በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኦቶና መማሪያና ህክምና ሆስፒታል በሲቲ ስካን እና በኤም.አር.አይ ማሽን የታገዘ የጨረራ ምርመራ አገልግሎት መሰጠት ተጀመረ።
ይህ የአገልግሎት በሆስፒታሉ መጀመር የአካባቢውን ነዋሪ ብቻ ሳይሆን የአጎራባች ዞን ሕዝቦችን ጭምር አላስፈላጊ ከሆነ የገንዘብ ወጪ እና እንግልት እንደሚታደግ ተጠቁሟል።
ማሽኖቹን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር 80 ሚሊየን ብር በመመደብ እንዲገዙ ማድረጉም ተገልጿል።
በሰው ልጅ የውስጥ አካላት ላይ የሚያጋጥሙ የጤና እክሎችን ለመመርመር አጋዥ ከሆኑ የዘመኑ የምርመራ መሳሪያዎች ውስጥ የሲቲ ስካን እና ኤም. አር. አይ መሳሪዎች ዋንኞቹ እንደሆኑ ነው በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኦቶና ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቩ ዲን የሆኑት ዶ/ር ጌታሁን ሞላ የሚናገሩት።
እጅግ የተወሳሰቡና ቀደም ሲል ለመለየት እጅግ አስቸጋሪ የነበሩ በሽታዎችንና የሰውነት እክሎችን ለመለየት የሲቲ ስካን እና ኤም. አር. አይ መሳሪዎች ጠቀሜታቸው ጉልህ መሆኑን ዶ/ር ጌታሁን ገልጸዋል።
ያለ ቀዶ ሕክምና የሰውነትን ውስጣዊ አካል መመርመር የሚያስችሉት የሲቲ ስካን እና ኤም. አር. አይ መሳሪዎች ከዚህ ቀደም በኦቶና መማሪያና ህክምና ሆስፒታል አለመኖሩ ተገልጋዩ ህብረተሰብ ብዙ ርቀት በመሄድ ለከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እና እንግልት ሲዳረግ መቆየቱንም ዶ/ር ጌታሁን አሳውቀዋል።
ሲቲ ስካንና ኤም.አር.አይ ስካን የተለያዩ የአካል ክፍሎችንና የሕብረ ሕዋሳትን ቅርጽ እንዲሁም በሰውነታችን የውስጥ አካል ያሉ ችግሮችን ለይቶ በማሳወቅ ፈጣንና ቀልጣፋ የምርመራ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ጌታሁን፤ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር 80 ሚሊየን ብር በመመደብ ማሽኖቹ ተገዝተው አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻሉንም አውስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው መማሪያና ህክምና ሆስፒታል በሲቲ ስካን እና በኤም.አር.አይ የታገዘ የጨረራ ምርመራ አገልግሎት መጀመሩ የአካባቢውን ነዋሪ ብቻ ሳይሆን የአጎራባች ዞን ሕዝቦችን ጭምር አላስፈላጊ ከሆነ የገንዘብ ወጪ እና እንግልት እንደሚታደግ ዶ/ር ጌታሁን ሞላ ገልጸዋል ሲል የዩኒቨርስቲው ኮሙኒኬሽን ዳይረክቴር ዘግቧል።