1000046896

የዩንቨርስቲ መምህራን፣ የህግ ጠበቆች፣ የሶፍትዌር ማሰልጠኛ ኮሌጅ ባለቤት ጨመረው ሌሎች የመብት ተሟጋቾች በዎላይታ ታሰሩ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ዞን ለጥቂት ጊዜ ጋብ ብሎ የነበረው በማህበራዊ ሚዲያ ሀሳባቸውን የሚገልጹ ወጣቶችና የመብት ተሟጋቾችንና ቤተሰቦቻቸውን ማሰርና መደብደብ ሁኔታ ማገርሸቱ ተገልጿል።

በዞኑ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ ጠበቃ እና የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ አሰፋ አየለ “በማህበራዊ ሚዲያ አመራሮችን ተችታሃል” በሚል ከበርካቶች ጋር ከታሰረ 15 ቀን አስቆጥሯል።

በተጨማሪም በዎላይታ ሶዶ ከተማ የቀድሞ አመራሩ የነበሩ አቶ ስጦታው መስፍን እና ጋሻው ጋልቻ የተባሉ ግለሰቦች ከአራት ቀን በፊት መታሰራቸውን ቤተሰቦቻቸው ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ገልጿል።

ከታሰሩት መካከል የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ባለቤት ጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ወንድም የሆኑትና የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ይስሐቅ ጌቾ (Associate ፕሮፌሰር) ዛሬ ማለዳ በዎላይታ ሶዶ ከተማ ከሚገኘው መኖሪያቤቱ በክልሉ ፕረዚዳንት ትዕዛዝ ፖሊሶች ለጊዜው ወዳልታወቀ እስርቤት በማፈን ይዘው እንደሄዱ ለመረዳት ችለናል።

በተመሳሳይ የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ቸርነት ወራና በትናንትናው በፖሊስ ታፍነው ወደ እስርቤት መወሰዱን ከቤተሰቡ ያገኘነው መረጃ አረጋግጧል።

ከዚህ በተጨማሪ በዎላይታ ሶዶ ከተማ የማሮታ ሲኒማቶግራፊ እና ሶፍትዌር ማሰልጠኛ ኮሌጅ ባለቤት የሆነው አቶ ማቴዎስ ከ10 ቀን በፊት ከስራ ቦታ በፖሊስ ተይዘው እስር ቤት እንደሚገኝም ለማረጋገጥ ችለናል።

አብዛኞቹ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዞኑ በሶዶ ከተማ እና ሌሎች መዋቅሮች የታሰሩት በዞኑ እና በአከባቢያቸው የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ሌሎች ችግሮችን ባመኑበት ሀሳብ በማህበራዊ ሚዲያ ይገልፃሉ የተባሉ ግለሰቦች እና ቤተሰቦቻቸው እንደሆነ ተነግሯል።

ቤተሰቦቻቸው ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደገለፁት፦ እነዚህ የታሰሩ ወጣቶች “እስከአሁን ድረስ የተጠረጠሩበት የወንጀል መረጃ ማስረጃ እና ከሳሽ በለሌበት በፖለቲካ አመራር ትዕዛዝ ብቻ ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ተነፍገው ህገመንግስት ያጎናጸፈው መብት በሚፃረር መልኩ ፖሊስ ማሳሰሩን ገልጸዋል።

አሁን ያለው አዝማሚያና መረጃዎች እንደሚጠቀሙ በዎላይታ ዞን በአከባቢው የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መናገር፣ መንግስታዊ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ማጋለጥ እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የተለያዩ የህዝብ ችግሮቹን ይፋ ለማድረግ የሚሞክሩ ወጣቶች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ያለምንም ህጋዊ መጥሪያና አሰራር እየታሰሩ ይገኛሉ።

በተለይም አንድ በዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ የተግባቦትና ጋዜጠኝነት መምህር በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው “ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሌለበት አስገድደው የማህበራዊ ሚዲያዎቻቸውን እንዲከተሉ በማድረግ የግለሰቦችን ድምፅ ለማፈን የሚደረግ አዝማሚያ የመብት ጥሰት ከመሆኑ ባሻገር በአከባቢው መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍንና ብልሹ አሰራር እንዲሰፍን ያደርጋል” ብለዋል።

የዎላይታ ዞን ከየትኛውም አከባቢ በላይ ሚዲያዎች፣ የመብት ተሟጋቾች እንዲሁም ወጣቶች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ተፈጥሯዊ እና ህጋዊ መብት ተጠቅመው በአከባቢው የሚስተዋሉ መንግስታዊ አሰራርና ብልሽት ላይ በሰላማዊ መንገድ ትችት በሚያደርጉበት ወቅት በህገወጥ መንገድ በማፈን፣ በማሰር፣ ያለጥፋታቸው ፍርድቤት እንዲመላለሱ በማድረግ እንዲሁም በስደት ከአከባቢው እንዲሸሹ የሚያስገድድ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለፃችን ይታወሳል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዎላይታ ዞን በየመዋቅሩ በማህበራዊ ሚዲያ በአከባቢው የሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ሀሳባቸውን በልዩነት የሚገልጹ ወጣቶችንና የመብት ተሟጋቾችን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ለእስርና ድብደባ መዳረግ ለጥቂት ጊዜ ጋብ ያለ ቢመስልም አሁን ላይ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መልሶ አገርሽቷል።

በጉዳዩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ነገር ግን የዞኑ ሆነ የክልሉ አካሄድ፦ በዞኑ ከዚህ በፊት የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በእርቅ መድረክ ለመጨረስ እየተንቀሳቀሱ ነው እየተባለ ባለበት በየቀኑ ተጨማሪ አለመረጋጋት ለመፍጠር ግለሰቦችን በህግ ወጥ መንገድ ለማሳሰርና ለማሰቃየት መጀመራቸው በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ እየፈጠረ ይገኛል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም በዎላይታ ዞን እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የህግ ባለሙያዎች፣ የኮሌጅ ባለቤቶች እና የመብት ተሟጋቾች ያለምንም ህጋዊ ምክንያት መታሰራቸው፣ መደብደባቸው እና መታፈናቸው ከፍተኛ ስጋት ይፈጥራል።

በመሆኑም የሰብዓዊ መብት ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላት እየተፈጸሙ ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአስቸኳይ እና በገለልተኝነት እንዲመረምሩ፣ የታሰሩት ግለሰቦች ሁኔታን እንዲከታተሉ እና በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥረት እንዲያደርጉ፣ መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲያከብር ግፊት እንዲያደርጉ፣ ጉዳዩ ዙሪያ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲሰጥ እና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ በመገንዘብ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ጥሪ ያቀርባል።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

Ethiopia #southethiopia #Wolaita