ሰበር ዜና
የደቡብ ኢትጵያ ክልል የፖለቲካ ብልሽቶችን በተመለከተ ከ12ቱ ዞኖች የተዉጣጡ ምሁራኖች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋዊ ደብዳቤ አቀረቡ።

ከክልሉ ከሁሉም አከባቢ የተወጣጡ ምሁራኖቹ ያቀረቡት ደብዳቤ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደሚከተለው ደርሰዋል።
“ይድረስ ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ
አዲስአበባ፤
ጉዳዩ፡- የደቡብ ኢትጵያ ክልል የፖለቲካ ብልሽቶችን በተመለከተ ከ12ቱ ዞኖች የተዉጣጡ ምሁራኖች የተላከ ይፋዊ ደብዳቤ
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስተራችን ትጋትና ቁርጠኝነት የተደራጀና የለዉጡ ትሩፋት ዉጤት እና የእዉነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ማሳያ ከሚጠቀሱት ክንዉኖች አንዱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ ነዉ።
ይህ አደረጃጀት የህዝቦች የዘመናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ቀስ በቀስ ይፈታል ተብሎ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ብሆንም በአንድ ዓመት ቆይታዉ ለህዝቦቿ ተጨማር ዕዳ እየሆነ ይገኛል፡፡
የብልፅግና ፓርቲዉን ምሶሶዎችን በተጻረረ መልኩ በተላይም መከፋፈልን እና አግላይ የፖለቲካ እሳቤ የወጣ አካታችነትን፣ ሚዛናዊነትን እና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን፣ ወንድማማችነትንና እህትማማችነት ከማፅናት ይልቅ በተቃራኒዉ ቅመኝነት፣ በቀለኝነት፣ ቡድንተኝነት፣ ኢ-ፍትሀዊነት፣ አግላይነት፣ የየአካባብዉ ገዥነትና የነጠላ ትርክት የበላይነት… ወዘተ የነገሰበት ክልል መሆኑን በተጨባጭ ማስረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ሌላዉ የማንደብቀዉ ሀቅ ለህዝብ ደንታ በሌላቸዉ ካድረዎች ምክንያት ፓርቲዎ ከህዝቡ ልብ የወጣ እንደሆነና እያደረ በሄደ ቁጥር ለሀገርቱ ተጨማር የፀጥታ ስጋት እንደሚሆን ከወድሁ ለመጠቆም እንፈልጋለን፡፡
በመሆኑም ክልሉ ከተደራጀ በአጭር ጊዜ የተፈፀሙ የአመራር ጥቅት ብልሽቶችን በሚከተለዉ መልኩ እየዘረዘርን ትክክለኛነቱን በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ተገቢዉ እንድደረግ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡
በክልሉ ያሉ ችግሮች ዋናዎቹ፦
👉 ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት/እህትማማችነትን እና ክልላዊ አንድነት መሸርሸርና ስርዓት አልበኝነት መስፈንና ለማረም የአመራር ዝግጁነት ያለመኖር
👉 በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴራ ፖለቲካ መጎንጎን፤ የመጠላለፍ፣ የመጠቃቃትና መጠቃቀም የክልሉ ብልጽግና ከፍተኛ አመራሮች ልዩ ባህርና ተግባር ሆኖ ይገኛል።
👉 የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የክልሉን ህዝብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በወል እውነትና በመሪህ ላይ ቆሞ ከመፍታትና ከማገልገል ይልቅ በተለያዩ ነጠላ ጉዳዮች ዙሪያ በጎራ በመከፋፈል በቡድንተኝነት ፖለቲካ በመተራመሳቸው ምክኒያት በሀዝቦች መካከልም አለመተማመን እና እርስ በእርስ መጠራጠረዎች እየተፈጠሩ ይገኛሉ።
👉 በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መካከል እየታየ ያለው የመጠላለፍ ፖለቲካ በፍጹም የብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካ እሳቤ አለመሆኑን ብንገነዘብም አመራሩ ብልጽግና አባል ስለመሆኑ የምነግረን አካል ማግኘት ባለመቻላችን በህዝብ ውስጥ ከፍተኛ ጥርጣሬ ፈጥሮ ይገኛል። ይህም ክልሉ እንዳይፈርስ ከፍተኛ ስጋት ሆኖብናል።
👉 ለከልሉ የመፍረስ ዋናው ስጋት ደግሞ ክልሉ አሁን በተደራጀው ቅርጽ እንዳይደራጅ ከክልሉ አደረጃጀት በፊት በአቶ ጥላሁን ከበደ አማካይነት በህቡዕ ተደራጅተው ስሰሩ የነበሩ የሴራ ፖለቲካ አራማጅ ኃይሎች ተጠራርተው የፊት አመራር በመሆን ካለእነሱ ፍላጎት ውጭ የተደራጀውን ክልል ለመምራት ስልጣን የያዙ መሆናቸው ነው።
👉 ፍላጎታቸው የነበረው ከዎላይታ ውጭ እንደራጃለን የሚል ሆኖ አሁኑ የተደራጀው ክልል ዎላይታን ያካተተ በመሆኑ አሁን እየታየ ካለው ተግባር አኳያ ስመዝን ክልሉን አፍርሰው ቀደም ስል አቅዶ ያልተሳካውን የራሳቸውን ወደራሳቸው ፕሮጀክት እንዳይመልሱ ከፍተኛ ስጋት ይታያል።
👉 የፓርቲዉን እሳቤ በአካታችነትና አቃፊነት ተደምሮ መፈጸም ቢሆን ከዚሁ በተቃራኒው ከመደመር ይልቅ በመከፋፈል፣ ከመደጋገፍ ይልቅ በመገፋፋት፣ ከመተባበር ይልቅ በጎራ መቧደን፣ ከፍቅር ይልቅ በጥላቻ፣ ከአካታችነት ይልቅ በአግላይነት እሳቤ እሳቤ እየተሰራ ያለው የአመራሩ ሴራ ፖለቲካ የአመራሩ ሁኔታ ካልተስተካከለ በብዛሀነትና በህብረ ብሔራዊነት የተደራጀውን ደቡብ ኢትዮጵያን ክልል ብዙ ርቀት ሳይሄድ በቅርብ ጊዜ አደጋ ላይ እንደምጥል ከወዲሁ የፖለቲካ ሁኔታው ያሳያል።
👉 የክልሉ ህዝቦች በብዙ በጋራ እሴቶች የተሳሳረ፣ የተጋባ፣ የተዋለደና የተጋመደ ቢሆንም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የክልሉ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከማጠናከር ይልቅ ለወጣበት አከባቢ መቆምና ራሳቸውን የወጡበት አከባቢ አባወራ አድርጎ በመንቀሳቀሳቸው ምክኒያት በክልሉ የየአጎራባች ህዝቦች የሀሳብና በየጊዜው የሚቀያየር የፓለቲካ አካሄድ ልዩነት በጋራ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ የጋራ መድረክ ፈጥሮ በቅንነት ከመስራት ይልቅ ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ተጨማር አጀንዳዎች የመዝራት አባዜ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
👉 በአደረጃጀት ሂደቱ ላይ የነበሩ ጉልህ ስህተቶችና ክልሉ ከተደራጀም በኋላ እየተፈፀሙ ያሉ የመልካም አስተደዳር ጉድለቶች፣ የሥልጣን ላይ ብልግና፣ የሕግ የበላይነት መጥፋት፣ የክልሉ አስተዳደራዊ ወሳኔዎች መርህ አልባ መሆን አሁንም ቀጥሏል።
👉 የክልሉ አደረጃጀት፣ ማዕከል ከተሞች ምርጫ፣ ተቋማት ስርጭትና በስልጣን ክፍፍል ላይ የተፈጠሩ ከፍተኛ ሽኩቻዎችና ተቃርኖዎች ሳይታረሙ በችኮላ ወደ ክልል ምስረታ መገባቱ፣ በክልሉ ሀብት የሚያስተዳድሩ ቢሮዎችን በመደልደል ሂደት የተፈጠሩ አድሏዊና ግልፅነት የጎደላቸው አሠራረሮች ለክልሉ አለመረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
👉 በዚህ ምክኒያት የፍትሐዊነትና የዕኩልነት መርሆዎችን በመጣስ አንዱን የህብረሰብ ክፍል አለአግባብ በመጥቀም ሌላውን አለአግባብ የሚጎዳበት አደገኛ ተጨባጭ አዝማሚያዎች መኖር በክልሉ ህዝብ ዘንድ መጠራጠር፣ መተማማትና የባለቤትነት ስሜት እንዳይሰማቸው ፍትሃዊነትና ግልጸኝነት የጎደለው ውሳኔዎችና አሰራሮች፣ የራስ ቡድን በማደራጀት በቡድን አማካኝነት የደቦ ውሳኔዎችን በማሳለፍ መቃቃርን እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
👉 ይህን ሁሉ የሚያደርጉበት ምክኒያት በአንድ በኩል የራሳቸውን የግል ጥቅም ለማግበስበስ፣ በሌላ በኩል አገራዊ ለውጡን ማደናቀፍ ሲሆን በህዝብ ይሁንታ የተመረጠው መንግስትና ብልፅግና ፓርቲው በህዝብ ዘንድ አመነታ እንድያጣ እየተደረገ ይገኛል።
👉 በፓርቲው ሕልውና ላይ የተደቀነው የአመራርና አከባቢያዊ ቡድንተኝነት መንገስ የክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ አሁናዊ የፖለቲካ አሰላለፍ በተመለከተ ለሶስት ጎራ የተከፈለ ነው። አንደኛው ጎራ (የርዕሰ መስተዳድሩ ሃሳብ ደጋፍ፤ ሁለተኛው ተቃዊሚ እና ሶስተኛው ራሱን መሀል ሰፋሪ በማድረግ) ጎራ ተለይቶ መካረር ተጀምሮ ቆይቷል። ይህም ከክልል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የዘለቀው ነው።
👉 በሴራ የተደራጀዉ አስተባባሪ ኮሚቴዉ ከአገራዊ ራእይ በተቃራኒ ስለቆሙ የክልሉ ህዝብ ገና ሳይደራጅ ሌላ ሀሳብ ውስጥ እንዲገባ ተስፋ እንድቆርጥ ለማድረግ በየዞኑ አጀንዳ ተፈብርኮ የሚሰጠው በክልሉ ቁልፍ አመራሮች ነው፡፡
👉 በአንድ ዞን ሁለት ቡድን በማደራጀት አንዱ አንዱን እንድመረጅ በመደረጉ ለአብነት ጋሞ ዞን፣ ኮንሶ ዞን፤ ዎላይታ ዞን፣ ደቡብ አሞ ዞን፣ ጎፋ ዞን፣ ባስኬቶ ዞን፣ ቡርጂ ዞን፣ ጌዴኦ ዞን…ወዘተ የዚህ አደረጃጀት ሰለባ ሆነዋል፡፡
👉 ለዘመናት አብሮ በአንድ ዞን ተደራጅቶ የኖሩ ያሁኖቹ የአሪና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በጦርነት ውስጥ ናቸው፡፡ በአሁኑ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ በሆኑት በአቶ ዓለማየሁ ባዉድ በሚመራዉ ሰሬኛ ቡድን እና በአቶ ንጋቱ ዳንሳ በሚመራዉ ሚዛናዊ እይታ ባላቸዉ ቡድኖች ትግል ላይ ናቸዉ፡፡
👉 ጋሞ ዞን በማንነት ቀዉስ ዉስጥ በሚገኝ በአቶ ጥላሁን ከበደ በሚመራ ቡድንና እዉነተኛ ጋሞዎች እኛ ነን በሚል ፍልምያ ዉስጥ ዉስጡን እየተናጠ ይገኛል፡፡ ጋሞነት እንደ አየር ሁኔታዉ የሚቀበሉ ርዕሰ መስተዳድሩ በአሁናዊ ሁኔታቸዉ የጋሞ ልማት አርበኛ ነኝ ነጠላ ዜማ በኔትዎርካቸዉ አማካይነት እንድዘመር እያደረጉ በመሆናቸዉ ድል የቀናላቸዉ ይመስላል፡፡
👉 የቀድሞ ሰገን ዞን ተብሎ የሚታወቁ አከባቢዎች በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ናቸው፡፡ በአቶ ዳዊት ገበየሁ ሰሬኛ ቡድን እና በአቶ ሃልጋዮ ጅሎ በሚመራዉ ቡድን ምክንያት በየቀኑ የሰዉ ህይወት እየበላ ይገኛል፡፡
👉 የጎፋ ዞን ደግሞ በአቶ አክልሉ አዳኝ በሚመራዉ ሴረኛ ቡድን እና በእሱ በተገፉት የህዝብ ቅቡልነት ባለባቸዉ ወጣት አመራሮች እየተናጠ ይገኛል፡፡
👉 ጌዲኦ ዞን በክልሉ ፕረዝዳንት የሚደገፍና በህዝብ ተጠልቶ በምርጫ ጭምር ተሸንፎ ብልጽግናን የጣለውና ያዋረደው አቶ ሃይለማርም ተስፋየን አስተባባሪ አደርጋለሁ በሚል እና በህዝብ ቅቡልነቱና በእውቀቱ ተወዳዳሪ የሌለው ዶ/ር አባባዬሁ ታደሰን “አነሳለሁ” በሚል ቅዠት ጌዴኦን እያበጣበጠ ይገኛል፡፡
👉 በዎላይታ ዞን ከ40 ዓመት በላይ በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ ራሳቸዉ አባት እርሻ ማሳ ከአንዱ ስልጣን ወደ ሌላ ስልጣን በሚሽከረከሩ በአቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ በአምባሳደር ተሾመ ቶጋ እና በአቶ ገብረመስቀል ጫላ ዘመዶችና ጎሳዎች በተፈጠረዉ አደረጃጀትና ይሄን በሚቃወም ቡድን እየታመሰች ይገኛል፡፡
👉 ኮሬ ዞን በክልሉ ፀጥታ ቢሮ ሃላፍ በሆኑት በአቶ ወገነ በሚመራ ቡድንና በጋሞ ስነ-ልቦና ባላት የመንግሰት ኮሚኒዩኬሽን ቢሮ ሃላፊ በሆኑት በወ/ሮ ሰናይት ቡድን
ቡርጂ ዞን በጋሞ ስነ-ልቦና ባለዉ በክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ በሆኑት በአቶ እንዳሻዉ እና በዞኑ አስተዳዳሪ በሚመራዉ ቡድን ሌሎች ቀሪ ዞኖችም በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በሚደገፉ ትናንሽ ገዥዎች እጅ ወድቀዋል፡፡
👉 የክልሉ መንግስት በዞኖቹ ውስጥ ጉዳዮች በመግባት የህዝብ ፍላጎት እንዳይሳካና በአከባቢው የውስጥ አንድነት እንዲጠፋ በየሳምንቱ ሹም ሽረት እየተካሄደ ይገኛል
በክልሉ የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት የቡድን መንፈስን በመጠበቅ ተግባብቶ ተልዕኮን ለመፈፀም አለመቻል፤ ፀረ ዲሞክራሲያዊ የሆኑ ተግባራትን መፈፀም፣
👉 ጫፍ የረገጠው የአመራር ብልሽትና የአሰራር ጥሰቶች ላይ መዘፈቅ ህግና ስርዓትን ተከትሎ ከመስራት ይልቅ ስልጣንና ኃላፊነትን ያለአግባብ በመጠቀም የከተማና የገጠር መሬት ጨምሮ የመንግስትና የህዝብ ሀብትና ንብረትን መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበር፣
👉 እንዲሁም በጉቦ፣ በትውውቅ፣ በአከባቢያዊነት፣ በጎሰኝነት፣ በዘመድ አዝማድነት፣ በፖለቲካ ወገኝተኝነት እና በኃይማኖት ትስስር በመመርኮዝ ፍትህን እያዛቡ የግል ጥቅምን ማካበትና ይህን ስህተት ለማረም የሞከረውን በሙሉ መፈረጅ፣ ማሳደድና ማጥቃት የክልሉ የፊት አመራሮች ባህሪይ ሆኖ ቆይቷል።
👉 በክልሉ ፌዴራል ባለሥልጣናት ተዋናይ እንደሆኑት የሚጠረጠረው ከጥቂት ዘራፊ ባለ ሀብቶች ጋር በመመሳጠር በፕሮጀክቶች፣ ከድንጋይ ከሰልና ከሌሎች ማዕዳናት፣ የእርሻ መሬትና የከተማ መሬት ምዝበራ፣ የሆቴል መስተንግዶዎች ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ አሻጥሮች መብዛት፥
👉 የኮንትሮቫንድ ንግድ ቀጥተኛ ተሳትፎ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አመራርና በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በጋራ ቅንጅት በዲላና በኮንሶ መስመር ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ሆኗል፡፡
👉 በጋሞ ዞን በ2010 እስከ 2014 ዓ.ም በዞኑ አስተዳዳሪ በነበሩና የአሁኑ የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ በአቶ ብርሃኑ ዘዉዴ ከክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት እውቅና ውጪ የመሬት መጠን 103,410.3 ካሬ ሜትር መሬት በምደባ በማስተላለፍ በምትኩ የግል ሀብት ማካበት ከአመራር የማይጠበቅ ውሎና ስነምግባር ብልሽት
ከአካባቢዉ ማህበረሰብ ባህልና ወግ ባፈነገጠ፣ ከአመራርነት ስብዕናና ስነምግባር የሚጻረሩ ድርግቶችን መፈፀም።
👉 ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም፣ በስራ ሰዓት ውሎውን መሸታ ቤት ማድረግ፣ አለፍ ስል መዛት በጦር መሣሪያ ማስፈራራትና ከህዝብን መንግስት አደራ ከተሰጠ አመራር የማይጠብቁ ተግባሮችን መፈጸም የአመራሩ ባህል ሆኖ ይገኛል።
👉 የፓርቲዉንና የመንግስትን ስም የሚያጎድፍ ድርግት መፈፀም፣ ሰሴኝነት በተለይ ወጣት ሴት እህቶቻችንን ከአከባቢው ባህል ባፈነገጠ መንገደሰ፤ ለወስብ ማስገደድ፤ ጠጥቶ ስክሮ በዜጎች ላይ ሽጉጥ መተኮስ፤ በዲች ዉስጥ ማደር…ወዘተ
👉 የፓርቲን ተልዕኮና የጋራ ውሳኔዎች በጠበቀ ሁኔታ ከላይ ወደታች የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ከመፈፀምና የሥራ አቅጣጫዎችን ከመከተል ይልቅ የግል ፍላጎትን ማዕከል አድርጎ መንቀሳቀስ፣
👉 በእውነተኛ የግንኙነት መሰረት ላይ በመቆም ስልጣንን ተቀብሎ ህዝብን በቅንነትና በግልፅኝነት የማገልገል ባህል በጣም ደካማ በመሆኑ በሀዝቦች መካከልም አለመተማመን እና እርስ በእርስ መጠራጠር ውስጥ እንዲገቡ ካደረገ ሰነባብቷል፡፡ ይህ ደግሞ ለተመሳሳይ አላማ ህብረተሰቡን አንቀሳቅሶ አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ፈታኝ ከባቢን ፈጥሯል፡፡ ይህም ደግሞ በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰዉ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ እንቅስቃሴዋ የተገደበና ወደ መፍረስ የምትመራ ክልል እንድትሆን አድርጓታል፡፡
👉 በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰሩ በተለይ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ ኢንሼቲቦች አንድ እንኳን በክልሉ ዉጤታማ ልሆኑ አልቻለም፡፡ በግል ባለሀብቶች ደረጃ የተሰራውን የእርሻ ልማቶች መጎበኘት ማንን ለመሸወድ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህ የሽወዳ ፖለቲካ ዲስኩር ህዝቡን ከደኢህደን ፖለቲካ በላይ አንገሽግሾታል፡፡
👉 ማህበራዊ ልማት መስክ ከመቸዉም ጊዜ በላይ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ለአብነት አብዘኛዉ ት/ቤቶች ላይ ተማሪዎች እየተማሩ አይደለም፡፡ጤና ተቋማት ተገቢዉን አገልግሎት መስጠት በማቆማቸዉ ህዝቡ በወረርሽኝ እያለቀ ይገኛል
የግብርና ባለሙያ ወርደዉ ለአርሶ አደር ድጋፍ ከመስጠት ካቆመ ሰነባብቷል በወረዳ እና በቀበሌ አካባብዎች ከዞንና ከክልል ተገብዉ ድጋፍ ባለመኖሩ ህዝቡ አገልግሎት እያገኘ አይደለም በተወሰኑ ግለሰቦች ጥረት የተሰሩ ትናንሽ ሥራዎች ፎቶ ከኦሮሚያ አካባብ ከተገኙ ፎቶዎች ጋር በማቀላቀል የአመራሩ የፎቶ ድራማዉ በማህበራዊ ሚድያ ይለቀቃል
👉 የፓርቲ ተቋማዊ አሰራርን ባልተከተለ መልኩ በተለያዩ ጊዜ የፓርቲዉን ስልጠና የወሰዱ ከ1400 የሚበልጡ ወጣት አመራሮች ላይ እርምጃ እንዲወሰድባቸዉ ማድረግና ያለ ግብራቸዉ መልካም ስማቸዉን ማጠልሸት አልፎም ማሳሰር በምትካቸዉ የሚሾመዉ በብቃቱና በስብዕናዉ ሳይሆን በአመራሩ በተለያዩ ኔትዎርክ በመሆኑ የተለያዩ ወቂታዊ ተግባራት አፈጻጸም ከመቸዉም ጊዜ በላይ ዝቅተኛ ነዉ።
👉 በክልሉ ምላሹ ባላገኙ የአስተዳደር እና የማንነት ጥያቄዎች ምክንያት እየተፈፀሙ የሚገኙ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ( በቁጫ፣ በሻራ አከባቢ፣ በዛይሴ፣ በቦሮዳ ወዘተ እየተፈፀሙ ያሉ ግድያዎች፣ የዘፈቀደ እስራት እና መፈናቀል)
👉በክልሉ የህግ የበላይነት የለም፦ ክልሉ የሚመራዉ በህግና በአሰራር ሳይሆን በርዕሰ መስተዳድሩ ፍላጎት ብቻ ነዉ። በሀሰት ዉንጀላ ጅምላ እስራት (ዎላይታና ኮሬ ዞኖች) እና
በፍርድ ቤት እንድለቀቁ የተባሉት ሁሉ በአመራሩ ትዕዛዝ በየፖሊስ ጣቢያ እየማቀቁ ይገኛሉ። የሐሰት ሪፖርት ማስተላለፍ
በአጠቃላይ ከላይ ለመዘርዘር የተሞከረዉ ክልሉ ዉስጥ ከታዩት ክልላዊ ቅርፅ ካላቸዉ በጣም ትንሽ ጉዳዮች ለማሳየት ያክል ስለሆነ የፌደራል መንግስትና ፓርቲ ለራሱ በሚመቸዉ መልክ የማጣራት ሥራ እንድሰራ ለፓርቲዉ እና ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር ካለን ዉግና አንጻር በቅንነት አቅርበናል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ከተወሰኑ ግለሰቦች በላይ ስለሆነ በብዙ ልፋትና የህይዎት መስዋዕነት ጭምር ተከፍሎ የተደራጀዉ ክልላችን በአንድ ግለሰብ ሴራ ምክንያት መፍረስ የለበትም የሚል ፅኑ ዕምነት ስላለን እረስዎም የክልሉን ችግር አቅልለዉ ሳያዩ አፋጣኝ እርምጃ እንድወስዱ እንጠይቃለን፡፡
በተጨማርም ክልሉ ለሀገራዊ ብልፅግና የራሱን ድርሻ እንድያኖርና ለሀገርቱ ዕዳ ሳይሆን ሚንዳ እንድሆን የተለመደዉ የእርስዎን ቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንዳይለይዎ በታላቅ ትህትናና አክብሮት እንጠይቃለን!!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!!!”
የደቡብ ኢትጵያ ክልል የፖለቲካ ብልሽቶችን በተመለከተ ከ12ቱ ዞኖች የተዉጣጡ ምሁራኖች ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የተላከ ይፋዊ ደብዳቤ
ህዳር 28/2017 ዓ.ም