የዎላይታ ታይምስ የፖለቲካ ወጌሻ ጥንቅር
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በቅርቡ በአዲስ ኮምፓስ ሚዲያ ከኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ ጋር የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶክተር ተስፋዬ በልጅጌ እና አቶ ዛዲግ አብርሃ ወደ አራት ሰዓት ገደማ የዘለቀ ቃለምልልስ ማድረጋቸዉ ይታወሳል። በቅድሚያ አጠቃላይ ስለ ቃለምልልሱ ምን አስተያዬት እንዳሎት ቢያጋሩን በዝርዝር የተወሰኑ ነጥቦችን ከማንሳታችን በፊት !?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እሺ መልካም። በመጀመሪያ ብልጽግና በማህበራዊ ሚዲያ ባለዉ የፖለተካ discourse ዉስጥ የተወሰደበትን ግልጽ ብልጫ ለመገዳደር እና ለመጋፈጥ የተወሰነ risk ወስዶም ጭምር መወሰኑን ያሳያል። አቶ ኤርሚያስ ለገሰም አቀራረቡ ለዘብተኛ የነበረ ይሁን እንጂ አሁንም የተወሰኑ ወሳኝ ጥያቄዎችን አንስቷል። ከዚህ በፊትም ብልጽግና ላይ በተለያዬ ጊዜ የሰላ ትችትም ሲሰነዝር እንደነበረም ይታወሳል።
ብሔራዊ ጥቅም በሚላቸዉ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ድጋፍ ለብልፅግና ሲሰጥ ነበር። ስለዚህ ብልጽግና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ወደማህበራዊ ሚዲያው መምጣቱ ጥሩ ነው። ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ያለዉን ኃይል መሸሽ ጤናማ አካሄድ አይደለምና። በሐገር ዉስጥም የተዘጉ ሚዲያዎች እና በጋዜጠኞችም ደረጃ ስደትን እንደአማራጭ ብዙዎች በብልጽግና ምክንያት መርጠዋልና ለዛም መፍትሔ ብልጽግና ማበጀት እንዳለበት እጠቁማለሁ።
በሐገር ዉስጥም ሚዲያዎች ላይ ጫና መፍጠር በማቆም እንደጋራ መድረክ ሚዲያን ማየት የመፍትሔ አካል ነው እላለሁ። ይህ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያም የተሰደደዉ በጫና ምክንያት መሆኑ ይታወቃልና።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ዶክተር ተስፋዬ በልጅጌ የለዉጡ ባለቤት ማነዉ ተብለዉ ሲጠየቁ፥ የደቡብን ተሳትፎ ለመግለጽ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቂያ ቀድመዉ ለደኢህዴን ማስገባታቸዉንና ተቀባይነት ማግኘታቸዉን ጠቅሷል። እርሳቸዉ ስልጣን ባይለቁ ነገሮች በሌላ አቅጣጫ እንደሚሄዱም ጠቅሷል።
ነገር ግን ለዉጡ ከመጣስ በሁዋላ ሐገሪቷ በሄደችበት መንገድ የደቡብ ሕዝብ ባለቤት ነው ማለት ይቻላል? በዚህ ላይ የእርሱዎ ምልከታ ምንድነዉ? በግልጽ ቋንቋ ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኃላ የደቡብ ሰው ruling circle (የሐገሪቷን እጣ ፋንታ የሚወሰኑ ግለሰቦች) ዉስጥ አለ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በጣም ዉስብስብና ሰፊ ጥያቄ ነው። ምን መሰለህ ከለዉጡ በፊት ያለዉን ካየን መካድ የማንችለዉ ሐቅ አጠቃላይ በኢህአዴግ ዘመን ኦሮሞ መገፋቱን ነው። ሚዛናዊ የስልጣን ዉክልና ተነፍጓል። በኢህአዴግ የመጀመሪያ አመታት ወሳኙ በአብዛኛው ህወሃት ቢሆንም የብአዴን ሰዎችም ተሳትፎ ነበራቸዉ ፣ተሳትፏቸዉም ቀላል የሚባል አልነበረም፣ እንግዲህ በወሳኝ መልኩ የደቡብ ሰዎች ወደ ruling circle የተቀላቀሉት ከዎጋጎዳ ትግል መልስ በተገኘዉ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የደቡብ ክልል አመራርነት በኃላ ነው ማለት ይቻላል።
አቶ ኃይለማርያም ከጀርባ የሚዘዉራቸዉ ሰዉ ካለመኖሩ በተጨማሪ ከወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር የፈጠሩት amicable relation ምክንያት የበራላቸዉ አሬንጓዴ መብራት፣ ለደቡብ ተደማጭነትና ተሳታፊነት በር የከፈተ ነበር። በትርምስ ይታወቅ የነበረዉን ክልል አረጋግተዉ ወደ ልማት መስመር አስገብተዉታል። የደቡብ ሕዝብም ተባብሮ በመቆም ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥታት አመራር ተገፍቶ መኖሩ ኢትዮጵያን ብዙ እንዳጎደለባት ማስመስከር ችሏል። የሚመሩት ክልል ከኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ጋር ትከሻ እንዲለካካ አስችለዉታል።
አቶ ኃይለማርያም ብዙ የደቡብ ምሁራንን ቦታ እየሰጡ በሐገራቸዉ እጣ ፋንታ ላይ ወሳኝ እንዲሆኑ ለማስቻል ከክልል እስከ ፈደራል በነበረዉ ስልጣን የድርሻውን ተወጥቷል። እርሳቸዉ ስልጣን ከለቀቁ በኃላ ግን አጠቃላይ የደቡብ ፖለቲካ ወርዷል። በብዙ ተግዳሮትም መሐል በሐገሪቷ እጣ ፋንታ ላይ ወሳኝ ከሚባሉ ሰዎች መሐል በእርሳቸዉ መሪነት ሌሎችም የደቡብ ምሁራን የነበሩበት ምዕራፍ ተዘግቶ ፍጹም ተላላኪ እና ግምባር አምባቢ ሊህቃን እጅ ላይ ወድቋል የደቡብ ፖለቲካ።
በእርሳቸዉም ዘመን ደቡብ፣ ትግራይ እና አማራ ruling circle ዉስጥ የነበሩ ቢሆንም ኦሮሞ ላይ ግን በእርሳቸዉ እዉቅና መጥፎ ዉሳኔ የሚደረግበት ሁኔታ አልነበረም።
አሁን ላይ ሐገሪቷን የሚዘዉሩት የኦሮሚያና የአማራ ሊህቃን ብቻ ናቸዉ፣ ለምሳሌ የትግራይ ሰዉ የለም በ ruling circle ዉስጥ። የደቡብም ፖለቲካ ብሔሩ የትኛውም ይሁን የኃይለማርያም አይነት እዉቀት፣ ቅንነትና የራስ መተማመን ያለዉ ሰዉ ቢመራዉ በሐገሪቷ እጣ ፋንታ ላይ ወሳኝ ከመሆን የሚያግደዉ ኃይል አይኖርም ነበረ።
ስለዚህ ከለዉጡ በሁዋላ የደቡብ ሕዝብ መገዳደሉ፣ መከፋፈሉ፣ የፖለቲካ ሚናዉ መዳከሙ፣ ጥርጣሬ መንገሱ፣ በተለይ የዎላይታ ሕዝብ መገፋቱና መጠቃቱ፣ የደቡብ አመራሮች ድክመትና አቅመ ቢስነት ያሳለጠዉ ነገር ነው። እኔ በአጭሩ የምለዉ ከለዉጡ በኃላ ከረባት አንጠልጥሎ ወሬ የሚያመላልስ፣ ግምባር እያነበበ ጥላ የተባለዉን የሚጠላ፣ በል የተባለዉን የሚል እንጂ እንደደቡብ ተወላጅ የሕዝቡን ጥቅም በእዉቀት አስልቶ፣ ከኦሮሞ እና የአማራ ሊህቃን ጋር ተገዳድሮ፣ በሐገሪቷ አቅጣጫ ላይ የወሳኝነት ሚና ያለዉ አንድም ሰዉ የለም።
አንድ ማሳያ አሁን ከላይ ስለጠቀስከዉ ግለሰብ ከቃለምልልሱ ላንሳልህ። ዶክተር ተስፋዬ በልጅጌ በቃለምልልሱ መሐል” እኛ እንደብልጽግና በሐገራዊ ምክክሩ የምናነሳቸዉን ነጥቦች አዘጋጅተን ጨርሰናል “ይላሉ። ይሄንን ስትሰማ እሳቸው የ ruling circle ዉስጥ ያለና ወሳኝ ከሆኑ አካላት አንዱ ይመስላል፤ ነገር ግን፣ ኤርሚያስ በግልህ presidential ወይስ parliamentary ሥርአት ለኢትዮጵያ ትመርጣለህ ሲለዉ፣ “የትኛው ይሻላል የሚለዉን አላጠናሁትም፣ የተለያዩ ሰዎች ግን የተለያዬ አቋም አላቸዉ ብሏል።”
ብልጽግና በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በዳኒኤል ክብረት በኩል presidential ሥርዓት ምርጫው እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል። እንግዲህ ብልጽግና ወስኖ ያደረዉን ጉዳይ እርሳቸዉ ካላጠኑት ዉሳኔዉ ላይ አልተሳተፉም፣ ከተሳተፉም ያኔ ግምባር አምብበዉ ወደነፈሰበት ተደርበዋል ማለት ነው። በአሁኑ ሰዓት ከደቡብ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርበዋል የሚባለዉ እና ከፍተኛ ስልጣን ካላቸዉ ግለሰቦች አንዱ ገዢዉ ፓርቲ፣ ወስኖት ባደረዉ ጉዳይ ላይ የደቡብን ሕዝብ ጥቅም የሚያስከብር አቋም ይዞ አጥንቶ አልተሳተፈም ማለት ነው።
ስለዚህ የደቡብ ሰው በ ruling circle ዉስጥ አለ ማለት አይቻልም ብዬ አምናለሁ። ይህ አንድ ከቃለምልልሱ የተወሰደ መገለጫ ነው እንጂ ብዙ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል። በማያገባቸዉ እንደ ደርግ ጊዜ የደቡብ ወጣቶች በጦርነት እየተማገዱ ነው። የደቡብ ሕዝብ የጦርነቶቹ ባለቤት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፣ ከሚያስጀምሩም፣ ከሚያስቆሙ ሰዎች መሐል ደቡቤ የለም።
አብዛኞቹ የደቡብ አመራሮች ኦሮማራ ብልጽግና ሰዎች ጋር የሕዝባቸዉን ጥቅም አስልተዉ በራሳቸዉ ወስነዉ እንደማይጋፈጡ የአደባባይ ሚስጥሪ ነው። የማዕከሉ ብልጽግና የወሰነዉ በሁሉም ላይ ይጫናል ማለት ነው። መሐል ላይ ደግሞ ወሳኝ ኃይሎች ኦሮማራ መሆናቸዉ ግልጽ ነው።
ስለዚህ በሐገራዊ ምክክሩ ብልጽግና ይዞ የሚቀርባቸዉ ነገሮች ከማዕከል የሚጫኑ እንጂ፤ የሁሉም አካባቢ ሰዉ የተሳተፈባቸዉ ሊሆኑ አይችሉም። ከላይም ያነሳሁት መከራከሪያ አንድ ግለሰብ ላይ character assassination ለመፈጸምም ሆነ፣ ማንነቱን በመጥላት ሳይሆን በግልጽ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ከለዉጡ በሁዋላ በሐገሪቷ እጣ ፋንታ ላይ ወሳኝ ሆኖ አለመቀጠሉን ለማሳዬት ነው።
እንደዉም ግለሰቡ በቅርብ ጊዜያት ዉስጥ የዎላይታን ሕዝብ ሐቀኛ ጥያቄዎች ደግፎ የተለያዩ መድረኮች ላይ ስለዎላይታ መሟገቱን መረጃዎች ያሳያሉ ፣እናም በግል እሱን ለማጠቃት ሊሆን አይችልም። ስለዚህ አላማችን ስም ማጥፋት ወይንም ጥላቻ ሊሆን አይችልም፤ ይልቅ የደቡብ ሕዝብ ከ ruling circle መገፋቱን እና ለሐገሪቷ ዉድቀት የደቡብ ሕዝብ መገፋት አንዱ ምክንያት መሆኑን ለማሳየት እንጂ።
፨ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ምናልባት ከለዉጡ በኃላ በፌደራልም በክልልም የዎላይታ ሕዝብ ሚዛናዊ የሥልጣን ዉክልና መከልከሉ ለምን ይመስልዎታል? የትግራይም ተመሳሳይ ስለሆነ አያይዘዉ ቢገልጹልን ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እንግዲህ የኦሮ_ማራ ብልጽግና ሰዎች፣ ትግራይንና ዎላይታን መግፋት፣ ስልጣናቸዉን የሚያደላድልላቸዉ እና የበላይነታቸዉን የሚያረጋግጥላቸዉ መስሏቸዉ ነው። መንገዱ ግን ሐገር አፍራሽ እንደሆነ ግልጽ ነው። በጸጥታ ተቋማት እና ከፖለቲካ ስልጣን ብሔር እየለዩ ሰዎችን መቀነስ በሁለቱ ሕዝቦች ላይ ያነጣጠረ ነበር። አግላይነት መጨረሻዉ ሐገራዊ ዉድቀትና ድቀት ነው ያም ነው የሆነዉ።
ከለዉጡ በሁዋላ መንግሥት የሔደባቸዉ መንገዶች፣ አግላይ እና ሕገመንግስታዊነትን የዘነጉ መሆናቸዉ ለዚህ ዉጥንቅጥ ዳርጎናል። አሁንም መፍትሔው ሐቀኛዉን የሕገመንታዊነትን መንገድ መከተል ነው።
ትግራይም ሆነ ዎላይታ በኢትዮጵያ ሐገረመንግስት ግምባታ አቅጣጫ ላይ ለመሳተፍ እና የኢትዮጵያ ዜጋነታቸዉን ለማረጋገጥ ብዙ ትግል አድርገዉ ብዙ መስዋዕትነትም ከፍለዋል በዘመናት መካከል የእነሱ በ ruling circle መኖርና አለመኖር በቀጥታ ከሐገሪቷ ሰላም ና ጸጥታ እንዲሁም ከብሔሮች እኩልነት ጋር የተያያዘ ነው።
በግልጽ ቋንቋ መገፋታቸዉ ሐገሪቷ ወደሁዋላ የመመለሷ ማሳያ ነው፣ የሁለቱ ብሔር ሰዎች በ ruling circle ዉስጥ አለመኖራቸዉ አጋጣሚ አይደለም ታቅዶበት የተደረገ ነው። ሁለቱም ሕዝቦች በጭቁን ሕዝቦች ትግል የፈር ቀዳጅነት ሚና የነበራቸዉ ናቸዉ፣ እነዚህን መግፋት ሐገሪቷን ወደሁዋላ እንደሚመልስ ሳይታለም የተፈታ እዉነት ነው መሬት ላይ የሚታየዉም እዉነታ ያ ነው።
ይህ ሁሉ ሥርዓት አልበኝነት ዉድመትና ፍጅት በዋናነት አግላይነት የወለደዉ ነው። አግላይነት ተቋማትን ሽባ ያደርጋል፣ ሕዝቦችን ይከፋፍላል፣ የእርስ በርስ ጦርነቶችን ያዋልዳል social fabric ይበጣጥሳል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ምናልባት ከዚህ በፊት ዶክተር ተስፋዬ (ያኔ አቶ ነበሩ)፣ በአርትስ ቴሌብዥን ከቁህዴፓዉ ዶክተር ገነነ እና አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ሰዉ ጋር ሆነዉ የዎላይታ ፓርቲዎች እራሳቸዉን ባገለሉበት ዝግጅት ላይ ከሕዝበ ዉሳኔዉ በፊት ደቡብ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ሶስተኛ ክልል ይሆናል ብለዉ ነበረ። የእዉነት አሁን ደቡብ ኢትዮጵያ ሶስተኛ ክልል ሆኗል?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ አልሆነም። እንዲሆን ማድረግ ይቻል ነበረ ፣በድርድር አሁንም ማድረግ ይቻላል። ዶክተር ተስፋዬ በልጅጌ አባባሉን የሰማዉ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ መሥራችና በብልጽግና ጫና ምክንያት የተሰደደዉ ፖለቲከኛ አንዷለም ታደሰ ቦልተና ከጋዜጠኛ አንተነህ አብረሃም ባባንቶ ጋር በዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ቀጥታ ስርጭት ውይይት ካደረገዉ ቃለምልልስ ላይ ይመስለኛል። በወቅቱ አንዷለም ኮንታንና ዳዉሮን ጨምሮ በአካባቢው የሚገኙ ሕዝቦች ዎላይታን ጨምረዉ በድርድር በኢትዮጵያ ሶስተኛዉን ትልቅ ክልል መፍጠር እንደሚችሉ የጠቆመበት ነበረ። ዎላይታ ክልል ጥያቄዉ ካልተመለሰ፤ ሲጀመርም ከሌሎች ጋር መኖርን ጠልቶ ሳይሆን መገፋት እና መጠቃት የፈጠረዉ ጥያቄ ነበረና።
የተፈጠረዉ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዳዉሮና ኮንታን አለመያዙ ብዙ አጉድሎበታል፣ የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች በሕገመንግስቱ አግባብ አለመመለሳቸዉ እና የዎላይታ ሕዝብ በተወካዮቹ በኩል በቂ ድርድር ሳያደርግ ክልሉ በመጫኑ የጨረቃ ክልል አድርጎታል። ክልሉን የሚመሩ ግለሰቦችም ለሕዝብ ሞራልና ስሜት የማይጨነቁ ሐሳባቸዉን እንዴት መግለጽ እንዳለባቸዉ የማያዉቁ ከዎላይታ ጋር ተቀራራቢ ከሆኑ ሕዝቦች አብራክ ተገኝተዉ በአደባባይ “ከዎላይታ ጋር በምድርም በሰማይም አንገናኝም” “ከዎላይታ ዉጪ ከማንም ጋር እንደራጃለን” ሲሉ የነበሩ ናቸው ።
መሰል ጤናማ አስተሳሰብ የሌላቸዉ ግለሰቦች ሕዝብን ማቀራረብም ሆነ ማስተባበር አይችሉም በዚህ ደረጃ በራስ መተማመን የሚጎድላቸዉ ሰዎች ሕዝብን ማቀራረብም ሆነ ማስተባበር አይችሉም። የክልሉ ትልቅ ቁጥር ያለዉ ብሔር ከፈደራልም ከክልል ስልጣን በተገፋበት፣ ፍትሐዊም ሆነ ሕገመንግሥትን የተከተለ አሰራር የሌለበት ክልል ተጽዕኖ አሳዳሪ ሊሆን አይችልም። ይህ ኢፍትሐዊ አስራር ደግሞ በክልል አመራሮች ብቻ የሚመራ አይደለም ከላይ ጀምሮ ነው ልጅ ቀማኛ አባት ዳኛ ሆኖ ነው እንጂ
እስካሁንማ መፍትሔ ይሰጠዉ ነበረ ችግሩ።
በቅርቡ የብልጽግናዉ ምክትል አቶ አደም ፋራህ ወደ ዎላይታ ሶዶ መጥቶ አደረገዉ የተባለዉ ግምገማም በተለይ እርሳቸዉ ከሱማሌ ክልል በመሆናቸዉ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ቢሆንም ችግሩን በልኩ የሚፈቱበት በቂ ስልጣንም በሕገ ደምብ ደረጃ ቢኖራቸዉም፣ የፓርቲዉ ዎላይታን የመግፋት ያልተጻፈ ኦሮ_ማራዊ ሕግ የሚያሰራቸዉ አይመስለኝም። ከዎላይታ ጋር መደራጀት ያልፈለጉ አመራሮች የዎላይታ ሕዝብ ተማርሮ ከክልሉ እንዲወጣ እየተጉ ነው፣ ብዙ ሕገወጥ ዉሳኔዎችን አስፈጽመዋል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ለመሆኑ ከዎላይታ ጋር መደራጀት የሚጠላ ነገር ነው ? አንዳንድ አመራሮች እንደሚሉት ከዎላይታ ጋር መደራጀት የሚጎዳ ነገር ነው ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እዉነት ለመናገር አይደለም ከዎላይታ ጋር እጅግ ተቀራራቢ ቋንቋ የሚናገሩ ጋሞ እና ጎፋ እንዲሁም ዳዉሮና ኮንታን ይቅርና ሌሎቹንም ሕዝቦች የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም። ዎላይታም ከእነዛ ሕዝቦች ጋር መሆኑ ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳዉም። ችግሩ የአመራሩ የፖለቲካ እዉቀት ዉስንነት፣ የሶስተኛ ወገኖች ተጽዕኖና አጠቃላይ የገዥዉ ፓርቲ የቅንነት ማጣት ነው።
የዎላይታ ሕዝብኮ ታግሎ አጠቃላይ የደቡብን ሕዝብ ነጻ ያወጣ አብዛኛውን የደቡብ ሕዝብ በታሪኩ ትልቅ በሚባሉ የስልጣን እርከኖች እንዲወከል በር የከፈተ ነው። እነ ዳዉሮ፣ ጎፋ፣ ኮንታም የዞን አስተዳደር ያገኙት የዎላይታ ሕዝብ በከፈተዉ በር ነበረ። ዎላይታ ብዙ የተማረ ሰው ስላለዉ ይዉጠናል የሚለዉም በጣም የተሳሳተ ነው። በድርድር ሁሉም የድርሻዉን እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል። በእርግጠኝነት የምነግርህ የቀድሞ ደቡብ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልል የነበረዉ status በዎላይታ ሕዝብ ትግል set የተደረገ ነበር።
አንዳንድ ሰዎች ዎላይታ ክልል ከሆነ ተጽዕኖዉ የሚቀንስ ይመስላቸዋል፤ ይህ በጣም የተሳሳተ ትንታኔ ነው። የሚያሳዝነዉ ከሚቀራረቡን የጎፋ፣ ዳዉሮ፣ ጋሞና ኮንታ በመዋቅር ደረጃ መለያዬታችን ነዉ እንጂ የመአከላዊ መንግስት ላይ የሚኖረን ተጽዕኖ ይጨምራል፣ በክልል ደረጃ ብዙ ነገሮች መቀየራቸዉ አይቀርም። የፈደራል መንግስት ስልጣን ትርጉም ባለዉ ደረጃ መቀነስና መገደቡ አይቀሬ ነው። ከዛ ዉጪ ብዙ ነገሮችን በ absolute congruence የዎላይታ ክልል ከአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ጋር በማነጻጸር ደረጃ ማግኘቱ አይቀርም፣ በፖሊሲ ክልላዊ ሉአላዊነቱን በሚገባ መጠቀሙ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለ ምህዳር መፍጠሩ የሚዲያ ነጻነት ማረጋገጥና በሐገር አቀፍ ደረጃ መገዳደሩ፣ በግልጽና ጉልህ በሆነ ሁኔታ በፈደራል መንግስት ላይ ተጨባጭ ተጽዕኖ ማምጣቱ አይቀርም።
እራሱ ታግሎ፣ ሌሎችንም ነጻ ያወጣ ሕዝብ ለእራሱ አያንስም። ለዉጥ የሚመጣዉ የሆነ ስም ያለዉ ክልል ስለያዝክ ሳይሆን የያዝከዉን ክልል በሕገመንግስቱ የተፈቀደልህን መብት አስከብረህ ነፍስ ስትዘራበት ነው፤ እንጂ የእጌሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተብለህ ከረባት አንጠልጥለህ ስለዞርክ አይደለም።
በተለይ የጥገኝነት ፖለቲካ በጣም አስቸጋሪ ነገሩ ተጽዕኖ እና ተደማጭነት የለሽነትን መሐል ሰፋሪነትን አልሞ በሁለት ጥይት መመታትን፣ የሌሎች ግጭት የሚካሄድበት ሜዳነት የራስን አካባቢ አሳልፎ መስጠትን፣ እና ለመሳሰሉ አስቸጋሪ ነገሮች ያጋልጣል። የደቡብ ኢትዮጵያ አመራሮች ከነአከርካሪያቸዉ በ ruling circle ዉስጥ የወሳኝነትን ሚና እንዳይጫወቱ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ይህ የክልሉ ያለበቂ ድርድር መቋቋምና በተለይ የዎላይታ ሕዝብ ቦታ እንዲያጣ መደረጉ የአንበሳዉን ድርሻ በቀጥታ ይይዛል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ የሱማሌ ክልል ሰሞኑን የተመሠረተበትን 32 ኛ ዓመት ማክበሩ ይታወሳል። የክልሉ ወቅታዊ የፖለቲካ ቁመና ምን ይመስላል ? በሐገሪቷ ፖለቲካ ላይ ያለዉ አሁናዊ ተጽዕኖ ምን ያህል ነው ? የክልሉ አመራሮች አቅም ምን ይመስላል ? በብልጽግና ፓርቲ ዉስጥስ ያላቸው ድርሻ ምንድነው ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በቅድሚያ የሱማሌ ክልል ሕዝብን በአጠቃላይ በሐገር ዉስጥም ዉጭም የሚገኙትን በሙሉ ለ32ኛ ዓመት የሱማሌ ክልል ምስረታ በአል እንኳን አደረሳችሁ ለማለት አዉዳለሁ። የበዓሉ መከበር የሱማሌ ሕዝብ ለፈደራል ሥርአቱ ያለዉን ቀናኢነት ያሳያል። በርግጥ የሱማሌ ሕዝብ በሁሉም የኢትዮጵያ መንግስታት ማለት በሚቻል ሁኔታ ተገፍቶ እና ተከድቶ የኖረ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም። በለዉጡ ዋዜማ አካባቢ ከኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ጋር የነበረዉ ችግር በአንጻራዊነት የረገበ ይመስላል።
የክልሉ አመራርም በአቅም ደረጃ ጥሩ ነው የሚል ግምገማ አለኝ፣ ነገር ግን የሱማሌ ሕዝብ በመከላከያ፣ በዲፕሎማሲ መስክ፣ በደኅንነት እና በፖለቲካ እንዲሁም በኢኮኖሚ በሐገር ደረጃ ያለዉ ተሳትፎ ከመገፋት የተነሳ ዉስን መሆኑ አቅሙን ገድቦታል። የብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረትም ከሕወሓት እምቢታ ዉጪ ፣አጋሩን ኢሶህዴፓ (ኢትዮጵያ የሚለዉ ተቀጽላ ተቀንሶ ነበር) አቅልጣችሁ፣ ብልጽግናን ተቀላቀሉ ሲባሉ ወጡን ፓርቲ ለመቀላቀል አንገራግረዉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጅጅጋ ድረስ ሄዶ አግባብቷል። ከሁለት የፓርቲው ምክትል ፕረዚዳንቶች አንዱም የሱማሌ ተወላጁ አደም ፋራህ ሆኗል።
በነገራችን ላይ የኦሮ_ማራ ኃይሎች ክልሉን እራሳቸዉ በተናጠል ለመዘወር በተደጋጋሚ ቢሞክሩም ክልሉ ለጥገኝነት እጁን አልሰጠም። የአማራ ክልል ኃይሎች ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድን የእኛ እያሉ በተደጋጋሚ ስሙን ማንሳት በማብዛታቸዉ ፣የኦሮሚያ ብልጽግናዎች በምርጫ ክርክር ላይ ሙስጠፌ መሐመድ የአማራ ሊህቃን የማይወዱትን የፈደራል ስርዓት ተከላክሎ እንዲከራከር አድርገዉታል። ሙስጠፌ መሐመድ በክርክሩ በጥሩ ሁኔታ አቅሙን አሳይቷል።
በሌላም በኩል የአማራ ክልሉ ልዩ ኃይል ፈረሳን ተከትሎ ግጭቶች የጀመሩ ሰሞን ብልጽግና በአልጀዚራ አንድ የሱማሌ ክልል ተወላጅ የፓርላማ አባል ከአማራ ተወካዮች ጋር እንዲከራከር መድቦት፣ ግለሰቡ መርሐግብሩን እንካ ሰላምቲያ ዉስጥ ሳይገባ በጥበብ ጨርሶታል።
በአሁኑ ሰአት በክልሉ ያለዉ የሰላም ሁኔታ በአንጻራዊነት ጥሩ ነው የልማት እንቅስቃሴዎችም አሉ። እነሙስጠፌ የትግራይ ጦርነትን ቢደግፉም ግጭቱን ከጠመቁ ኃይሎች መሐል አሉ ለማለት አይቻልም፣ በተለይ ከሚኒስትርነት ስልጣን በፈቃዷ የለቀቀችዉን ፊልሰን አብዱላሂን “ከእሴቶቼና ከታማኝነቴ ጋር ተቃራኒ የሆኑና ሥነ ምግባሬን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ነገሮች፤ እንዲሁም እነዚህን እምነቶች መካድ የእራሴንና የዜጎቻችንን እምነት መጣስ በመሆኑ ነው” ስልጣን የለቀቅኩት ማለቷን መርሳት አይገባም። ክልሉ መሰል አቋም ያላቸዉን አመራሮች በብዛት ማፍራት እንደሚችልም አያጠራጥርም።
በአጠቃላይ በሐገሪቷ አሁናዊ ruling circle ዉስጥ የሱማሌ ክልል ተወላጅ አለ ባልልም፣ በተለይ ክልላቸዉን የሚያስተዳድሩበት መንገድ በአንጻራዊነት ጥሩ ነው ማለት ይቻላል። ክልሉ በዋናነት በራሱ የጸጥታ ኃይል ድምበር ጥሶ የገባዉን የአልሸባብ ኃይል መግታት መቻሉም የሚጠቀስ ተግባር ነው። እዚህ ጋር የፈደራል መንግስትን ድክመት መጥቀስ ተገቢ ነው። በሱማሊያ ድንበር አካባቢዎች አልፎ አልፎ ከሚታዩ ግጭቶች በተጨማሪም ከአፋር ክልል አዋሳኝ ጎሳዎች ጋር በየጊዜዉ የሚከሰተዉ ግጭት የክልሉ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።
በቅርቡ ደግሞ አንድ የደቡብ ክልል ተወላጅ ሴት ደፍሯል ተብሎ በተለይም በጉልበት ሥራ ላይ የተሰማሩ የደቡብ ተወላጆች ላይ አፈሳና ድብደባ ተደርጎ ነበር፣ ክልሉ መሰል ነገሮችን ማሻሻል ያለበት ይመስለኛል። ሱማሌዎች በአዲስ አበባ ቦሌ መድሐኒአለም አካባቢ በብዛት ይኖራሉ፣ አጠቃላይ ሱማሌዎች በንግድ ሥራ ላይ ጎበዝ እንደሆኑ ይነገራል።
በሁሉም ዘርፍ በኢትዮጵያ ሱማሌዎች በፍትሐዊነት የድርሻቸዉን ሚና እንዲጫወቱ እድሎች መሥፋት አለባቸዉ ያ ከተደረገ ኢትዮጵያ ትጠቀማለች አንድነታችንንም ያጠናክራል።
በክልሉ የፖለቲካ ምህዳር ላይ አሁንም ቅሬታዎች ይደመጣሉ፣ ኦብነግ ግን ብዙ ቅሬታ ቢኖረዉም እስካሁን በሰላማዊ መንገድ በክልሉ ይንቀሳቀሳል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ደረጃ የክልሉ ሚና በኦሮ_ማራ መራሹ ብልጽግና ምክንያት የተገደበ ቢሆንም ክልሉ ግን እንደሌሎቹ ፣በቀላሉ የሚዘወር አይደለም፥ ምናልባት በክልል ደረጃ በself rule የፈደራል ሥርዓቱ ሕይወት አለዉ ከሚያስብሉ ክልሎች አንደኛዉ ነው ሱማሌ ክልል፣ በ shared rule አኳያ ክልሉ የሚገባውን ድርሻ አላገኘም። ይህ መገፋት በዘመነ ብልጽግና ብቻ ሳይሆን ከጥንትም የኢትዮጵያ መንግስታት ነባል ሥህተት ነው።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ በሐገራዊ ምክክሩ ላይ ከክልሉ እንደ አጀንዳ የተያዙ ጉዳዮችን እንዴት አገኟቸዉ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በእዉነቱ interesting ናቸዉ። ለምሳሌ የፈደራል መንግስት ስልጣን ተቀንሶ የክልሉ ይጨመር የሚል ተነስቷል። በተለይ ለዘመናት ተገፍቶ የኖረ ሕዝብ ይሄንን ማንሳቱ አይገርምም አሁን ደግሞ የኦሮ_ማራ majority tyranny ሌሎቹንም ክልሎች ይሄንን እያስመኘ ነው። ሱማሌዎች ብዙ ምሁራን አሏቸዉ እናም በሐገራዊ ምክክሩ ጎልተዉ ከሚወጡ ድምጾች መሐል እንደሚኖሩ አልጠራጠርም። ምናልባት ኢትዮጵያ ጎብጣ ከቀረችባቸዉ ምክንያቶች አንዱ የሱማሌን ሕዝብ ስትገፋ መኖሯ እንደሚሆን አልጠራጠርም። አምባሳደር መሐመድ ድሪሪም ኮሚሽነር ነው ያም ተገቢ ይመስለኛል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ የአሁኑ የሱማሌ ክልሉ ፕረዚዳንት ሙስጠፌ መሐመድን የፖለቲካ አቋምና አቅም እንዴት ይገመግማሉ ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ከክልሉ ተወላጆች በፈደራል በከፍተኛ ስልጣ ለረዥም ጊዜ የሚታወቀዉ አህመድ ሽዴ ነው። ሙስጠፌ መሐመድ አሁን በኢትዮጵያ ካሉ የክልል ፕረዚዳንቶች በአቅም ደረጃ የተሻለ ይመስላል። በፈደራል ሥርዓቱ ላይ የማያወላዉል አቋም አለዉ፣ የክልሉ ሊህቃን በአብዛኛው መሰል አቋም አላቸዉ። በግሌ ሙስጠፌ መሐመድ በፌደራል ደረጃ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የድሮዉ ፈደራል ጉዳዮች አይነት ቦታዎችን የሚመጥን አመራር ይመስለኛል።
በኢትዮጵያ ruling circle ዉስጥ የሱማሌ ተወላጅ በቋዋሚነት መኖር አለበት የሚል እምነት አለኝ ያ በሐገሪቷ ሰላም ለማስፈንም ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረዉ ይመስለኛል። በኦሮ_ማራ ብቻ ሐገሪቷ መመራቱ ከባድ አደጋ ዉስጥ እንደከተታት በግልጽ ይታያል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ፦ በክልሉ የፖለቲካ ኃይሎች ላይ መሻሻል ያለበት ድክመት ብለዉ የሚጠቅሱት ነገር ካለ ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ያዉ ከሌሎች ኃይሎች ጋር ተቀራርቦ የመስራት ክፍተት አለ፤ ግን ሌሎቹስ መች አቀረቧቸዉ? የሁለቱም ድክመት ነውና መሻሻል ያለበት ነው። የሱማሌ ሕዝብ ፍትሐዊ ዉክልናና ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ በጋራ መታገል ይገባል። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱንም ለማጠናከር ሁላችንም ብንሰራ እላለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እጅግ አብዝተን እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
Ethiopia #southethiopia #Wolaita #Politicalparty
ማሳሰቢያ ለውድ አንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ “የፖለቲካ ወጌሻ” መደበኛ እንግዳ ዝግጅት ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ በማድረግ ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረብነው የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው