ሐቀኛዉ ፌደራሊስት … (በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተጋባዥ ጸሓፊ)

የዛሬዉ ባለታሪካችን የተወለዱት በምዕራብ ወለጋ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በቦጂ ዲርማጂ እና በጊምቢ ተከታትለዋል። የቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ ድግሪያቸዉንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። በአዳማ የመምህራን ኮሌጅ ከተሰማሩበት የማስተማር ሥራ በግፍ ሲባረሩ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በግል ዩኒቨርስቲዎች ሲያስተምሩ ቆይተዉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን በመምህርነት ተቀላቅለዋል፣ ባለታሪካችን ሐቀኛዉ ፌደራሊስት ኦቦ በቀለ ገርባ ይባላሉ።
በኢህአዴግ ጊዜ በግፍ ለእስር የተዳረገዉ ኦቦ በቀለ ገርባ በእስር ቤት ድብደባ ተፈጽሞበታል የሚል ዜና በመሰራጨቱ ብዙዎች አዘኑ፣ ዜናዉም በስፋት ተሰራጭቶ ነበር፣ በወቅቱ ድብደባ አልተፈጸመበትም ነበርና ሐቀኛዉ በቀለ እዉነቱ ለጃዋር መሐመድ እንዲደርስ በማድረግ የሞራል የበላይነቱን አረጋገጠ። አልተደበደብኩም የሚለዉ ዜና በሰፊዉ ባይሰራጭም ከለዉጡ በሁዋላም ያኔ “ዎያኔ ደበደበዉ” ተብሎ የተሰራጨዉ ዜና ሐሰት መሆኑን መስክሯል።
በአንድ ወቅት ከትግራይ ጦርነት በፊት በአማራ ክልል ወደትግራይ የሚያስኬደዉ መንገድ ለአንድ ዓመት መዘጋቱን ኦቦ በቀለ አምርሮ ተቃዉሞ ነበር። በተለይ የመንገድ መዘጋት ያጋጠመዉ በሌላ አካባቢ ቢሆን መንግስት በኃይል እንደሚያስከፍት በመጠቆም ተቸ። በተመሳሳይ በአንድ ወቅት የእርሳቸዉ ክልል ኦሮሚያ ላይ ወደ ቤንሻንጉሏ አሶሳ የሚወስድ መንገድ በመዘጋቱ ሕዝብ መቸገሩን የሰማዉ ኦቦ በቀለ፣ ድርጊቱን በግልጽ በመቃወም መንገዱን ለማስከፈት የድርሻዉን ኃላፊነት ተወጣ፣ በዚህም የመርህ ሰዉ መሆኑን አስመሰከረ።
በክልል ጥያቄ ወቅት አጋርነት ለማሳዬት ወደ ዎላይታ ሶዶ ከፖለቲከኛ ሙላቱ ገመቹ ጋር ጎራ ባለበት ወቅት እንደሚከተለዉ ብሎ ነበር” እዚህ ክልል ስገባ መጀመሪያ በአረንጓዴነቱ በጣም ነው ደስ ያለኝ፣ አንደኛ ነገር ተስፋ ያለው ሕዝብ ለወደፊቱ ያስባል፣ የተፈጥሮ ሐብቱን ይንከባከባል መሬቱን ይንከባከባል፣ ዛፎቹን ይንከባከባል ለልጆቹ ያስተላልፋል።
ስለዚህ ስለ ወደፊታችሁ ምን ያህል አሳቢዎች እንደሆናችሁ፣ ምን ያህል መልካም ነገር ለሕባችሁ እንደምትመኙ ከምድራችሁ፣ ከአፈራችሁ ለተፈጥሮ የምታደርጉት እንክብካቤ ራሱ የሚያመለክት ይመስለኛል።” በቅርቡ በብሔሮችና ብሔረሰቦች ቀን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብዬዉ ሶዶዎችና ዲላዎች ዛፍ መትከል ከእነ እገሌ ተማሩ የሚል አሽሙረኛ ንግግር ማድረጉ ይታወሳል። ኦቦ በቀለ የተደነቀበት አንዱ በዳሞት ተራራ ላይ በደርግ ጊዜ የዎላይታ ተማሪዎች በተከሉት የጽድ ዛፍ ሲሆን፣ ጌዴኦም በቡናዉ ደን የሚታወቅ ነው።
በወቅቱ ስለ ዎላይታና የኦሮሞ ሕዝብ ትስስር
“… የጋራ ታሪክ፣ የተዋሐደ ታሪክ፣ በጋብቻ እና በጉርብትና በተለያዩ መንገዶች ተያይዘን ያለን፣ ልንነጣጠልም፣ ልንለያይም የማንችል ሕዝቦች ነን።” በማለት የታዳሚዉን ቀልብ የሳበ ንግግር አድርጓል።
በተለይ ለተበደሉ ሕዝቦች አጋርነት ስለማሳዬት
“በተበደሉ ሕዝቦች ጎን መቆም የስብአዊነት principle ነው። Martin Luther king አሜሪካዊ ሆኖ ሳለ፤ ነገር ግን አሜሪካ በጭቁን ቤትናማዉያን ላይ ስታደርግ የነበረዉን ጦርነት አብዝቶ ይቃወም ነበር” በማለት ገልጿል።
በፖለቲካ ተሳትፎዉ በግፍ ብዙ እስርና መከራ ያስተናገደዉ ኦቦ በቀለ በአንድ ወቅት ከ ኢትዮ ፎረም ሚዲያ ጋር ባደረገዉ ቃለምልልስ ከፓርቲ ፖለቲካ ሊሰናበት እንደሚችል እንደሚከተለዉ ገልጾ ነበር። “እኔ ለፖለቲካ የተፈጠርኩ ሰው እንዳልሆንኩ በጣም አዉቀዋለሁ። ብዙ ሰዎች ላያዉቁ ይችላሉ፣ እኔ ግን ዉስጤ የሚነግረኝ እንደዛ ነው፣ የፖለቲካ ሰው ያለመሆኔን፣ በፖለቲካም ያለመርካቴን ነው። …እኔ ፖለቲካ ብተዉም፣ ለሕዝቦች መብት መታገልን አልተዉም። ምክንያቱም እኔ የተፈጠርኩት አምባገነኖችን ለመታገል ነው። ግን የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ሆኜ ለመቀጠል ምናልባት፣ አንድ ቦታ ላይ ማቆም አስፈላጊ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
የሰዎች አፈጣጠር የተለዬ ነው፣ እኔ ይሄ ሐገር ፖለቲካ የሚፈልገው አይነት ስብዕና ያለኝ አይመስለኝም ሳስበዉ። …እያንዳንዱ ሐገር context የዛን ሐገር ፖለቲካ ባህል ማወቅ ይፈልጋል እና ከዛ ጋር እራስን ማዋሐድን ይፈልጋል። እኔ ዳግም ከዚህ ረዥም ጊዜ በሁዋላ ከዛ ጋር መዋሐድ የምችል አይመስለኝም። የሚመስለኝንና ልክ ነው ብዬ የማምንበትን ነገር ወደፊት እየገፋዉ መሄድ፣ መናገር፣ መጻፍ አስፈላጊ ከሆነ እነዚህን ነገሮች እየገለጽኩ መሄድ ካልሆነ በስተቀር እንደ ፖለቲካ መሪ ወይም ተሿሚ ሆኜ ለመምራት ናለማስተዳደር ዉስጤ እንደዛ አይነት ፍላጎት የለም።”
የታዋቂውን አርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን ሞት፣ ተከትሎ ከእነ ጃዋር መሐመድ ጋር ለእስር ከተዳረገበት ከተፈታ በሁዋላ ወደ አሜሪካ ያቀናዉ ኦቦ በቀለ፣ ከፓርቲ ፖለቲካ ሆነ በግሉ እራሱን ማግለሉን፣ ይፋ አድርጓል ከፖለቲካ ተሳትፎ። በአሁኑ ሰአት ብዙ የኦሮሞ ተወላጆች እንደሚገኙባት በምትታወቀዉ በሚኒሶታ በሚገኝ ዩኒበርሲቲ የኦሮምኛ ቋንቋ መምህር ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
ይህ ሐቀኛ ፈደራሊስት የሆነ ፓለቲከኛ የፓርቲ ፖለቲካ በቃኝ ያለበትን የራሱን ዉሳኔ በማክበር ከ547 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አንዷን በግል ተወዳድሮ ቢይዛት እንኳን የሞራል ድምጽ በመሆን ልዩነት መፍጠርና ለሐገርና ሕዝብም ትርጉም ያለዉ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላልና ቢያስብበት መልካም ነው። በአሜሪካ ቢኖርም ስብሰባ ሲኖር እየመጣ መሳተፍ ይችላል፣ ብዙ አምባሳደሮች በዉጪ እየኖሩ የፓርላማው አባል ናቸዉ። እዚሁስ ከሚኖሩት ስንቱ ነው ትርጉም ያለዉ የፓርላማ ተሳትፎ የሚያደርገዉ? ስለዚህ ኦቦ በቀለ ገርባ በግል ተወዳድረዉ ፓርላማ ስለመግባት ቢያስቡበት ጥሩ ይመስለኛል።
በአሜሪካ ጥገኝነት እንደጠየቁ ቢታወቅም፣ አሁንም ቢሆን የእርሳቸዉ አይነት የሞራል ድምጽ ፓርላማችን ይጎድለዋልና በግል ተወዳድረዉም ቢገቡ ለሐገራችን ጠቃሚ ነው።
ለሐቀኛዉ ፌደራሊስት ኦቦ በቀለ ገርባ ከመላ ቤተሰቡ ጋር መልካሙን ሁሉ እንመኛለን።
ከ5 ዓመት በፊት አቶ በቀለ ገርባ በዎላይታ ሶዶ ጉተራ አዳራሽ ተሞክሮ ስያካፍሉ “እናንተ ነፃነታችሁን እንዳታገኙ፣ ራሳችሁን በራሳችሁ የማስተዳደር መብታችሁን እንዳትጎናፀፉ የሚፈልጉ አካላት የማይሸርቡዎቸዉ ሴራዎች የሉም። ለዝህ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል! መታሰር ልኖር ይችላል፣ ለዛ ዝግጁ እንድትሆኑ ነው ምፈለገው። የኦሮሞ ወጣቶች እኛ እስከ መቼ ነው ምንታሰረው ? አንዳንድ ጊዜ ሰው ለመታሰር ሁሉ ይሸሽ ነበር። ለመታሰር ሁሉ ይሸሽ ነበር በኃላ ግን በተደረገው ትግሉ እየበሰለ በሚመጣበት ጊዜ የት ነው ሚሸሸው? ከትግል የት ቦታ ነው ምሸሸው? የራስህን መብት ከመጠየቅ ወዴት ነው መሸሽ የሚቻለው? ተሸሽቶስ የትኛው መብት ነው የምገኘው? መብት የሚገኘው ፊትለፊት በመጋፈጥ ነው። መጋፈጥ ያስፈልጋል። ፊትለፊት በመጋፈጥ ነው በሰላማዊ መንገድ አሁንም።” ብለው ነበር።
👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏
#Ethiopia #southethiopia #Wolaita #Oromia