1000054818

By Journalist Natnael Gecho

የ5% ፖሊሲ፣ ለሕዳጣን… የሕገመንግስት ማሻሻያ ሐሳብ… (በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተጋባዥ ጸሓፊ)

የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን በሚያስከብር መልኩ ተቀርጾ ኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዓት የምትከተል ሐገር እንድትሆን እንዳስቻላት ይታወቃል። ሥርዓቱ ለዘመናት የታፈኑ የሕዝቦችን ጥያቄ የፈታና በሐቀኝነት ከተተገበረ ያንኑ መንገድ አጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑ እርግጥ ቢሆንም፤ እንደማንኛውም ሥርዓት ጉድለቶች አሉት።

ከነዚህ አንዱ በቀጥታ ከብሔራቸዉ ጋር ከሚያያዝ ክልላቸዉ ዉጪ የሚኖሩ ሕዳጣን ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ በአብዛኛው ከተማ አካባቢዎች፣ አንዳንድ ገጠራማ አካባቢዎችም የተለያዩ ብሔርና ብሔረሰብ የሆኑ ሰዎች በማይናቅ ቁጥር እንደሚኖሩ ይታወቃል።

ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ስትፈጠር ጀምሮ ባለዉ ጊዜ በጦርነትም በአስተዳደርም፣ በሥራም፣ በንግድም፣ በሐይማኖትም እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰዋል። በኢትዮጵያ በጣም የሚያስገርም አንድ እዉነታ አለ ያም፣ ከክልሉ ዉጪ በብዙ ቁጥር የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ብሔር አማራ መሆኑ ሕዝቡ ሐገሪቷን define ከማድረጉ አንጻር የሚጠበቅና ብዙም የማያስገርም ቢሆንም፤ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘዉ ዎላይታ መሆኑ በጣም አስገራሚ ነው።

ምክንያቱም ዎላይታ ኢትዮጵያ ስትፈጠር፣ ሐገሩ እንዳይፈርስበት ከፍተኛ ጦርነት ያደረገና በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳ ሕዝብ ነው። መሰል አካባቢዎች ብዙ ጊዜ በመላዉ ሐገሪቷ ተሰራጭተዉ ይኖራሉ ተብሎ አይጠበቅም። ለዚህ ፍልሰት ግን የሕዝቡ industriousness ብቸኛ ምክንያት እንደማይሆን ግልጽ ነው። በአካባቢው በዲዛይን የተንሰራፋዉ ድሕነትና ሥራ አጥነት፣ የብሔር ጭቆና፣ መዋቅራዊ ጭቆና፣ ሕዝቡን ከቋንቋዉ ከባህሉና መሬቱ በትኖ የማጥፋት መንግስታዊና የተለያዩ ኃይሎች ፍላጎቶች ለጥናት ጥሩ መነሻ መላምት እንደሆኑ አያጠራጥርም።

የሆነዉ ሆኖ ወደ ዛሬዉ ጉዳያችን ስንመለስ አማራ፣ ዎላይታ፣ ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ትግራይ፣ ኦሮሞ፣ ሐዲያ፣ ከምባታና የመሳሰሉት ከብሔራቸዉ ክልል ዉጪ በማይናቅ ቁጥር እንደሚኖሩ ይታወቃል።

ለዚህ ጉዳይ መፍትሔ ለማበጀት አንዳንድ ሰዎች አጠቃላይ የፌደራል ሥርዓቱን ማፍረስን እንደመፍትሄ ያነሳሉ፤ ይሄ ግን በምንም አይነት ተቀባይነት ሊኖረዉ አይችልም።

አለም አቀፍ ሕጎችን መሰረት ያደረገዉ የብሔሮች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ሚገረሰስበት አማራጭ ተቀባይነት አይኑረዉ እንጂ፣ ለሐገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከብሔሮች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ጋር የማይጋጭ የአካታችነትን መፍትሔ ማበጀት ግን ይቻላል።

ለምሳሌ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ ለአንድ constituency በቂ መራጭ ሕዝብ ላልነበራቸዉ ሕዳጣን ተብሎ፣ ያለ ምርጫ የሚሰጥ 20 ወንበር መኖሩ ይታወቃል።
በሕገመንግስቱ ወሳኝ የሚባሉ የራስን እድል በራስ የመወሰን ከፍተኛ ድምጽ ከምክር ቤት አጠቃላይ አባላት የሚፈለገዉ 2/3ኛ ወይንም 66.67% አካባቢ ነው።

ስለዚህ በተመሳሳይ መርሕ በየአካባቢው በብዛት ለሚኖሩ ሕዝቦች በክልሎችና በተዋረድ ባሉ ምክር ቤቶች ከ1%_ 5% እንደየ አካባቢው ሁኔታ ያለምርጫ ቢመደብ መልካም ይመስላል። ከዚህ በፊት የነበሩ የምርጫ ክልሎች እንዳይነኩ ከተፈለገ ደግሞ ነባሩን የምክር ቤቶች ወንበር ቁጥር እንደ 95% በመዉሰድ 5% መጨመር ይቻላል።

በሕገመንግስቱ የተፈቀደዉ የማንኛውም ዜጋ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያዩ ምክንያት ሕዳጣን እድሉን ላያገኙ ስለሚችሉ ይሄንን የሚቀርፍና የብሔሮቹንም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን በማይጋፋ መልኩ ሕገመንግሥት ማሻሻል ያለብን ይመስለኛል። ይህም በየቦታዉ የሚደርሰዉን ጥቃትና የመገፋት ስሜት ለማስተካከል ያግዛል። ይህ በሕግ ምሁራን በደምብ ዳብሮ መተግበር ያለበት ምክረ ሐሳብ ነው።

👉🤝 እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚንፀባረቅበት መረጃዎች🙌
👉🤝 ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ነን🙏
👉🤝 ስለዘውትር አብሮነታችሁና ድጋፍ እናመሰግናለን🤲
🤜👁👀 #WolaitaTimes ሚዲያ👏

#Ethiopia