1000046736

ለመረጋጋት ከኢትዮጲያ የሚነሳ አዲስ አስተሳሰብ የናፈቀዉ የሚመስለዉ ቀጠና፣ የአፍሪካ ቀንድ… (በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተጋባዥ ጸሓፊ)

ለዘመናት ከግጭትና አለመረጋጋት ተላቆ የማያዉቀዉ የአፍሪካ ቀንድ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ብሶበታል። በአንጻራዊነት መረጋጋት የነበራትና ቀጠናዉም ላይ የማይናቅ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ለራሷም መሆን አቅቷት ከባባድ የእርስበርስ ጦርነቶችን እያስተናገደች ነው።

በትግራይ አለምን ያስደነገጠ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመበት ጦርነት ብልጽግና መራሹ የፌደራል መንግስት በኤርትራና በአማራ ክልል አጃቢነት አድርጓል። እናም ጦርነቱን ለማስቆም የተፈረመዉ የፕሪቶሪያ ስምምነት በአማራ ክልልና በኤርትራ በኩል ሌላ ኩርፍያ ፈጥሯል። ከሲቢሉ አሸጋጋሪ የአብደላ ሐምዶክ መንግስት ስልጣን ሲነጥቁ የልተጎራበጡት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉና መከላከያዉ መሪዎች ሓሚቲ ና አልቡርሐን ታጣቂዎች ጎራ ለይተዉ መፋለም ከጀመሩ ሰነባብተዋል፣ ይህም በሱዳን ከፍተኛ የሰብአዊ ቀዉስ አስከትሏል።

ረገብ ብሎ የነበረዉ የደቡብ ሱዳኖቹ ሳልባኪርና ሪክ ማቻር ነገርም አገርሽቶ ድጋሚ ሐገሪቷን ከባድ ወጥረት ዉስጥ ከቷታል ሰሞኑን።በአንጻራዊ ነት የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ በቀጠናው የምትታወቀው ኬንያም ብትሆን በቅርቡ የተቀሰቀሰዉ ሕዝባዊ አመጽ በሕግ ስረዛ እና ካቢኔ ሹም ሽር ፕሬዝዳንት ሩቶ ቢያረግቡትም ፣በተጨማሪም ለአፍሪካ ሕብረት ፕሬዚዳንትነት ተወዳድረዉ ያልተሳካላቸው ራይላ ኦዲንጋ ጋር የስልጣን ክፍፍል ስምምነት ቢፈራረሙም፣ ነገሩ ያበቃለት አይመስልም።

የኢትዮጵዉ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተደጋጋሚ በድንበሯ ዉስጥ በመንቀሳቀስ ሳትወድ በግድ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ትኩሳት ጋር አነካክቷታል፣ በተጨማሪም ከሱማሊያ መንግስት እና አልሸባብ ጋርም ቀሪ የቤት ሥራዎች አሏት ኬንያ። በሐሰን ሼክ የሚመራዉ የሱማሊያዉ ፈደራል መንግስት አልሸባብ የደቀነበት ፈተና ሳያንስ ራስ ገዞቹ ሱማሌ ላንድና ፑንት ላንድ ራስ ምታት ሆነዉበት ቀጥሏል።

በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር በሐገር ዉስጥ በራሱ ከሕገመንግስት በማፈንገጥና በተሳሳተ ፖሊሲ የፈጠረዉን ትርምስ መጋፈጥና ማረም ሲገባዉ፣ ለማደናገር ያለበቂ ጥናትና ተቋማዊ አሰራር ከሱማሌ ላንድ ጋር የባሕር በር የሚያስገኝ MOU ተፈራረምኩኝ በማለቱ፣ ሱማሊያ እና ኢትዮጲያ ከባድ ፍጥጫ ዉስጥ ገብተዉ በቱርክ አደራዳሪነት በአንካራዉ ስምምነት ጋብ ቢልም፤ አካሄዱ ኢትዮጵያን ብዙ ነጥብ አስጥሏታል።

ሱማሊያም ከኤርትራ እና ግብጽ ጋር ከደኅንነት ጋር የሚያያዝ ዝርዝሩ ይፋ ያልተደረገ ስምምነት ተፈራርማለች። ከኢትዮጵያዎቹ የሱማሌና አፋር ክልል ግጭት ጀምሮ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እሳቶቾ ወላፈን በቀጥታ የሚጋረፋት ጅቡቲ በቅርቡ ወደ አፋር ክልል ዘልቃ በስመ ታጣቂ ንጹሓንን አጥቅታለች። አሁን ላይ በአፍሪካ ቀንድ የሚደረጉ ግጭትና አለመግባባቶች ከሞላ ጎደል ቀጠናዊ ኃይሎችን የሚያሳትፉ መሆናቸዉ በግላጭ የሚታይ ነው።

በቀጠናዉ የጦር ሰፈር የመሰረቱና ለመመስረት የሚያስቡ ሐገራት ቁጥር ከመቼዉም ጊዜ በላይ ጨምሯል። በተለይ አሁን ላይ የፕሪቶሪያ ስምምነት በሙላት እንዳይተገበር በኤርትራ እና በአማራ ኃይሎች የተያዙ በትግራይ ስር የነበሩ መሬቶች አለመመለሳቸዉ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል።

ኤርትራ የያዝኩት የትግራይ መሬት የለም በሚለዉ ገታራ አቋም ብትጸናም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም በአቶ ረድዋን ሁሴን በኩል ኤርትራ በአልጀርስ ስምምነት የተወሰነላትን መሬት ነው የያዘችዉ የሚለዉን አቋም በመቀየር በዶክተር አብርሃም በላይ በኩል ኤርትራ የያዘችው የትግራይ መሬት እንዳለ አምኗል።

በኢትዮጵያ በኩል አሰብ የኛ ነው፣ ከሚለዉ እስከ ሻዕቢያ መደምሰስ ያለበት ኃይል ነው፣ ከኤርትራ ጋር ሆነን የአማራን ሕዝብ እናድን ከሚለዉ እስከ ከሻዕቢያ ጋር ሆነን ብልጽግናን እናስወግድ የሚሉ ድምጾች ከሐገር ዉስጥ እስከ ዉጪ ይደመጣሉ።

በተለይ ይህ ጉዳይ በአብዛኛው በቂም እና በቀል የሚነዳ እንጂ በደምብ የተጠና አካሄድ ያራምዳል የሚባል ቡድን አይታይበትም። ጠላትነት እንጂ ወዳጅነት አይታይበትም፣ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነዉ ከሚለዉም አልፎ የኔና የጠላቴ ጠላት፣ ወዳጄ ነው የሚል መጨረሻውን ለመተንበይ እንኳን የማይመች የዉድቀት መንገድ ነው። በኤርትራም ሆነ በኢትዮጲያ በኩል አሮጌዉ የተንኮልና የጠላትነት ጉርብትና በአዲስ የመልካም ጉርብትና ዲፕሎማሲ የሚቃኝበት መንገድ መፈለግ እና መቀየስ አለበት።

አሁን ላይ ካልተቻለም እስከሚቻል ወደ ቀድሞዉ no war no peace ሁኔታ መመለሱ ይሻላል እንጂ በሁለቱም በኩል ጦርነት የሚፈታዉ ችግር አይኖርም። እልቂት፣ ፍጅት እና የኃያላንን ጣልቃ ገብነት ይጋብዛል ጦርነት ከተነሳ። በተለይ የቀጠናውን መረጋጋት የሚሹ አለም አቀፍ ተቋማትና የሁለቱም ሐገራት ወዳጅ የሆኑ መንግስታት ፣በሁለቱ ሐገራት መሐል በዉጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶቻቸዉ በኩል ሰላማዊ ድርድር እንዲጀመር ግፊት ማድረግ አለባቸዉ ልዩነቶች እንዲፈቱ፣ የረበበዉን የጦርነት ደመና ለመግፈፍ ይህ ወሳኝ መንገድ ነው።

በተለይ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በዋናነት ለፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ትግበራ በትኩረት መሥራትና ትግራይ የፈደሬሽን አባልነቷን በትርክትም በተሳትፎም ማረጋገጥ ብቸኛው መዉጫ መንገድ ነው። ከትግራይ ጋር ተፈርጆ ከፌደራልም፣ ከክልልም ሚዛናዊ ዉክልና የተገፋዉ ዎላይታም ጉዳዩ በመከላከያ፣ በደኃንነት፣ በዲፕሎማሲዉ መስክ የደረሰበት መገፋት ማብቃት አለበት። በሰላም አስከባሪነት የሚታወቀዉና ስለዉጤታማነቱ የቀድሞ የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የመሰከረለት የኢትዮጲያ ጦር ዛሬ በዘር ማጥፋት ለመከሰስ ከመብቃቱ በፊት፣ የትግራይን ጦርነት ለማሳለጥ 40ሺ የዎላይታ ልጆች እንደተቀነሱበት ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ለሐገር ሰላም የለቀቀዉ ብሔር፣ በታሪክ የደቡብ ሕዝቦች በሐገሪቷ አቅጣጫ ላይ ወሳን እንዲሆኑ ታግሎ፣ ሰርቶና መተማመን ፈጥሮ ያስቻለ ብሔር ባህልና ስፓርት ሚኒስቴር ብቻ በሆነበት ሐገር ይረጋጋል ብሎ ማሰብ ቀልድ ነዉ። ዎላይታ በጉልበት የገባበት ክልል በዞኑ የተደረገዉ መፈንቅለ መንግስትና የመሳሰሉ ጉዳዮች ወደ ጠሬጴዛ መምጣት አለባቸዉ።

በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ሕገመንግሥት የሚያከብሩ የሰላም ስምምነቶችን ከፋኖና ከኦነሠ ጋር ከተፈራረመ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ አላት። የኤርትራና የትግራይ ሊህቃን መቃቃር በዋናነት ወንድማማቾቹንና በቋንቋ የሚመሳሰለዉን ሕዝባቸዉን ከማንም በላይ እየጎዳ ስለሆነ በየሐገራቸዉ በኩል ለግንኙነቱ ወደሰላማዊ እና ዘላቂ ወዳጅነት እንዲመጣ በትጋት የመሥራትን አቅጣጫ ካልተከተሉ፣ ኪሳራዉ ይቀጥላል። በምንም አይነት የትግራይና የኤርትራ ሕዝብ እየተዋጋና አንዱ ለአንዱ እንቅፋት በሚፈጥሩ ሊህቃን ምክንያት ዋጋ እየከፈለና በጦርነት ደመና ተከቦ መኖር የለበትም።

የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ ሌላ ቀጠናዊ ትርምስ ከሚያመጡ ድርጊቶች ተቆጥቦ፣ የሐገር ዉስጥ ቀዉሶችን ለመፍታት ከተንቀሳቀሰ፣ በተለይ የተገፉ ኃይሎች በፌደሬሽኑ የሚገባቸዉን ዉክልና ካገኙ በሞተዉ የኢትዮጵያ ፓለቲካ ላይ ነፍስን በመዝራት፣ ቀጠናዉን ለማረጋጋት አዲስ አስተሳሰብ በማመንጨት ኢትዮጵያ በፋን አፍሪካዊ እይታ ቀጠናዉን ለማረጋጋት የድርሻዋን ወደምትወጣበት ቁመና ልትደርስ ትችላለች።

የራሷን የዉስጥ ችግር በሰላማዊ መንገድ ከፈታች የጎሬቤት ሐገራትን የርስ በርስ ግጭትም ማሸማገል ትችላለች። የባህር በርም ቢሆን በወራሪነት ሳይሆን በወዳጅነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ሰጥቶ በመቀበል፣ ለጋራ ሰላምና ጸጥታ በሰላማዊ መንገድ የምታገኝበት መንገድ እንዲፈጠር በጋራ መታገል ይቻላል።

ኢትዮጵያ በጸረ ሽብር እንቅስቃሴ የአሜሪካ እና የምዕራቡ አለም አጋር የነበረችበትን ታሪክ ማደስም ይቻላል። ይህ የሕልም እንጀራ ሳይሆን ሕገመንግሥታዊዉን መንገድ ተከትለን የሁሉም ኃይሎች ቁርጠኝነት ከተጨመረበት በተጨባጭ ማሳካት የምንችለዉ ሐቅ ነው፣ ግን ቀላል ነው ማለት አይደለም።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

Ethiopia #Somalia #Kenya #Eritrea #Djibouti #Uganda #Horn#of#Africa