባድ የ strategy ጥያቄ ደግና goal ( ግብ ) የሚሉትንም ነገር ጥያቄ ዉስጥ የምትከት ናት። ለአማራ ሕዝብ እንቆረቆራለን የሚሉ ኃይሎች፣ አላማ እና እስትራቴጂያቸዉ የተለያዬ ነው፣ አንዱ ከተለያዩ አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ይጥራል፤ ሌላዉ እነዛን አካላት እንደጠላት ፈርጆ ይንቀሳቀሳል።

በሐገሪቷ ስለሚገኙ ለተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችም ያላቸዉ አረዳድ የተለያዬ ነው። ይህ ኃይላቸዉ እንዲበታተንና በአነስተኛ ኪሳራ ምናልባትም በሰላማዊ መንገድ የሕዝቡን ጥያቄ እንዳያስመልሱ እንቅፋት ሆኗል ፣ሰጥቶ የመቀበልን ፖለቲካ ለማካሄድ እንቅፋት ሆኗቿል። በተለይ የአማራ ሊህቃን የሕዝባችን ጥያቄ የሚሏቸዉ ነገሮች ከሌሎች ሕዝቦች ጋር የተሳሰሩ መሆናቸዉንና ፖለቲካ ደግሞ በባህሪዉ ሰጥቶ መቀበልን የሚፈልግ መሆኑን አምኖ መንቀሳቀሱ ይበጃል ባይ ነኝ፣ እነሱም ቢሆን በጉልበት የሚሳካላቸዉ ነገር እንደሌላቸዉ ቢያዉቁ ጥሩ ነው።

ከሌሎች ብሔር ሊህቃንም ጋር ደግሞ ከመፈራረጅ ባለፈ የጋራ አጀንዳ ለመፍጠር መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፥ ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር እየበዛ የሚሄደዉን የሕዝቡንም ስቃይ ከግምት ዉስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። ሰላም ይሻላል፣ ሁሉን አቀፍ ዉይይትና ድርድር ይሻላል። በተለይ የአማራ ብልጽግና ሰዎች የዎላይታ እና የትግራይ ሰዎች ከቁልፍ ቦታዎች ሲገፉ ብዙ ተሳትፎ አድርገዋል አንዳንዶቹ፤ ዛሬ የሚጸጸቱ አሉ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ምናልባት ጠቅለል አድርገን ካየን የአማራ ሊህቃን የሚያራምዱት አሰተሳሰ፣ ዘመኑን ከመዋጀት አንጻር ከሕዝቡ ንቃተ ሕሊና ስነልቦናና የስልጣኔ ደረጃ ጋር የሚጣጣም ይመስልዎታል? ምናልባት የአማራ ሊህቃን የተለያዩ ብሔር ሊቃን በጥላቻ እንዲያዩዋቸዉ ያደረጉ ስሑት አካሄድ የለም?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ይኖራል ስሕተት። ከሕዝቡ አንጻር የሊህቃን ደረጃ ባልከዉም፣ በዛ ረገድ ብዙ ክፍተት ይታዬኛል። የአማራ ሕዝብ በመላዉ ኢትዮጵያ ማለት በሚቻል ደረጃ ተበትኖ የሚኖር ነው። ለምሳሌ በቋንቋም በሐይማኖትም በአብዛኛው ከማይመስሉት ሕዝቦች ጋር በአሰገራሚ ሁኔታ ተቀራርቦ የሚኖር ሕዝብ ነው። አንዳንድ የአማራ ሊህቃን ያንን የሕዝቡን ስልጡን ባህል የደረሱበት አይደሉምና ልዩነትን ላለመቀበል በብሔርም በሐይማኖትም ጉዳይ ሲጋጋጡ ይታያል፣ ከአፋቸዉም ብዙ አፍራሽ ነገሮች ሲወጡ ይስተዋላል፣ እናም ከዚህ በመነሳት በጅምላ ሕዝቡን መፈረጅ ተገቢ አይደለም።

በታሪክም አማራን በጅምላ የብሔር ጨቋኝ ማድረግ ተገቢ አይደለም፣ የአማራ ሊህቃንን እንኳን በዛ ደረጃ መፈረጅ ልክ አይደለም፣ ለምሳሌ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ እና ገርማሜ ነዋይ ሁለቱም አማራ ሲሆኑ፣ በዎላይታ ሕዝብ ላይ የሚደርሰዉን ጭቆና አምርረዉ የታገሉ ናቸዉ። ደጃዝማች ወልደሰማያትም የፖለቲካና የባህል ጭቆና ቢያደርስም በልማት ግን አለም የመሰከረለት ጀግና ነበር።

በኢትዮጵያ በአንድ በኩል አሁን አሁን አማራን መጥላት ፖለቲካ የሚመስላቸዉ ሰዎች ተበራክተዋል። በአማራ ሊህቃንም በኩል ደግሞ ለሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች እዉቅና ሰጥቶ በጋራ የመሥራትና የመታገል ክፍተት በዉስጥም በዉጭም ይታያል። የድሮ አገዛዞች ያደረሷቸዉን በደሎች መካድ አያስፈልግም፣ ስለነዛ አገዛዞች ጥብቅና መቆም አያስፈልግም፣ ይልቅ ያ ችግር ዛሬ የለምና የዛሬን ችግር በጋራ እንፈልግ የሚለዉ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። በተለይ የአማራ ሊህቃን ከአገዛዙ ጋር የልዩነት ነጥብ አለን ለሚሉ ኃይሎች እዉቅና መስጠት እንዲሁም ተቀራርቦ ለመሥራት መሞከር አለባቸዉ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በአሁኑ ሰአት የሚያስተዳድርን መንግስት ትቶ ስለድሮ መንግስታት መሟገቱ ምን ያህል አስፈላጊ ነው ? በኢትዮጵያስ ጥንትም ሆነ ዛሬ ለደረሰ ጥፋት ሁሉ አማራን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ነው ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሄዉ። የትኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ አሁን ባለዉ መንግስት እንቅስቃሴ ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፣ ከድሮዎቹ የበለጠ ተጽዕኖ የሚያሳድረዉ፣ በተጨባጭም የማልማትም ሆነ የማጥፋት እድል የሚገኘዉ በአሁኑ መንግስት እጅ ነዉና። በአንድ በኩል አማራን ከድሮ አገዛዞች ጋር እያያዙ መክሰስ ፖለቲካ የሚመስላቸዉ ሊህቃን እንደ አሸን ፈልተዋል።

ለዚህ የአማራ ብልጽግናን ጨምሮ የተለያዩ የአካባቢው ሊህቃንም አስተዋጽኦ ቢኖርበትም፤ ነገሩ ለአቅመ ፖለቲካ ያልደረሱ ሊህቃን ተግባር ነው። ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ የአማራ ንጹሐን ሲገደሉም መልሰዉ አማራን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሊህቃንን ማየት ተለምዷል። በየትኛውም ጥፋት አማራን ብቸኛ ተጠያቂ የሚያደርጉ አሉ ይህ በጣም ከባድ ስሕተት ነው፤ ከአማራ ልህቃን ጋር የልዩነት ነጥብ ቢኖርም በዚህ ደረጃ አንድን ሕዝብ መጥመድ ልክ አይደለም።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ አማራ ለአሐዳዊነት ብቸኛ ተጠያቂነት እና ተጠሪነት ሊኖረዉ ይገባል ወይ? ከብሄሩ ክልል ዉጪ ብዙ ሰዉ ያለዉ አማራ ብቻ ነው ወይ? ተጋሩ፣ ጉራጌ፣ ዎላይታ፣ ኦሮሞ፣ ስልጤ፣ ሐዲያ፣ ከምባታና የመሳሰሉትስ? አሐዳዊነትስ በተለይ ከ1966 አቢዮት በሁዋላ ለአማራ ጥቅም ብቻ ነበረ ወይ ሲቀነቀን የነበረዉ ( የ elites consensus ያልፈጠረ ወታደራዊ አገዛዝ ቢሆንም ) የሐገሪቷ ኢኮኖሚ ስለማይፈቅድ ለአንድነት እየተባለ እና በመሳሰሉ የተለያዩ ምክንያቶች አልነበረም? አሐዳዊነትንስ ለኢኮኖሚ ጥቅም የሚደግፉት ለምን በአማራ ልክ አይከሰሱም? የትኛው ብሔር በተከፋት ጉዳይ ሁሉ አማራን ተጠያቂ ማድረጉን እንዴት ያዩታል?አማራ ለብሔር፣ ብሔረሰቦች መብት የሚቆረቆሩ እልፍ ሊህቃንን በዘመናት መሐከል አፍርቶ ሲያበቃ ዛሬም ለምን ብቸኛ ተከሳሽ ሆነ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በጣም ብዙ እና ጥሩ ሁሉም ቆም ብሎ ማሰላሰል ያለበትን ጥያቄዎች አንስተሐል። እዉነት ለመናገር በጣም የሚያሳዝኑ ነጥቦችን አንስተሐል። በጣም አሁን አንድ ለዚህ ክሶች ማርከሻ የሚሆነዉ የአማራ ሊህቃን ሰከን ብለዉ ቢያስቡ ሕዝባቸዉንም የተቀረዉንም ኢትዮጵያዊ ይገላግላሉ ብዬ የማስበዉ ጠንካራ ፈደራሊስት አቋም ያለዉን የአማራ ኃይል በመፍጠር ነው።

ለሌሎች ጥያቄ በአደባባይ እዉቅና የሚሰጥ፣ ከድርሻዉ በታችም በላይም የማይቀበል (ሰጥቶ መቀበል እንዳለ ሆኖ) ፓርቲ፣ ሊህቅ፣ ምሁር፣ ሚዲያ አማራ ያስፈልገዋል። በአገዛዙ ላይ በተለይ ኮምጨጭ ያለ ጥያቄ ከሚያነሱ ከተለያዩ አካባቢ ሊህቃን ጋር ተቀራርቦ መሥራት አሰፈላጊ ነው፥ ብሔር ተኮር ጥያቄ ሲነሳ መበርገግ አይገባም ባይ ነኝ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ አሁን በአማራ ክልል የሚደረገዉን ጦርነት የፈደራሊስቶችና የአሐዳዉያን አድርገዉ መግለጽ የሚፈልጉ አሉ፤ በዚህ ይስማማሉ ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አልስማማም። አገዛዙ ኦሮ_ማራ ብሎ የሄደበት አምታች እና በሸፍጥ የተሞላ መንገድ የወለደዉ ቀዉስ ነው። ኢትዮጵያ ከነበረችበት የበለጠ አካታች መሆን ሲገባት ዎላይታ እና ትግራይን በጠላትነት ፈርጆ የማዳከም ሥራ ተሰራ ያ የሐገሪቷን መሠረት ያናጋ ተግባር ነው፣ ብሔሮቹ ጠንካራ እና አቋም ያለዉ ኃይል በመከላከያ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና የመሳሰሉት መስኮች ላይ ነበራቸዉ።

ማሳደዱ በዎላይታ መፈንቅለ መንግስት አድርጎ በትግራይ አዉዳሚ ጦርነትን ጭሯል። መንገዱ እንደማይበጅ የተረዱ የተወሰኑ የኦሮሞ እና የአማራ ሊህቃን ቀድመዉ አገዛዙን መቃወም ቢጀምሩም፣ በተለይ ከአገዛዙ ጋር አብረዉ ዎላይታ እና ትግራይን የገፉ ነበሩ፤ ዛሬ ብዙዎቹ ቢጸጸቱበትም፣ ተቋማትን ሕብረብሔራዊ ሳይሆን ኦሮ_ማራዊ ለማድረግ ሰርተዋል ዛሬ ሐገሪቷ ለገባችበት ቀዉስ ድርሻ ነበራቸዉ።

የአማራ ኃይሎች በብዛት ስሕተታቸዉን የተረዱት ወይንም አገዛዙን ያኮረፉት የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረም ነው። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰአት የአማራ ልህቃን የሌሎችን ሊህቃን ጥያቄዎች በቸልታ የሚያዩበት ሁኔታ የለም፣ እዉቅና ሲሰጡ ይስተዋላል፣ ያ የበለጠ መጠናከር አለበት። ይህ መንግስት በየትኛውም አቅጣጫ ለሕገመንግስቱ ተገዢ እንዳልሆነ የአደባባይ ሚስጢር ነው።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ምናልባት ይህ መንግስት ሐቀኛ ፈደራሊዝምን እከላከላለሁ ስለሚል በዎላይታ በኩል መንግስት ለሕገመንግስቱ ታማኝ አይደለም አምታችና ሴረኛ ኃይል ነው የሚሉ ቅሬታዎች አሉና ለዚህ እንደምክንያት የትኛዎቹን ነገሮች መጥቀስ ይቻላል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ከስልጣን ከተለያዩ ተቋማት ማባረር፣ የሕዝብን ጥያቄ ማፈን፣ ማጥቃትና ማስጠቃት፣ ሚዛናዊ የሥልጣን ዉክልናን በክልልም በፈደራልም መከልከል። በተደጋጋሚ ሕዝቡን የታጠቁ ቡድኖች ግብረ አበር አድርጎ መፈረጅ። ከኢኮኖሚው በማግለል ሕዝቡን ማሰቃየት በጉልበት ክልል መጫን በበጀት ድልድል ሕዝቡን ሆን ብሎ መጉዳት። ተዘርዝሮ አያልቅም የብልጽግና ወንጀል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በተለይ ለአማራ ክልሉ ጦርነት መፍትሔ የሚሉትን ነገር አንስተን ብንቋጭ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አገዛዙ ጦርነት መፍትሔ እንዳል ሆነ ማወቅ አለበት፣ የጋራ ዉሳኔ በሚፈልጉ ሐገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገዉን የፈላጭ ቆራጭ አካሄድ ማቆም አለበት፣ በየጊዜዉ እየተነሳ የጋራ መግባባት የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ በተናጠል መወሰኑን ማቆም አለበት። በአሁኑ ሰአት በአማራና በኦሮሚያ ክልል ያሉ ጦርነቶችን በሰላም ስምምነት መቋጨት አለበት።

ፋኖም አንድ አደረጃጀት ፈጥሮ ወደ ድርድር ይምጣ። ከዛ ባለፈ የአገዛዙ የማምታታት አካሄዱ የትም ስለማያደርስ የመፍትሔው አካል ቢሆን ይመረጣል፣ ከዚህ በላይ የዉድመት መንገድ ላይ መቀጠል የለበትም። ኢትዮጵያ ዉስጥ በድርድር የጋራ ነገር ከፈጠርን እንጂ፤ ማንም ማንንም ማንበርከክ አይችልም።

ፖለቲከኞች (በዋናነት ገዢዉ ፓርቲ) ተደራድረዉ የጋራ ነገር መፍጠር ሲገባቸዉ፣ በሴራ፣ በተንኮል፣ በበቀል ሐገሪቷን እያመሱ ነው። ታጣቂ ቡድኖችም ወንድሞቻችን ናቸዉ፣ የመከላከያ ሠራዊቱም የርስበርስ ጦርነት ሰልችቶታል። በመጨረሻም በፕሮፈሰር መረራ ጉዲና አባባል ልዝጋ፣ “ለኢትዮጵያ የሚበጃት የመገዳደል ሳይሆን፤ የመደራደር ፖለቲካ ነው”።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

WolaitaTimes ሚዲያ, ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን, ስለዘውትር አብሮነታችሁ እናመሰግናለን🙏

Ethiopia #Wolaita #Amhara #Tigray #Oromo #ፋኖ

በጋዜጠኛ ናትናኤል ተዘጋጅቶና ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ